የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚንስቴር በመሠረታዊ ፍጆታዎች ላይ ያለአግባብ ዋጋ የጨመሩ 542 የንግድ ድርጅቶች ታሽገው ንግድ ፍቃዳቸው እንደታገደና 324ቱ ደግሞ ማሰጠንቀቂያ እንደተሰጣቸው አስታውቋል።
ሚኒስቴሩ ትናንት በመሠረታዊ የምግብ ሸቀጦች ላይ አላግባብ የዋጋ ጭማሬ ያደረጉ የንግድ ተቋማት ላይ እርምጃ መውሰዱን አመላክቷል፡፡
እንዲሁም ጉምሩክ ኮሚሽን ይዟቸው የነበሩ የዘይትና ስኳር ምርቶችም፣ ከዛሬ ጀምሮ ወደ ገበያ እንደሚገቡ ሚንስቴሩ ጠቁሟል።
ሸቀጦቹ የተያዙት፣ ፍራንኮ ቫሎታ ተፈቅዶላቸው ዘይትና ስኳር በሚያስመጡ ነጋዴዎችና በጉሙሩክ ኮሚሸን መካከል ከታክስ ክፍያ ጋር የተያያዘ ችግር በመፍጠሩ ነበር።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ያስታወቀውን የውጭ ምንዛሬ የዋጋ ማሻሻያን ተከትሎ በተለያዩ ቦታዎች እና ሱቆች በእቃዎች ላይ የዋጋ ጭማሬ ታይቷል፡፡
ይህን ጉዳይ ተከትሎ በመርካቶ እንዲሁም በተለያዩ አካባቢዎች አዲስ ማለዳ ባደረገችው ቅኝት በተለያዩ ምግብ ነክ እና ምግብ ነክ ያልሆኑ ሸቀጦች ላይ የዋጋ ጭማሬ እንዳለ የተመለከተች ሲሆን በመርካቶ አካባቢ አንዳንድ ነጋዴዎች ሱቆቻቸውን እንደዘጉ እንዲሁም የተለያዩ እቃዎችን በማሸሽ እና የለም በማለት የዋጋ ጭማሬውን እያባባሱት እንደሚገኙ አዲስ ማለዳ መዘገቧ ይታወሳል፡፡
Via Addis_Reporter