በሶማሊያ ውስጥ ለኢትዮጵያ የሰላም፣ የጸጥታ፣ የደህንነት ስጋት እስካለ ድረስ ኢትዮጵያ የማንንም ፈቃድ ሳትጠይቅ አስፈላጊውን እርምጃ ከመውሰድ ወደኋላ የሚያግዳት ጉዳይ አይኖርም
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃልአቀባይ ነብዩ ተድላ ‹‹ግብፅ ወታደሮቿን ለሰላም ማስከበር ተልዕኮ በሶማሊያ ለማሰለፍ ያለት ፍላጎት ኢትጵያን እንደአዲስ የሚያሸብር ጉዳይ አይደለም›› ሲሉ ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ተናግረዋል፡፡
‹‹ሶማሊያ እንደማንኛውም ሉዓላዊ መንግስት የወታደራዊም ሆነ ሎሎች ዓይነት ስምምነቶች ከፈለገችው አገር ጋር የማድረግ መብት አላት ›› ያሉት ቃል አቀባዩ ‹‹ ከዚህ ቀደምም ኢትዮጵያን እና ግብጽን ጨምሮ ከሱዳን፣ ከኡጋንዳ ፤ ከኤምሬትስ፣ ከሳውዲ እና ሌሎች አገራት ጋር ተመሳሳይ ግንኙነቶች ›› የነበሯት መሆኑን በማስታወስ ሰሞንኛው ጉዳይ እንዳ አዲስ መንግስታቸውን የሚያሸብር አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡
በሶማሊያ የተሰማራው የአፍሪካ የሽግግር ተልዕኮ አትሚስ በተያዘው የ2024 እ.አ.አ. በወርሃ ታህሳስ ተልዕኮውን አጠናቅቆ ለሶማሊያ ብሔራዊ መንግስትና ተቋማት አስረክቦ እንዲወጣ እቅድ እንደነበረ ያስታወሱት ቃል አቀባዩ ‹‹ ነገር ግን ከአልሸባብ መጠናከር ጋር ተያይዞ እቅዱን መከለስ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷልም ›› ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
ነብዩ አያይዘውም ‹‹ ኢትዮጵያ ወታደር እንዳዋጣ አገር፣ የጸጥታ እና የደህንነት ስጋት እንዳለባት አገር፤ ከ2000 ኪ.ሜ በላይ ድንበር ከሶማሊያ ጋር እንደምትጋራ አገር፣ እንደጎረቤት አገር፣ ድርሻ እንዳለው አገር ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተለችው ትገኛለች ›› ብለዋል፡፡
አክለውም ‹‹ በሶማሊያ ውስጥ ለኢትዮጵያ የሰላም፣ የጸጥታ፣ የደህንነት ስጋት እስካለ ድረስ ኢትዮጵያ የማንንም ፈቃድ ሳትጠይቅ አስፈላጊውን እርምጃ ከመውሰድ ወደኋላ የሚያግዳት ጉዳይ አይኖርም ›› ሲሉ ፈርጠም አድርገው ተናግረዋል፡፡
FBC