በፓሪሱ የኦሊምፒክ ውድድር ኢትዮጵያን ከወከሉት አትሌቶች መካከል አንዱ የሆነው ለሜቻ የሶስት ሺህ ሜትር መሰናክል ውድድር መጨረሻ ዙር ላይ በደረሰበት ግጭት ሳቢያ ይህ እስከተጻፈ ድረስ መንቃት እንዳልቻለ ኢትዮሪቪው ስምታለች። በዚሁ ሳቢያ በአምቡላንስ ውስጥ ህክምና እየተደረገለት ወደ ሆስፒታል ተወስዷል።
የርቀቱ ባለ ክብረወሰን ለሜቻ አሁን ላይ ያለበት የጤና ሁኔታ አስፈሪ ባይሆንም፣ ሙሉ በሙሉ አልነቃም። መጨረሻው ዙር ላይ ለመንጨቅ ዝግጅት ላይ እያለ ከመሰናክሉ ጋር ተጋጭቶ የወደቀው ለሜቻ አስፈላጊው ሁሉ የህክምና አገዛ እንድተደረገለትና እየተደረገለት መሆኑን ተጠኢንነት ሁኔታውን የሚከታተሉ አመልክተዋል።
በ3000 ሜትር መሰናክል ወንዶች ፍጻሜ አትሌት ለሜቻ ግርማ በመጨረሻው ዙር ላይ ከመሰናክል ጋር ተጋጭቶ በመውደቁን ተከትሎ አትሌቶች መደናገጣቸው ተነግሯል።
ለሜቻ ግርማ፣ ጌትነት ዋለና ሳሙኤል ፍሬው በ3000 ሺህ መሰናክል ፍጻሜ ውድድር ላይ ኢትዮጵያን ወክለው ነበር። በውድድሩ ለሜቻ ሜዳሊያ እንደሚያገኝ ከፍተኛ እምነት ነበር። እሱ ሲጎዳ እስከመጨረሻው የሮጡት አትሌት ሳሙኤል ፍሬው ስድስተኛ፣ አትሌት ጌትነት ዋለ ዘጠነኛ ደረጃን በመያዝ ውድድራቸውን አጠናቅቀዋል።
በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ታሪክ ከፍተኛ የሚዲያና የማህበራዊ አምድ ውርጅብኝ የደረሰበት የኢትዮጵያ ልዑክ ለሜቻ ላይ ከደርሰው ጉዳት ጋር ተዳምሮ ጫና እንደበዛባቸው ለማወቅ ተችሏል።
ስማቸውን እንዳንተቅስ የጠየቁን አንድ አስልጣኝ “አገር ቤት ስገባ ሁሉንም ጉዳይ በግልጽ እናገራለሁ። በዚህ ደረጃ በአገሩ ሚዲያ ውድድር ላይ እያለ ዘመቻ የተከፈተበት ቡድንም ሆነ አገር ዓለም ላይ ታይቶ አያውቅም። ውድድሩን እስኪጨርሱ ማበረታታና ማገዝ ሲገባ በተቃራኒው ነው እየሆነ ያለው። ችግር ቢኖርም በሚወራው ደረጃ አይመስለኝም። የተለያየ ፍላጎት ያላቸው ሃይሎች ፍጥጫ ነገሩን ሁሉ አበላሽቶታል። እዚህ ላይ የተሳተፉ ሁሉ ሊጠየቁ ይገባል። እኔም ጭምር” ሲሉ እግረመንገዳቸውን አስተያየት ሰጥተዋል። አያይዘውም ከተራ ወገንተኝነትና የግለሰብ ደጋፊ ከመሆን በዘለለ በማስተዋል ለአትሌቲክሱ የሚበጀውን ስራ መስራቱ እንደሚጠቅምም አስታውቀዋል።
አትሌት ለሜቻ ግርማ! በመልካም ጤና ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል
የ3,000 ሜትር መሰናክል ሪከርድ ባለቤቱ ለሜቻ ግርማ ትናንት ምሽት በውድድሩ ወቅት ሲዘል ባጋጠመው ጉዳት ምክንያት በፍጥነት ወደ ሆስፒታል እንደተወሰደ እና አሁን በመልካም ጤና ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል።
አትሌት ለሜቻ ግርማ ትናንት ምሽት ባጋጠመው ከባድ ጉዳት ምክንያት ራሱን ስቶ ወደ ሆስፒታል የተወሰደ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ሙሉ በሙሉ የነቃ ሲሆን በተደረገለት የሲቲ ስካንና የኤም አር አይ ምርመራ ምንም አይነት ጉዳት እንዳልተገኘበት ኦሊምፒክ ኮሚቴው አስታውቋል።
የፓሪስ 2024 ኦሎምፒክ ቃል አቀባይ በበኩላቸው ፤ ” አትሌት ለሜቻ ግርማ አስፈላጊ የሆነ አፋጣኝ ህክምና ተደርጎለታል ” ብለዋል።