አማራ ክልል ቁልቁል እየተምዘገዘገ ይገኛል። በቅጡ ያልተገመገመ፣ በቂ ዝግጅት ያልተደረገበት፣ ድንገቴ እልህ አመጣሽ ትግል ህዝባችንን ለኋላ ቀርነት፣ ለሞት፣ ለስደት፣ ለጉስቁልና፣ ለእርስ በርስ መገዳደል ዳርጎት ይገኛል። እናቶች ምጥ ተይዘው በአምቡላንስ ሆስፒታል የሚደርሱበት ታሪክ እንደ ሰማይ የራቀ ሆኗል። ጤና ጣቢያዎች የወፍ ማደሪያ ከሆኑ ሰነባብቷል። አቅም ያላቸው ሰዎች ክልሉን ለቀው ተሰደዋል።
አንድ የወረዳ አስተዳዳሪ እንደነገረኝ ከሆነ በወረዳው ካሉ 133 ትምህርት ቤቶች አንዱም ትምህርት አልሰጠም። 4 ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የዩንቨርሲቲ መግቢያ ፈተና አላስፈተኑም። አንድ የዞን አመራር በበኩሉ በዞኑ ውስጥ 5 አምቡላንሶች ብቻ ናቸው የቀሩት ሲል ነግሮኛል። ሌሎቹ የሉም። የት ሄዱ የሚለውን አንባቢው በራሱ ለመመለስ ብዙም ከባድ አይሆንበትም። ይህንን የአንድ ወረዳ እና የአንድ ዞን እንደ ማሳያ ብንወስደው እና በ14 ዞኖች እና በ267 ወረዳዎች አብዝቶ የጥፋቱን ጥልቀት ማግኘት ይቻላል።
በተለያዩ የግምገማ ወቅቶች የፌድራል ተቋማትን ሪፖርት የመከታተል እድል አለኝ። ይህንን ተከትሎ በሁሉም መለኪያ አማራ ክልል ቁልቁል እየተምዘገዘገ ይገኛል። የመብራት ኃይል የኃይል ተሸካሚ ምሰሶዎች ውድመት በአማራ ክልል 158 ሲሆን በኦሮሚያ ክልል 56፣ በቤንሻንጉልጉሙዝ 8 እያለ በአጠቃላይ በሃገሪቱ ከወደመው ጋር ሲነጻጸር የአማራ ክልሉ ከ60% በላይ ይሸፍናል። ልብ አድርጉ ባለፉት 27 የወያኔ አመታት አንድም ሰብ-ስቴሽን ባልተገነባበት እና ጨለማ በወረሰው ክልል ነው ይኸ ሁሉ የመብራት ኃይል ውድመት ያጋጠመው። የፌድራል ተቋማት ዓመታዊ እቅዳቸውን ያላሳኩበት ምክንያት ተብሎ ሲጠቀስ ዋነኛል በአማራ ክልል ያጋጠመው ግጭት ነው። ከዚህ ሁሉ ተነስቶ ግጭቱ የዛሬውን ብቻ ሳይሆን የነገውን ትውልድ ሁሉ ዋጋ የሚያስከፍል ለመሆኑ ሰከን ብሎ የሚያስብ ሰው አያጣውም።
አቶ ገዱ ባልፈው ፅፎ ባሰራጨው ረጅም ፅሁፍ ውስጥ በአማራ ክልል እየተደረገ ባለው ግጭት እንደ ስኬት የቆጠረው “አማራ ክልልን የማይገዛ አድርገነዋል” በሚል ነበር። አቶ ገዱን የሚያክል የፖለቲካ ስብዕና እና ክልሉን አብጠርጥሮ የሚያውቅ ሰው በኩራት የማይገዛ ክልል ፈጥረናል ሲል የችግሩ ጥልቀት ምን ያክል ከባድ እንደሆነ ለመረዳት ፍንጭ ይሰጣል። ለመንግስት የማይገዛ ህዝብ ከፈጠርክ በኋላ ነገ ማን ሊገዛው እንደሚችል የሚያውቁት አቶ ገዱ እና መሰሎቹ ብቻ ናቸው። “መንግስት የቆመጠው ቆማጣ አይባልም” እያለ ለህግና ስርዓት እየተገዛ የኖረን ትልቅ ህዝብ ስርዓቱን አፈራርሶ የማይገዛ እና እንደ ድንጋይ ዘመን በጉልበት ብቻ የሚተዳደር ወደሆነ ህዝብ ማውረድ ኪሳራው ምን ያክል እንደሆነ ለመረዳት የፖለቲካ ሳይንስ ሊቅ መሆንን አይጠይቅም።
አንባቢ የተሳሳት ግምት እንዳይወስድ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባኛል። የአማራ ክልል ብሎም የአማራ ህዝብ ችግር የለበትም፣ መንግስት እንዲመልስለት የሚፈልጋቸው ጉዳዮች የሉትም እያልኩኝ አይደለም። የአማራ ህዝብ ጥያቄዎች ተብለው በሁሉም ሰው ዘንድ እንደ አስሩ ትዕዛዛት የሚነበነቡትን ጉዳዮች እንዴት ሊመለሱ እንደሚችሉ ሁሉ አበጥረን እናውቃቸዋለን። ጥያቄዎቹንም እንደዛሬው አልፎ ሂያጁ ሁሉ የፖለቲካ ተንታኝ ባልነበረበት ወቅት እኔ እና ጓደኞቸ የቀረፅናቸው ናቸው ብየ በድፍረት መናገር እችላለሁ። የአማራ ህዝብ መሰረታዊ ጥያቄዎች መፈታት እና መመለስ አለባቸው ብለን ብዙ ደክመናል አሁንም እየጣርን እንገኛለን። አሁን አማራ ክልል እየሆነ ባለው መንገድ ግን የአማራ ህዝብ ጥያቄዎች ሊመለሱ አይችሉም የሚል ፅኑ እምነት አለን። ይኸ መንገድ ሌላ ጥያቄ የሚፈጥር እንጅ ጥያቄን የሚያስመልስ አይደለም ብለን አበክረን ተከራክረናል። አሁንም ቢሆን ማንም ሰው በዚህ ጉዳይ ላይ ሊከራከረኝ ቢፈልግ በማንኛውም መንገድ ለመከራከር እችላለሁ።
ይኸ ሁሉ ሲሆን ግፋ በለው የሚል እንጅ “ኧረ ተው ይኸ ነገር መፍትሄ ይበጅለት” የሚል አንድም እንኳ የለም። አሁን አሁን ችግሩ ከመንግስት ጋር ከመግጠም አልፎ የእርስ በርስ እየሆነ ወደ አደገኛ ደረጃ እየተሸጋገረ ይገኛል። “ነጻነት” እናመጣለን ብለው ዱር ቤቴ ያሉ ሰዎች እርስ በርስ የሚፈላለጉ ባላንጣዎች ወደመሆን ተሸጋግረዋል። በዚህም ህዝባችን አደገኛ ዋጋ እየከፈለ ይገኛል። ወንድሞቻችን አላስፈላጊ መስዋዕትነት እየከፈሉ ነው። “የገደለው ባልሽ የሞተው ወንድምሽ” አይነቱ ተረት እውን ሆኗል።
በ1970’ቹ እና 1980’ዎቹ አከባቢ የቀዝቃዛው ጦርነትን ማብቃት ተከትሎ የሁለቱ ዓለም ፍትጊያ ወደ ምዕራብ መራሽ ፖለቲካል ኦርደር ስለተለወጠ ብዙ አማፂያን የቤተ መንግስትን ደጅ ሊረግጡ ችለው ነበር። 16 ዓመታትን በጫካ ቆይቶ መቀሌን እንኳን መቆጣጠር ያልቻለው ወያኔ በዚህ አጋጣሚ የአሜሪካንን ጡጦ እየጠባ በአንድ ዓመት ውስጥ ከትግራይ በርሮ አራት ኪሎ ለመግባት ችሎ ነበር። “የፋሲካ እለት የገባች ባሪያ ሁልጊዜ ፋሲካ ይመስላታል” እንዲሉ ይህን ሃቅ ያላገናዘበው ወያኔ የሰሜን እዝን በውድቅት ሌሊት አጥቅቶ ወደ አራት ኪሎ ለመገስገስ ቢሞክርም እንደ ድሮው አልተሳካለትም። የኢትዮጵያ ህዝብ ሆ ብሎ እንደ አዋሽ ወንዝ ሊያሰጥመው ችሏል። ይህም የትጥቅ ትግል እንደ ቀስቃዛው ጦርነት ወቅት ቀላል አለመሆኑን በሚገባ አስረጅ ሆኖ አልፏል።
አሁን ላይ የዓለም የፖለቲካ ሁናቴ ተቀይሯል። በተራዘመ ጦርነት ማሸነፍ እንደማይቻል ብዙ አማፂያን ምስክር ናቸው። የተራዘመ ጦርነት መንግስት ክፍተቱን እንዲለይና እንዲዘጋጅ የሚያደርግ ይልቁንስ ህዝብ እና ሐገርን ወደ ፍርስራሽነት የሚለውጥ ለመሆኑ ከአረብ አብዮት በኋላ የተከናወኑ ክስትቶች ማሳያ ናቸው። ይልቁንስ ጥያቄዎችን አደራጅቶ በአጭር ቀናት ውስጥ መንግስትን መጠምዘዝ እንደሚቻል ከአረቡ አለም አብዮት በተጨማሪ የራሳችን የቅርብ ጊዜ ተሞክሮ አስረጅ ነው። ከ2008 እስከ 2010 ድረስ የተደረገው የህዝብ ትግል ብዙ ዋጋ ያልተከፈለበት፣ መሰረተ ልማቶች ያልወደሙበት፣ ብዙ ጠባሳ ያላሳረፈ ስኬታማ ትግል ነበር። ይህንን ተሞክሮ በማስፋት እና በማሳደግ መንግስት ጥያቄዎችን እንዲመልስ ማስገደድ እየተቻለ ለመንግስት አቅም በሚፈጥር መልኩ እና በሚቀለው የትግል ስልት መታገል ትርፉ የህዝብ ኪሳራ ብቻ ነው።
ከዚህ ሁሉ በመነሳት የመፍትሄ ሃሳብ ነው ያልኩትን ጠቁሜ ፅሁፌን ልዝጋ።
እስካሁን የተደረገው ትግል ያመጣውን ትርፍ እና ኪሳራ መገምገም ይገባል። ትርፍ እና ኪሳራው ተሰልቶ ንግግር መጀመር አለበት። በመንግስትም ሆነ በአማፂ ኃይሎች በኩል ህዝብን መሰረት ያደረገ ሆደ ሰፊነት የተገባ ነው። “የይዋጣልን” ፖለቲካ መጨረሻው በዝሆኖች ፀብ አሳሩን የሚበላው ሳሩ እንደሆነ ሁሉ ህዝብን ያልተፈለገ ዋጋ ማስከፈል ነው። ሰከን ብሎ ራስን ለንግግር ክፍት ማድረግ ይገባል። በውጭም ሆነ በውስጥ ያለን ጉዳዩ ይመለከተናል የምንል ወገኞች ከዝምታ ወጥተን በቃ ማለት ያስፈልገናል። በዝምታ ውስጥ አንድ ዓመት ዘልቀናል። ከአሁን በኋላ በዚህ መንገድ ከቀጠልን ህዝባችን እንደ ቅጠል ይረግፋል። ዝምታው መሰበር፣ ንግግር መጀመር አለበት።
ጋሻው መርሻ