ሕግና ሥርዓትን በማበጀት ረገድ ሀገራችን ኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ ታሪክ እንዳላት መዛግብት ያስረዳሉ፡፡ ሀገሪቱን የመሩ ሥርዓተ መንግሥታት እንደየዘመናቸው የየራሳቸው መተዳደሪያ ሕግ ነበራቸው፡፡ ሕዝቡም አምላኩን የሚፈራ ለሀገሩም ሕግ የተገዛ እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ያወሳሉ፡፡
አባቶቻችን የሚታወቁበት የማኅበረሰብን ወግና ደንብ አክባሪነት፤ መንግሥታት ላወጡት ሕግ ተገዢነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሸረሸረ መጥቷል፡፡ ለዚህም በየጊዜው የምንሰማቸው ወንጀሎች፣ እያወቅን የምንጥሳቸው በርካታ ደንቦች ምስክሮች ናቸው፡፡
የትራፊክ ሕግን እንዲከበር፣ ጤናማ የንግድ ሥርዓት እንዲፈጠር፣ አካባቢን ብሎም ከተሞችን ከቆሻሻ የጸዱ ለማድረግ፣ የራሳችን ሀብት የሆኑ መሠረተ ልማቶችን ከጉዳት ለመታደግ ሕግ ማውጣቱ ብቻ በቂ አልሆነም፡፡ እንደ ማኅበረሰብ ሕግ ቢከበር ጥቅሙ ለእኔው የሚል አመለካከት ብዙም ሰርጾ አይታይም፡፡
ሕግ ለማክበር በመጠኑም ቢሆን የምንነሳው ሕግ የማስከበሩ ሥራ ወደ ቅጣት ሥርዓት ሲገባ እንደሆነ የሕግ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ ሰዎች አንድ ድርጊት በሕግ ያስጠይቃል ወይ ከማለት ይልቅ ሕግ አስከባሪ አይቶናል ወይ ለሚለው ትኩረት የሚሰጡ እየሆኑ እንደመጡም ትዝብታቸውን ያጋራሉ።
አቶ አምደሚካዔል አድማሱ በሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ከፍተኛ የሕገ መንግሥት ተመራማሪ ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት፣ በሀገራችን በየጊዜው ጥሩ የሚባል ይዘትና አስፈላጊነት ያላቸው ሕጎች ይወጣሉ። የወጡ ሕጎችን በማክበርና ለሕግ በመገዛት በኩል ግን፣ እንደ ሀገር ጉልህ ችግር አለ። ይህ ደግሞ፣ በሀገር እድገት፣ ሠላምና የፖለቲካ ሥርዓት ላይ በርካታ ችግሮችን ሲፈጥር ይስተዋላል።
የሕገ መንግሥት ተመራማሪው እንደሚሉት፤ እንደ ማኅበረሰብ በሕግ ከመገዛት ጋር በተያያዘ ላሉ ችግሮች ዋና ከሚባሉ ጉዳዮች ቀዳሚው፤ ሕግ ለማውጣት የሚደረገውን ጥረት ያህል ሕግን ለማስፈጸም ያለው ትጋት እምብዛም መሆኑ ነው።
ሌላኛው መሠረታዊ ሆኖ ሊገለጽ የሚችለው ደግሞ፣ የማኅበረሰቡ ንቃተ ህሊና አለማደግ ነው በማለት ይገልጻሉ። አንድ ሕግ ከወጣ በኋላ በማኅበረሰቡ ዘንድ እንዲሰርጽ ለማድረግ የሚሠሩ ሥራዎች ጠንካራ አለመሆናቸው ህብረተሰቡ ሕግን አውቆ እንዳይገዛ አንዱ መንስዔ እንደሆነም ጠቅሰዋል።
በብዙ ማኅበረሰብ ዘንድ ሕግ ወጣልን ሳይሆን መጣብን የሚል አስተሳሰብ መኖሩንም የሚጠቅሱት አቶ አምደሚካዔል፤ አንድ ሕግ ሲወጣ በብዙ መልኩ ተፈትሾና ተገምግሞ አስፈላጊነቱ ታምኖበት እንጂ ማንንም ለመጉዳት አይወጣም ሲሉ ያስገነዝባሉ።
ፍርድ ቤቶችን ጨምሮ ሕግ ማስከበር ላይ ያሉ አካላት በአግባቡና በታማኝነት ኃላፊነታቸውን የማይወጡ ከሆነና ብልሹ አሠራሮች ከተበራከቱ ሕዝብ በሕግ ከማመን ይልቅ ሕገወጥነትን አማራጩ አድርጎ የሚወስድ እንደሚሆንም ያብራራሉ።
ለሕግ የተገዛ ማህበረሰብን ለመገንባት በሕግ አስከባሪ አካላት ዘንድ የሚስተዋሉ ብልሹ አሠራሮችን ማስተካከል እንደሚገባም ነው የሚመክሩት።
ሕግን አክብሮ ለሕግ ተገዝቶ መኖር ዘመናዊነት ነው የሚሉት አቶ አምደሚካዔል፤ በዚህ ረገድ በአህጉረ አፍሪካ ደቡብ አፍሪካ፣ ጋና፣ ጥሩ ተሞክሮ ያላቸው ሀገራት ሲሆኑ፣ አውሮፓና ሰሜን አሜሪካ አካባቢ ደግሞ ጠንካራ የሕግ ሥርዓት በመዘርጋቱ ሰው በጤነኛው አዕምሮ ሕግ ይጥሳል ተብሎ የማይታሰብበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል ብለዋል።
ይህንን ዘመናዊ አመለካከት ወደ ሀገራችን ለማምጣት ህጻናት ከልጅነታቸው ጀምሮ የሥነ ምግባር ትምህርት ሲማሩ ለሕግ መገዛት ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ማሳየት ይገባል ይላሉ።
ዜጎች ከቅጣት በፊት ወደውና ፈቅደው ለሕግ የሚገዙበትን አመለካከት በመገንባት ረገድ ሕግ አስፈጻሚው በተለያዩ የሕዝብ መገናኛ መንገዶች ሕግ የማስረጽ ሥራ ሊሠራ እንደሚገባ ያነሱት የሕገ መንግሥት ተመራማሪው፤ ሕገ ወጥነት ላይ ጠንካራ ርምጃ መውሰድና የሚወሰዱ ርምጃዎችን አስመልክቶ ሕዝቡ በቂ እውቀትና መረጃ እንዲኖረው ማድረግ ላይ ጠንካራ ሥራ መሥራት እንደሚገባ አስምረውበታል።
በሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ ከፍተኛ የሕገ መንግሥት ተመራማሪ አቶ አቤኔዘር ጥሩአየሁ በበኩላቸው፣ ሕግን ከማክበር ጋር ተያይዞ የሚስተዋለው ችግር ሕግን አለማወቅ ሳይሆን “ሕግን እያወቁ መጣስ ነው” ይላሉ።
ለዚህም ከትራፊክ እንቅስቃሴ ጋር የተያያዙ የሕግ ጥሰቶችን አብነት አድርጎ በመጥቀስ፤ በህብረተሰቡ ዘንድ ሕግ ማክበርም ሆነ መብቱን በሕግ ማስከበር ላይ ከፍተኛ የግንዛቤ ችግር መኖሩን ያነሳሉ።
ሌላው ያነጋገርነው በግል የሕግ ማማከር አገልግሎት የሚሰጡት አቶ ኢዘዲን ፈድሉ፣ ሰዎች በራሳቸው ተነሳሽነት ሕግን የማያከብሩ የሚሆኑበት አንደኛው ምክንያት የማኅበራዊ ውል መላላት ነው በማለት ሃሳባቸውን ይገልጻሉ።
የሀገረ መንግሥት ግንባታ አለመጠናቀቅም እንዲሁ ዜጎች ወደውና ፈቅደው ለሕግ እንዳይገዙ ምክንያት እንደሚሆንም ይጠቅሳሉ።
ግለሰቦች ከሕግ በታች የሆኑባት፣ ሕግ የሚከበርባት ሀገርን ለመመስረት በማኅበረሰብ መካከል ጠንካራ ውል ማበጀት ያሻል ብለውም፤ ይህም የመንግሥት፣ የምሁራን፣ የእምነት አባቶች ብሎም የመላው ህብረተሰብ ኃላፊነት እንደሆነ ይናገራሉ።
ከመንግሥት ሥርዓት ጋር በተያያዘ ዜጎች ሕግ አውጪው የሚያወጣቸውን ሕጎች በራሳቸው ተነሳሽነት የሚያከብሩ እንዲሆኑ፤ ሕዝብ አመኔታ የሚጥልበት እና ሁሉም ወጥ በሆነ መልኩ የሚተዳደርበት ሥርዓትን መቅረጽ ያስፈልጋል ሲሉ ያስረዳሉ።
ዜጎች ሕግን አክብረውና ተከባብረው የሚኖሩ ከመሆናቸው የተነሳ የፖሊስ ኃይል የሌለባቸው አንዳንድ ስካንዲኒቪያን ሀገራት መኖራቸውን የሚያነሱት አቶ ኢዘዲን፤ በእነዚህ ሀገራት ሕግ አስከባሪ ጣልቃ የሚገባው ከአቅም በላይ የሆኑ ጉዳዮች ሲፈጠሩ ብቻ መሆኑን በማሳያነት ጠቅሰዋል።
ዮርዳኖስ ፍቅሩ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 26 /2016 ዓ.ም