ታዬ አቅጸስላሴ “ኢትዮጵያ ትክክለኛ ዲፕሎማት አገኘች” ያስባለ መገልጫ ሰጥተዋል። ንግግራቸውን፣ የንግግራቸው ፍስት፣ የሚመርጡዋቸው ቃላቶች ከዚህ ቀደም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩትን ካድሬዎች ፋይል ዳግም እንዲበረበር አድርጓል። ሻለቃ ጎሹ ወልዴ የታሰቡበትን መግለጫ የሰጡት አምባሳደር ታዬ አንኳር የፖሊሲ ጉዳዮችን ለአገሪቱ ሚዲያዎች አመላክተዋል።
ሶማሊያ ሙሉ ጠንካራ የፀጥታ ተቋም እጇ ላይ እስኪገባ ድረስ ኢትዮጵያ ድጋፏን እንደምትቀጥል አምባሳደር ታዬ አፅቀሥላሴ አረጋግጠዋል። ይሁንና ሶማሊያ አካባቢውን ለማተራመስ ከሚጥሩ ያሏቸው አካላት ጋር የምታደርገው እንቅስቃሴ “በአዘቦት የሚታለፍ ነገር አይደለም”፣ ስለሆነም ሶማሊያ ይህንን ልታቆም ልታቆም ይገባል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
“ሽብር ፓኬጅ ነው ይሸጣል፣ አልሸባብ ሃብታም ነው፣ ድርጅት፣ ፖለቲካ፣ ፖለቲከኛ፣ አገራትን ይገዛል፣ ክህሎቱም አለው፣ ምሱ ደም ነው ወዘተ ” ሲሉ ያስቀመጧቸው አንኳር ጉዳዮችና የስጋት እይታቸው እፊታቸው ለተቀመጡ የሚዲያ ሰዎች አጀንዳ የመስጠት ያህል እንደሆነ ንግግራቸውን የሰሙ በቅጽበት አስተያየት ሰጥተዋል። ኢትዮጵያ ውስጥ እዛም እዚህም እንደሚነቀሳቀሱት አይነት ሳይሆን አልሸባብ ርዕዮዓለም ያለው እንደሆነ በመጠቆም ሚዲያዎች ይህንኑ አስፍተው ለህዝብ እንዲያስረዱ አቅጣጫ የመስጠት ያህል በዲፕሎማቲክ ቋንቋ ገልጸዋል።
“አልሻባብ ርዕዮት የሚነዳው ሃብታም ድርጅት ነው” ያሉት አምባሳደር ታዬ አፅቀስላሴ ለመጀመሪያ ጊዜ አገራዊ ሃላፊነታቸውን በጥንቃቄ እንዲወጡ በተማጸኗቸው የሚዲያ ሰዎች ፊት ሲቀርቡ። ሚኒስትሩ አልሸባብ ሃብታም ስለሆነ ሰዎችን፣ ፖለቲካንና አገራትን የመግዛት አቅምም ክህሎትም እንዳለው አስቀድመው በማስታወቅ ነው። ይህን ድርጅት እንደ ቀድሞ አብሮ መታገል የኢትዮጵያ አቋም መሆኑን ይፋ አድርገዋል።
“አሸባሪ ምሱ ደም ነው” ሲሉ አልሸባብን በግብሩ ሰይመው እጅግ በተመረጡ ቃላቶች ማብራሪያ የሰጡት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፣ ይህን እጁ ረዥም ደም ቀለቡ የሆነ አሸባሪ ኢትዮጵያ በሺህ የሚቆጠሩ ሴትና ወንድ ልጆቿን በመሰዋት የሶማሌ ህዝብ የማይረሳውን ውለታ ማስቀመጧን አመልክተዋል።
አምባሳደር ታዬ አፅቀስላሴ ” ኢትዮጵያ ከረዥም ዓመታት በሁዋላ ሞገስ ያለው ዲፕሎማት አገነች” የሚያስብለውን ማብራሪያቸውን ሲሰጡ ህይወቱን፣ ደሙን፣ አጥንቱን የገበረውን የአገር መከላከያ ሰራዊት ማብጠልጠል እጅግ የሚያም መሆኑን ያስታውቁበት አግባብ የንግግራቸው ሁሉ ምሰሶ ነበር።
” መንግስት እንደ አክቲቪስት ከሆነ አደጋ ነው” በማለት “አንዳንድ” ያሉት ላይ እንዲሰመርበት ጠይቀው ሚኒስትሩ እንዳሉት የአንድ አገር ከፍተኛ ባለስልጣናት ውድ ህይወት ከፍለው የአገር መከላከያ የሰጡትን ምላሽ በተራ አክቲቪስትነት ፈርጀውታል። ብዙም ሳይዘረዝሩ ” አሳፋሪ፣ እንደ ኢትዮጵያዊ የሚያም” ሲሉ ህዝብና ሲያደምጡዋቸው የነበሩ ሚዲያዎች እንዲያሰምሩበት አስረግጠው ተናግረዋል።
ይህ ደም ምሱ የሆነ አሸባሪ ቡድን ለሶማሊያ ብቻ ሳይሆን በአካባቢው ላሉ አገሮች ሁሉ አስጊ በመሆኑ ኢትዮጵያ ቀድሞ እንደምታደርገው በትብብር የመታገል አጀንዳ እንዳላት፣ ይህ አጀንዳዋ ደግሞ ብሄራዊ ጥቅሟ እንደሆነ አውስተዋል።
እንደ አንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ምንም ዓይነት የፀጥታ ሥጋት እንዲኖር አልፈልግም ነገር ግን በኢትዮጵያ አቅም በተለይም በሕዝቦቿ ስለምተማመን እንቅልፍ አልባ ሌሊት የለኝም፡፡ ግብፅ በሶማሊያ በኩል መጥታ ኢትዮጵያን አጣቢቂኝ ውስጥ መክተት ትችላለች ማለት የቀን ቅዠት ነው።
ሶማሊያ የራሷን ሰራዊት ገንብታ አልሸባብን መቋቋም እስክትችል ኢትዮጵያ አስፈላጊውን ሁሉ እንደምታደርግ ያወሱት አምባሳደር ታዬ አፅቀስላሴ ፣ ሶማሊያ የኢትዮጵያን እድገት የማይፈልጉ ሃሎችን ከመሰብሰብ እንድትቆጠብ አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ ፎላጎት ይህ ሆኖ ሳለ “አንዳንድ ” ያሏቸው የሶማሊያ ከፍተኛ ባለስልጣናት የእለት ተእለት ስራቸው እስኪመስል ድረስ ውድ ህይወቱን የከፍለውን የአገር መከላከያ ሰራዊት ማብጠልጠል ላይ መጠመዳቸው አሳዛኝ መሆኑን ተናግረዋል።
መንግስት ያለፈውን በማስታወስ፣ የወደፊቱን በማየት ሊንቀሳቀስ እንደሚገባው ያመለከቱት አምባሳደር ታዬ፣ ” መንግስት አስተውሎ፣ በአርማሞ አለው” ሲሉ ደረጃውን ጠብቆ ሊራመድ እንደሚገባ አመልክተዋል። እንደ አክቲቪስት፣ ግብረ ሰናይ ተቋማትና ድርጅቶች ከሆነ አደጋ እንዳለው ገልጸው የተግሳጽ ዓይነት መልዕክት አስተላልፈዋል።
” በአፍሪካ አንድ ችግር አለ” ሲሉ ልምዳቸውን አጣቅሰው ሲናገሩ ” የአፍሪካ ፖለቲካ የጎደለው ነገር ፖለቲካውን ከፍ ባለ ደረጃ ማስኬድ ነው” ብለዋል። አምባሳደር ታዬ አፅቀስላሴ “አንዳንድ” ያሉዋቸው የሶማሊያ ባለስልጣናት በናይሮቢና በአናካራ ውይይት የግንኙነት መርህ ያስቀመጠ ገንቢ ንግግር ተደርጎ ሳለ የመንግስት ሃላፊነትን በማይመጥን መልኩ አመጽን ሲሰብኩ እንደሚውሉ አመልክተዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የሶማሊያ መንግሥት ወደ ሰላም ሊመጣ እና አሸባብን በጋራ መዋጋታችንን ልንቀጥል ይገባል ሲሉ ጥሪ አድርገዋል። ሶማሊያ ሙሉ ጠንካራ የፀጥታ ተቋም እጇ ላይ እስኪገባ ድረስ ኢትዮጵያ ድጋፏን እንደምትቀጥልም አረጋግጠዋል። ይሁንና ሶማሊያ አካባቢውን ለማተራመስ ከሚጥሩ ያሏቸው አካላት ጋር የምታደርገው እንቅስቃሴ “በአዘቦት የሚታለፍ ነገር አይደለም”፣ ስለሆነም ሶማሊያ ህንን ልታቆም ይገባል ብለዋል።
የአፍሪካ ሕብረት የሽግግር ተልዕኮ (አትሚስ) በቀጣዩ ጥር ወር ተጠናቆ በቀጣይ AUSOM የሚበል የተለያዩ ሀገራት ጥምር ጦር ይዋቀራል ያሉት አምባሳደር ታዬ አፅቀ ሥላሴ የዚህ አወቃቀር ሁኔታ በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ላይ “አዲስ ሥጋት” ይዞ መምጣቱን መንግሥታቸው ሰሞኑን ያስታወቀ ሲሆን በዚህ ሂደት ሶማሊያ የኢትዮጵያን የተሳትፎ ጉዳይ በውል ታጤናለች የሚል እምነት መኖሩን አብራርተዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ሀገራትም ሆነ ከሌሎች ሀገራት ጋር የሠመረ ግንኙነት እንዲኖራት ጥረት ከማድረግ ወደ ኋላ እንደማትል ሲያመላክቱ፣ የውጭ የዲፕሎማሲ ዋና ምሶሶ የሆነው ግን ቅድሚያ ለጎረቤት አገር የሚለው መርህ እንደሆነ ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያዊነትንና የአገርን ልዕልና አጉልቶ በሚያሳየውና ስሜትን በሚያርደው መግለጫቸው አምባሳደር ታዬ አፅቀስላሴ ያኢትዮጵያ ከሶማሊያ መንግስት ጋር ያሉ ልዩነቶችን በውይይትና በዲፕሎማሲያዊ መንገድ የመፍታት ፍላጎት አላት ሲሉ ደጋግመው ነው ያስታወቁት።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በቀጣናዊ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ያተኮረ ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጡ እንዳሉት የኢትዮጵያ የውጭ ፖሊሲ ከጎረቤት ሀገራት ግንኙነት ማጠናከርን ማዕከል ያደረገ መሆኑን አጽንዖት ሰጥተው ካስታወቁ በሁዋላ። ሶማሊያ ለአካባቢ ሰላም ከጎረቤት አገራት አገራት ጋር የምታደርገውን ግንኙነት ዳግም መመልከት አንዳለበት መክረዋል።
“ከኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር የመግባቢያ ሰነድ ከተፈራረመች በኋላ ከሶማሊያ ጋር ተከታታይ ምክክር አድርጋለች፤ ውጤትም አሳይቷል። የኢትዮጵያ ፍላጎት ችግሮችን በሰለጠ የዲፕሎማሲ መንገድ መፍታት ነው ” ሲሉም ጉዳዩን በውይይት ለመፍታት የተኬደበትን ርቀት አሳይተዋል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እ.ኤ.አ ከ2005 ጀምሮ ሶማሊያ እንደ ሀገር እንድትቆም ብዙ ዋጋ መክፈሉን አንስተው የሶማሊያ መሪዎች እንዲያስቡ አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ያደረገውን ተጋድሎና የተከፈለውን መሰዋእትነት ማጣጣል ተገቢነት እንደሌለው ከማሳሰብ አልፈው ” ኢትዮጵያ ለሶማሊያ ምን አጎድለች፣ ምን ነፈገች?” የሚል ጥያቄም ሲያነሱ ተሰምተዋል።
ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ በመሆኗ ለአፍሪካ ሀገራት ልዩ ትኩረት እንደምትሰጥ ያስታወቁት አምባሳደር ታዬ፣ ህብረቱ ስራውን በተገቢው መንገድ እንዲሰራ አስፈላጊው ድጋፍ ታደርጋለች ብለዋል።
ከሶማሊያ ጋር ያለውን አለመግባባት በሰላማዊ መፍታት እንደሚገባ በመግለጽ፣ ኢትዮጵያ ዝግጁ ናትም ብለዋል። “አምባሳደሩ መንግስት አክቲቪስት ከሆነ አደገኛ ነው” በማለት የሰጡት የጥልቅ ምልከታና ልምድ ምክር ለሶማሊያ ብቻም ሳይሆን አገር ውስጥ ዋና ስራቸውን በአክቲቪዘም ቀይረው እዛው ላይ ሲያቦኩ ለሚውሉ የአገር ውስጥ ባለስልጣናትም ትምህርት የሰጠ ሆኗል።
በሌላ ዜና በሶማሊላንድ የሚገኘው የኢትዮጵያ ቆንስላ ጽ/ቤት አዲስ አምባሳደር ተሹሞለታል። ተሿሚው አምባሳደር ተሾመ ሹንዴ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ ዘውዴ ባለፈው ሰኔ ለ24 የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሠራተኛ ለነበሩ ዲፕሎማቶች የባለ ሙሉ ስልጣን አምባሳደር እና የአምባሳደርነት ሹመት በሰጡበት ወቅት የአምባሳደርነት ሹመት የተሰጣቸውና አሁን ለዚህ ቆንስላ ጽሕፈት ቤት የተመደቡ ናቸው። ኢትዮጵያ ሶማሊላንድ ውስጥ ባላት የቆንስላ ጽ/ቤት ልዩ መልዕክተኛ ሆነው ሲያገለግሉ የቆዩት አምባሳደር ደሊል ከድር ነበሩ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ታዬ አፅቀ ሥላሴ የግብጽ ወደ ሶመሊያ የጦር ኃይል ማስገባቷ ኢትዮጵያን እንቅልፍ የሚያሳጣ ጉዳይ እንዳልሆነና ይልቁንም ከሕዳሴ ግድብ ጋር ያለውን ልዩነት ለመፍታት አሁንም እንፈልጋለን ብለዋል። የኢትዮጵያን የባሕር በር የማግኘት ጉዳይም “ካጣነው በኋላ የገባን” ብለውታል።