“ዳግም ቪዲዮውን የመመለከት አቅም አጣሁ” ይላል በተመሳሳይ መድረክ ላይ ደጋግሞ የተሳተፈ ታዋቂ አትሌት። የማራቶን አሰልጣኝ ገመዶ ደደፎ በቤተመንግስት ልዩ የዕውቅና ግብዣና ሽልማት ስነ ስርዓት ላይ ሕዝብን ባቀለለ፣ የአገርን ክብርና ብሄራዊ ሃላፊነትን ባራከሰ መልኩ ያስተላለፈውን መልዕክት ተከትሎ አሳቡን የሰጠው አትሌት ” ገመዶ ከታሪካዊው የኦሊምፒክ ክብር ጎን ለጎን ለራሱ ብሄራዊ ውርደትን አከናንቧል። ይህ ታሪኩ ነው” ብሏል።
የባለቤቱ ሌይላ አማንን እግር ተከትሎ ወደ አትሌቲክስ ሰፈር ብቅ ያለው ገመዶ ደደፎ፣ በወቅቱ የፌዴሬሽኑ የቴክኒክ ክፍል ሃላፊ በነበሩት አቶ ዱቤ ጅሎ አማካይነት በር ተከፈተለት። አቶ ዱቤ ጅሎ የፌዴሬሽኑን የሃላፊነት ወንበር ተጠቅሞ ከጣሊያናዊው ሚስተር ዶናዶኒ ጋር በማናጀርነት ይሰራ ስለነበርና አትሌት ሌይላ ከዶናዶኒ ጋር ትሰራ ስለነበር አጋጣሚው ለገመዶና ዱቤ መገናኘት በር ከፈተ።
በርካቶች እንደሚያውቁት የስልጠና ፕሮግራም በማናጀሮቻቸው አማካይነት ለሚነደፍላቸው አትሌቶች ሰዓት በመያዝና ቁሳቁስ በማቅረብ የሚሰሩ፣ የአትሌቶቹ የትዳር ጓደኛ የሆኑ ለራሳቸው የአሰልጣኝነት ክብር የሚሰጡበት አጋጣሚ የሚቆጣጠረው አካል ባለመኖሩ በተመሳሳይ መልኩ ገመዶም ራሱን አሰልጣኝ አደረገ።
ከዚያ በሁዋላ ራሱን በስልጠና ድግግሞሽ እንዲሁም ከማናጀሮች በሚደረግ ድጋፍ ታግዞ ራሱን አደረጀ። ኮተቤም ገብቶ ለክ እንደ ዱቤ ጅሎ ስፖርት ተምሯል። ሊካድ በማይችል መልኩም በተወሰኑ አትሌቶች ውጤት አመጣ። ሚስቱን ግን ወጥ አቋም ያላት አትሌት ማድረግ አልቻለም።
እንግዲህ በዚህ መነሻ ታሪኩ ነው ገመዶ ዶክተር ወልደ መስቀልን ጠቅሶ ራሱን ለንፅጽር ለማቅረብ የዳዳው። በአስተሳሰብም ሆነ በስራው ገና አንጭጭ እንደሆነ ባሳየበት ንግግሩ ብዙዎች የተቃወሙት ገመዶ ራሱን ጎዳ። ብሄራዊ ጀግንነትና ታሪካዊ እውቅናን በዚህ ደረጃ ለማራከስ የታደፈርበት አግባብም ከዚሁ እንጭጭነቱ የመነጨ እንደሆነ በስፋት አስተያየት ተሰጠ። ከዚያም በላይ ይህ ተግባር እንዳይለመድና በለኤሎች እንዳይደገም፣ ለመጪው ትውልድ ሁሉ መማሪያ እንዲሆን ገመዶ አስተማሪ ቅጣት መቀጣት እንዳለበት በርካቶች አጠንክረው አሳሰቡ።
በ33ኛው የፓሪስ ኦሎምፒክ ጨዋታዎች ላይ ተሳትፎ ለተመለሰው የኢትዮጵያ ልዑክ በብሔራዊ ቤተ መንግሥት የዕውቅና መርሐ ግብር ሲካሄድ ፕሬዚዚዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ እጅግ ድንቅ ንግግር አድርገው ነበር። ፕሬዚዳንቷ ልብ በሚነካው ንግግራቸው የወርቅ ሜዳሊያ ላገኘው ታምራት ቶላ ስልክ መደወላቸውን ሲያስታውቁ ” በተቀመጥኩበት መቀመጫ፣ በኢትዮጵያ ህዝብ ስም ስልክ ደውዬ ደስታዬን ገልጬለታለሁ። ክብርም ይገባዋል” ካሉ በሁዋላ ሲሳይን የገለጹበት አገባብ ደግሞ ልዩ ነበር።
” ሲሳይ ለምን ፓሪስ እንደሄደ የሚያውቅ ነበር” ካሉ በሁዋላ ስላመመው ራሱን ተጠራጥሮ ወንድሙን ታምራት እንዲተካው አድርጓል። ሲሳይን የህብረት፣ የፍቅር፣ የብሄራዊ ጅግንነት ምሳሌ አድርገው ያቀረቡት ሳህለ ወርቅ፣ሲሳይ ህመሙን ሚስጥር አድርጎ ቢሮጥ ሊመጣ የሚችለውን ውጤት የሚያውቀው ፈጣሪ ብቻ መሆኑን አመልክተዋል። አያይዘውም ተግባሩ ልዩ ትርጉም ያለው ውጤት እንዲመዘገብ ምክንያት በመሆኑን አጉልተው አመስግነውታል።
” እኔ ብሎ አላሰበም። እኛ ብሎ፣ ህዝብ ብሎ አሰበ” ሲሉ ሲሳይን ያጎሉት ፕሬዚዳንቷ፣ የሲሳይ ድንቅ ውሳኔ ለስፖርቱ ብቻ ሳይሆን በሁሉም መስክ፣ ለሁላችንም ትምህርት ነው። ይህ የአስተሳሰብ ትልቅነት ነው” ብለዋል። ፕሬዚዳንቷ መስመር አሲዘው በደማቁ ገመዶ የሚያስለጥነውን አትሌት የስብዕናና የአስተሳሰብ ትልቅነት ሲገልጹ ደጋግመው ከሚያጨበቡት መካለ አንዱ ገመዶ ራሱ ነበር።
በዚህ ስሜት ውስጥ ሆኖ ለሽልማት የተጋበዘው ገመዶ በታላቅ ብሄራዊ ክብር፣ በከበደው የአገር ታሪክና ዝና ወደ መድረክ ለሽልማት ሲጋበዝ የሰጠው ግብረ ምላሽ ከሲሳይ ጫማ ስር የማይጠጋ፣ እጅግ የረከሰ፣ ለኢትዮጵያዊያን በየትኛውም ደረጃ የማይገባቸው፣ ክብረ ነክ ሆኖ መገኘቱ የዕለቱ አስደንጋጭ ክስተት ነበር። በየትኛውም ዓይነት ሌላ መድረክም ሆነ አጋጣሚ ሊፋቅ የማይችል በታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ጉድፍ ለራሱ ያኖረበት አጋጣሚ ሆነ።
በዛ የከበረ መድረክ የቀረበለትን ምስጋናና እውቅና ህጻናት፣ አዋቂዎች፣ ጀግኖች፣ ተተኪዎች፣ ታላላቅ ሰዎች በጥቅሉ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ እያየ አራከሰ። ይህ ኪሳራው በየትኛውም ደረጃ በካሳም ሆነ በይቅርታ ሊፋቅ የማይችል ሃፍረቱ ሆኖለት።
በየትኛውም ዓለም ሽልማት ምንም ይሁን ምን ሸላሚ እንጂ ተሸላሚ የሚመርጠው እንዳልሆነ እየታወቀ፣ በታላቅ አገራዊ ክብርና እውቅና የተለወሰ የሁለት ሚሊዮን ብር ሽልማትን መግፋቱ ነበር ህዝብን ከዳር እስከዳር ያስቀየመው፣ ያስቆጣው ” ዳግም አትሌቲክስ ሰፈር ድርሽ እንዳይል፣ መቀጣጫ እንዳይሆን ተደርጎ ይቀጣ፣ ይታገድ” የሚል የከረር ተቃውሞ እንዲሰነዘር ምክንያት የሆነው።
በወርቅ ቅብ ታትሞ የተዘጋጀለትን ታላቅ ክብር በሳንቲም አስልቶ ለራሱ የሃፍረት ታሪክን የጻፈ፣ “አልጋ ሲሉት አመድ” እንደሚባለው ራሱን ከክብር አውርዶ የከሰከሰው ገመዶ፣ በመርሐ-ግብሩ ላይ ከኢትዮጵያ መንግሥት የተበረከተለትን የሁለት ሚሊዮን ብር ሽልማት አልቀበልም ካለ በሁዋላ አፍታም ሳይቆይ ይቅርታ ጠይቆ ገንዘቡን ለመውሰድ ቢሞክርም የሚኒስትር መስሪያ ቤቱ እንደከለከለው ተሰምቷል። መከልከል ብቻ ሳይሆን ሌላ ቅጣትም እያዘጋጀለት እንደሆነ ታውቋል።
ወዲያው ይቅርታ መጠየቁ ብቻ ሳይሆን ገመዶ ይህን ባለ ማግስትም በሌሊት ኢትዮጵያ ቴሌቪሽን ወረፋ በመያዝ ይቅርታ ለመጠየቅ አመልክቶ፣ ባገኘው ዕድል ወዶና ፈቅዶ “ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴንና የኢትዮጵያን ህዝብ ደግሜ ደጋግሜ ይቅርታ እጠይቃለሁ” ሲል ተደምጧል። ገመዶ በወቅቱ ስሜታዊ ሆኖ ስህተት መስራቱን ገልጿል።
“በተናገርኩትና በውሳኔዬ አልጸጸትም። ያደረኩት ሁሉ ትክክል ነው” በማለት ለአንድ ሚዲያ በኩራት ራሱን እያወደሰ የተናገረው ገመዶ የገንዘብ ሽልማቱን ያልተቀበለው “ለሙያው የሚሰጠው ክብር ማነስ“ ስላበሳጨው እንደሆነ መሆኑን አውስቷል። አክሎም ከሀገር የተበረከተለትን ሽልማት መግፋቱና በመድረኩ ላይ ያደረገው ንግግር ስህተት በመሆኑ፤ የኢትዮጵያ ህዝብና ፕሬዚዳንቷን ይቅርታ መጠየቅ እንደሚፈልግ አስታውቋል፡፡
“ቀድሞ ነበር አልሞ መደቆስ፣ ሁዋላ ምን ያደርጋል ድስት ጥዶ ማልቀስ ” እንዲሉ አስቀድሞ ወርቃማ ታሪኩን በእብሪት ያጠለሸው አሰልጣኝ ገመዶ ደደፎ ሽልማቱን ከሀገሪቱ ርዕሰ-ብሔር እጅ በክብር ተቀብሎ፤ ከአሰልጣኝነት ሙያ ጋር ተያይዞ ያሉትን ቅሬታዎች በሌላ መድረክ ሊያነሳቸው ይችል እንደነበረም በሌሊት ወረፋ ይዞ በኢቲቪ በኩል አስታውቋል።
ከዚህ ቀደም የትሌቲክስ አሰልጣኞች ከአትሌቶች እኩል ዕውቅና እና ሽልማት ሊሰጣቸው እንደሚገባ በተደጋጋሚ ጥያቄ አቅርበናል የሚለው አሰልጣኙ፤ “ብዙ ችግሮች ተደማምረው ስሜታዊ ስላደረጉኝ ነው ሽልማቱን አልቀበልም ያልኩት” ብሏል።
ድርጊቱ ያልተገባ መሆኑን በመረዳትም ከመርሐ-ግብሩ መጠናቀቅ በኃላ ወዲያውኑ ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴን ይቅርታ ስለመጠየቁ ገልጿል፡፡
“ለመሆኑ ስንት ብር እንዲሰጥዎ ነበር የፈለጉት” የሚል ጥያቄ ከኢቲቪ የቀረበለት አሰልጣኝ ገመዶ ደደፎ፤ “ለእኛ እንኳን ሁለት ሚሊዮን ብር ሁለት ብርም ትልቅ ነው፤ ስጦታውን መግፋት ትክክል አልነበረም” የሚል ምላሽ ሰጥቷል፡፡
አንድም ቀን ከሀገር ገንዘብ አስቀድሞ እንደማያውቅ እና እስካሁን እየሰራ ያለው ያለክፍያ መሆኑን የሚናገረው አሰልጣኙ፤ በድርጊቱ ህዝቡን ይቅርታ ቢጠይቅም የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር አሰራር ግን ትክክል አይደለም የሚል እምነት እንዳለው ገልጿል። የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱን ይቅርታ እንደማይጠይቅም እዛው መድረክ ላይ አስታውቋል።
አሰልጣኝ ገመዶ ወደ ኢቢሲ ያለማንም ጫና በገዛ ፈቃዱ ህዝቡን እና ፕሬዚዳንቷን ይቅርታ ለመጠየቅ መምጣቱንም ገልጾ የሰጠው አስተያየት ከተሰማም በሁዋላ ከቅርብ ሰዎቹ ሳይቀር ወቀሳው ጋብ አላለለትም።
የአገር መከላከያ አባላት ደማቸውን፣ ህይወታቸውን፣ ኑሯቸውን ሁሉ ለአገር እየከፈሉ የሱን ቅንታት የምታክል እንኳን ክብርና ሽልማት እንደማያገኙ በማስታወስ ገመዶ የህሊና ግልሙትና መፈርጸሙን በርካቶች በማህበራዊ ሚዲያ ጽፈዋል።
ሽልማቱ የአስራ አንድ ዶክተሮች የዓመት ደመወዝ መሆኑን ያመለከቱ በማናጀርነት ደም ተፈተው ከሚሮጡ አትሌቶች የሚያገኘው የአስራ አምስት በመቶ ኮሚሽን ልቡን ስለነፋው እንደሆነ ጠቁመው ይህ ፈቃዱ እንዲሰረዝ የጠየቁም ጥቂት አይደሉም።
ያሳየው ባህሪና፣ በብሄራዊ ደረጃ በተዘጋጀ የአገሪቱ ትልቁ መድረክ ላይ ያንጸባረቀው ሁሉ ተደምሮ ሲታሰብ ያለፉት ሰላሳ ዓመታት የታየው የስነምግባር ጉድለትና አገራዊ አስተሳሰብ ውድቀት ማሳያ አድርገው ያዩትም አሉ። እስካሁን ድረስ ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም ሆነ ከአትሌቲክስ ፌዴሬሽን በይፋ ምንም የተባለ ነገር የለም።
በሌላ በኩል ገመዶ ታሰረ በሚል ኤሊያስ መሰረትን ጨምሮ በስፋት ሲሰራጩት የነበረው ወሬ ሃሰት መሆኑን ገመዶ ራሱ ” በሰላም ቤቴ አለሁ” ሲል አስተባብሏል።