“ከፀረ-ሰላም ኃይሎች ተልዕኮ ተቀብለው የተንቀሳቀሱ በመሆናቸው በሽብር ወንጀልም ተጠርጥረዋል” ሲል ፖሊስ ክስ እንደሚመሰረት ይፋ ባደረገበት መግለጫው በአዲስ አበባ አውሮፕላን ማረፊያ አውሮፕላን ውስጥ ሁከት የፈጠሩት ተከሳሾች ፍርድ ቤት የሚቀርቡት ነኞ ማለዳ ነው።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሲቪል አቪዬሽን ሕግና አሠራር ጥሰዋል ባላቸው ስድስት ተጠርጣሪዎች ላይ የሽብር ወንጀል ምርመራ መጀመሩን ሲያስታውቅ እንዳለው የህግ ጥሰትና በሽብር ወነጀል የሚያስጠረጥር መረጃ አለው።
ሰሞኑን ከአዲስ አበባ መቀሌ ለጉዞ በተዘጋጀ አውሮፕላን ውስጥ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሲቪል አቪዬሽን ሕግና አሠራር በመጣስ ግርግርና ወከባ ፈጥረዋል ሲል የሽብር ወንጀል ምርመራ መጀመሩን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አስታውቋል። ፍርድ ቤት የሚያቀርባቸውን ስም ጠቅሶ ይፋ አድርጓል።
በዚሁ መሰረት 1. ዮሀንስ ዳንኤል በርሄ፣ 2. አማኑኤል መውጫ አብርሃ፣ 3. ናትናኤል ወንድወሰን ሹሜ፣ 4. ኤልያስ ድሪባ በዳኔ፣ 5. ይዲድያ ነጻነት አበበ እና 6. እሌኒ ክንፈ ተክለአብ ፍርድ ቤት የሚቀርቡ መሆናቸው ተመልክቷል።
በተጠርጣሪዎቹ ላይ ክስ የተመሠረተው አሁን ላይ በሀገራችን ካለው የክረምት ወቅት ጋር ተያይዞ በተፈጠረው የአየር መዛባት ምክንያት አውሮፕላኑ መብረር አይችልም ያሉ የበረራ ባለሙያዎችን በማስገደድ በረራውን ለማስቀጠል በፈጠሩት አምባጓሮና ግርግር ወንጀል ተጠርጥረው እንደሆነ የወንጀል ምርመራ ቡድኑ ከሰጠው ገለጻ ለመረዳት ተችሏል።
የፖሊስ የምርመራ ቡድኑ ተጠርጣሪዎቹ ላይ ከተመሠረተባቸው የወንጀል ክስ በተጨማሪ ከፀረ-ሰላም ኃይሎች ተልዕኮ ተቀብለው የተንቀሳቀሱ በመሆናቸው በሽብር ወንጀልም መጠርጠራቸውን ጨምሮ ገልጿል።ይሁን እንጂ “ጸረ ሰላም የተባሉትን” ቡድኖች፣ አገር ወይም ድርጅቶች ለጊዜው በስም አልጠቀሰም።
ኤርትራና ሶማሊያ በተከታታይ የኢትዮጵያ አየር መነገድን ስም ለማቆሸሽ ያልተገባና መረጃ አልባ አቤቱታ ሲያሰራጩ አየር መነገዱ ድርጊቱን በማስተባበል “እውነት ” ያለውን መረጃ ሲያቀርብ እንደነበር አይዘነጋም። በረባና ባልረባ ጉዳይ የኢትዮጵያ የባህር በሯ ጭምር የሆነውን ይህን ግዙፍና ገናና ተቋም “ኢትዮጵያዊያን እንደ አይናችሁ ብሌን ጠብቁት” ሲሉ በትናንትናው ዕለት አየር መንገዱ መገለጫ ከመስተቱ በፊት የህግ ባለሙያዎች ድርጊቱ እስከ አስራ አምስት ዓመት የሚያስቀጣ መሆኑን ጠቅሰው ምክር ሲለገሱ ነበር።
በርካታ የተቆጡ ዜጎችም ተገባሩን “ድንቁርና” በማለት አውግዘው ተጠርጣሪዎቹ በራሳቸው ላይ ማስረጃ የሚሆን የወንጀል ማስረጃ ማሰራጨታቸውን ጠቅሰው መንግስት ሊከስና ለሌሎች ትምህርት የሚሰጥ እርምጃ እንዲወስድ ከወቀሳ ጭምር ሲያቀርቡ ውለው አምሽተዋል።
“አንወርድም፣ ይከስከስ” በሚል በህብረት ጩኸት የሚሰማበት ቪዲዮ ይፋ ከሆነ በሁዋላ “ይህ መንግስት ቸል ያለው የማህበራዊ ሚዲያና አክቲቪስት ነን ባዮች መረን የወጣ ተግባር ማሳያና መገለጫ ነው “ሲሉ በነጻ አሳብ ስም በኢትዮጵያ ሚዲያዎችና ማህበራዊ አውታሮች መንግስት እሹሩሩ ብሎ የሚነከባከበው የጋግጠወጦች ተግባር ውሎ አድሮ ከዚህ በላይ ጉዳት እነድሚያስከትል የቆየ ትዝብታቸውን አጣቅሰው የጻፉም ነበሩ።
ዛሬ ማለዳ ላይ ፖሊስ “በወቅቱ የአየር መንገዱ የደህንነት ኃይሎችና የበረራ ባለሙያዎች በትዕግስት ሁኔታውን ለማርገብ ቢማጸኗቸውም፣ ድብቅ አጀንዳቸውን እያራመዱ አሻፈረን ማለታቸውንም በወንጀል ምርመራ መዝገቡ ተካቷል” ብሏል።
በቁጥጥር ሥር የዋሉት ተጠርጣሪዎች የሀገር ውስጥ እና የዓለም አቀፍ የበረራ ሕግና አሰራርን በመጣሳቸው እንዲሁም በተጠረጠሩበት የሽብር ወንጀል በነገው ዕለት ነሐሴ 20 ቀን 2016 ዓ.ም ፍርድ ቤት ፖሊስ እንደሚያቀርባቸው ፖሊስ ይፋ ያደረገው።
የህግ ባለሙያዎች ወቀሳ ብቻ ሳይሆን ችግር ካለ፣ ካሳ የሚያስጠይቅ አጋጣሚ ከተፈጠረ የሚጠይቅበት አግባብ መኖሩን አመልክተው ምክር መለገሳቸውን ጠቅሰን መዘገባችን ይታወሳል።
አየር መንገዱ ከ40 በላይ ዓለም ዓቀፍ በረራዎችን በአየር ጸባይ ችግር አዲስ አበባ ማስተናገድ ሳይችል መቅረቱ በተደጋጋሚ ይፋ ማድረጉ እየታወቀ፣ አጋጣሚውን የተቋሙን ስም ለማጠልሸት ሌት ተቀን የሚደክሙ ወደ እንግሊዘኛ በመቀየር ጉዳዩን የዓላማቸው ማስፈጸሚያ ወይም ለቀጠራቸው ወገን ታማኝ መሆናቸውን ማሳያ አድርገው ተጠቅመውበታል።
ይህንኑ የማህበራዊ ሚዲያ ገበያ ተከትሎ አጋሰስ ላይ ተቀምተው፣ አውቶቡስ ላይ ሆነው ዜጎች የቀልድ ፊልም በመስራት ድርጊቱን መሳቂያ ሲያደርጉትም ታይቷል። በተለይ አንድ አጋሰስ ልካይ የተሳፈረ ወጣት የጋሪው ባለቤት ” ውረድ” ሲለው “አንዴት ተሳፍሬያለሁ አልወርድም” እያለ በአውሮፕላን ውስጥ የተፈጠረውን ድርጊት ሲይበሻቅጥ የሚያሳየው ቪዲዮ በጥቂት ሰዓታት ውስጥ በረክቶች የተጋሩት ሆኗል።