‹‹በከተማዋ 11 ቦታዎች ላይ የመሬት መንሸራተት አደጋ አጋጥሟል›› የደሴ ከተማ አስተዳደር
በደሴ ከተማ በ11 የተለያዩ አካባቢዎች በደረሰው የመሬት መንሸራተት አደጋ ከ300 በላይ የሚሆኑ የከተማዋ ነዋሪዎች መፈናቀላቸው ተነግሯል፡፡
አደጋው ፊትበር፣ዶሮ ተራ፣ቄራን ጨምሮ 11 በሚሆኑ የከተማዋ አካባቢዎች የተከሰተ መሆኑን የገለጹት በደሴ ከተማ አስተዳደሩ የአራዳ ክ/ከተማ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ግርማ ከተማዋ ላይ በቀጣይ መሰል አደጋ ይከሰታል የሚል ስጋት እንዳለ ጠቁመዋል፡፡
ከአደጋው ጋር ተያይዞ መኖሪያ ቤቶች በየቀኑ እየፈረሱ ነው የተፈናቃዮች ቁጥርም በከፍተኛ ደረጃ እያሻቀበ ነው ያሉት ስራ አስፈጻሚው እየተደረገ ያለው ድጋፍ ግን አጥጋቢ ነው የሚባል እንዳልሆነ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል፡፡
የደሴ ከተማን ከኮምቦልቻና ከአዲስ አበባ የሚያገናኘው ዋና አውራ ጎዳና በአደጋው ምክንያት አገልግሎት መስጠት ማቆሙ ፣ እርዳታ በተፈለገው ልክ ወደ ከተማዋ እንዳይገባ እንዳደረገውም አንስተዋል፡፡
አሁን ላይ የተፈናቀሉ ዜጎችም በትምህርት ቤቶች ውስጥ በጊዚያዊነት ተጠልለው እነደሚገኙ የገለጹት ሃላፊው መጪው የትምህርት ዘመን ከመቃረቡ ጋር ተያይዞ ነዋሪዎችን በዘላቂነት ለማቋቋም ሁሉም ዜጋ ለከተማዋ ድጋፍ እንዲያደርግ ትብብር ጠይቀዋል፡፡
ከሁለት ሳምንት በፊት የብሄራዊ ሜትሮሎጂ ኢንስቲትዩት ባወጣው የቅድመ ስጋት ሪፖርት በመሬት መንሸራተት አደጋ ተጋላጭ ናቸው ካላቸው የአገሪቱ አካባቢዎች ውስጥ ደሴ ከተማ አንዷ እንደነበረች አይዘነጋም፡፡
አዲስ ማለዳ