ኢትዮጵያ በሰላሟም ሆነ በችግሯ ጊዜ ከጎኗ የሚቆም ወዳጅ አጥታ ባታውቅም በተቃራኒ ሰላሟን ለማደፍረስ እሳት የሚተፉ፣ ችግሮች ሲፈጠሩ ከዳር ቆመው የሚያራግቡ፣ ዳግመኛ እንዳትነሳም በተቻላቸው ሁሉ የሚፍጨረጨሩ የቅርብም ሆነ የሩቅ ባላንጣዎች ያጋጥሟታል፡፡ ክንዳቸውን ያፈረጠሙ ባዕዳን በተለያዩ ዘመናት ከተፈጥሮ ሀብቷ ለመቀራመት፤ በሕዝቦቿ መካከል ልዩነትን ለመዝራት ሙከራ አድርገዋል፡፡ ይህ በተለያየ መልኩ ሀገራችን ላይ የሚያደርሱት ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና ዛሬም እንደቀጠለ አለ፡፡
ሀገራችን ላይ እኩይ ዓላማን ያነገቡ አካላት እንደ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና መሰል ጠንካራ ተቋማቶቻችንን ኢላማ ያደረጉ የሳይበር ጥቃት ሙከራዎችና ስም የማጥፋት ዘመቻዎችን እያካሄዱ ይገኛሉ፡፡
ለመሆኑ እነዚህ ተቋማት ኢላማ የመሆናቸው መንስዔ ምን ይሆን? ለጥቃት የሚተጉ አካላትስ እነማን ናቸው? ለምንስ ተቋማቱ የጥቃት ኢላማ ሆኑ? ተቋሞቻችንን ከጉዳት ለመታደግስ ምን ይጠበቅብናል?
የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሁሩ ደጉ አስረስ (ዶ/ር) እንዳብራሩት፣ ተቋማቱ ኢላማ የመደረጋቸው ቀዳሚ መንስዔ ከብሔራዊ ጥቅም ጋር የተቆራኙና ከፍተኛ አትራፊ ድርጅቶች መሆናቸው ነው። ተቋማቱ ከፍተኛ ገቢን የሚያስገኙ በሀገር ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ውስጥም ሰፊ ሚና አላቸው፡፡
ከዚህ በመነሳት ተፎካካሪ ሀገራትና ሌሎችም እኩይ አላማ ያላቸው ኃይሎች የተቋማቱን ገፅታ ለማበላሸት፣ ሀገራችን ከተቋማቱ የምታገኘውን ገቢ ለማሳጣትና ብሔራዊ ጥቅሟን ለመጉዳት ሲሉ እነዚህን ተቋማት የስም ማጥፋት ዘመቻ ኢላማ ያደርጋሉ ይላሉ፡፡
በቴክኖሎጂ በመታገዝ ለጥቃት የሚደረጉ ሙከራዎች ተቋማቱ የመረጃ ሥርዓታቸው እንዲዛባና ይህንን ለመቆጣጠር ጥረት በሚያደርጉበት ጊዜ ሊቆጣጠሩት የማይችሉት አይነት አደጋ እንዲገጥማቸው የማድረግ ሙከራዎችም ይኖራሉ፡፡
ከተፎካካሪ ሀገራት በተለየ ሁኔታ ደግሞ ለስርቆት የተደራጁ ኃይሎችም እነዚህን ተቋማት ኢላማ ያደረገ ስርቆት ለመፈጸም ጥረት የሚያደርጉበት ሁኔታ አለ። ጭምር በዚህ የስርቆት ወንጀል ሊሳተፉ ይችላሉ፡፡ በመሆኑም እነዚህ ተቋማት የብሔራዊ ጥቅም ማስከበሪያ እስከሆኑ ድረስ ደህንነታቸውን ለማረጋገጥ ጠንክሮ መስራት እንደሚጠይቅ ያስገነዝባሉ፡፡
እስካሁንም ተቋማቱን መጠበቅ የተቻለው ጠንካራ የደህንነት ሥራ በመኖሩ መሆኑን ያነሱት ደጉ (ዶ/ር)፤ ዓለም በየጊዜው ራሱን በቴክኖሎጂ እያበለጸገ በሄደ ቁጥር ክፉ አጀንዳ ያነገቡ አካላትም በዚህ ልክ ራሳቸውን እያዘመኑ መሄዳቸው አይቀርም፡፡ የተቋማቶቻችንን ደህንነትና የሀገርን ክብር የማስጠበቅ ሥራ በየጊዜው በቴክኖሎጂ እያደገ ሊሄድ እንደሚገባ አስተያያት ይሰጣሉ፡፡
የሕዝብ አስተዳደርና ፖሊሲ ባለሙያው ገመቹ አራርሳ (ዶ/ር) እንዳሉት ደግሞ፤ የአንዲትን ሀገር ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ በተጻራሪ የሚመለከቱ ሀገራት ሀገሪቱን ለመጉዳት ኢላማ የሚያደርጉት ትላልቅ ተቋማትን ነው፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የዓባይ ግድብ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ኢትዮ ቴሌኮምን የመሳሰሉ ተቋማት ደግሞ ለሀገራችን የኢኮኖሚ መሠረት ብቻ ሳይሆን የሀገር መገለጫዎቻችንም ጭምር ናቸው፡፡
በተለይም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከሠንደቅ ዓላማችን ቀጥሎ ያለ ሠንደቃችን፣ ኢትዮጵያን ከፍ አድርጎ ያሳየ፣ ለአህጉራችን አፍሪካም ኩራት የሆነ ትልቅ ተቋም ነው፡፡ ስም የማጥፋት ዘመቻው መከላከያ ኃይላችንንም ጭምር መሆኑን ያስታወሱት ገመቹ (ዶ/ር) ፤ ለሀገራችን መልካም ዕይታ የሌላቸው ጠላቶች፣ የተቋማቱን መልካም ገጽታ የማጠልሸት፣ ሀገራችን በዓለም አቀፍ ደረጃ ጎልታ እንዳትታይና መልካም ገጽታ እንዳይኖራት በእነዚህ ተቋማት ላይ ይዘምታሉ፡፡
የሀገር መለያ በሆኑ ተቋማት ላይ መዝመት በሀገር ላይ እንደመዝመት ነው፡፡ ዓላማቸው መልካም ገጽታን ማጥፋት ብቻ ሳይሆን፣ የመንግሥትን የደህንነትና የኢኮኖሚ መሠረት ማዳከም ነው፡፡ ይህ ቢሳካላቸው ደግሞ የተቋማቱን አቅም የመሸርሸር፣ የመንግሥትን የኢኮኖሚ መሠረት የማዳከምና በሕዝብና በመንግሥት መሀል ያለው ግንኙነት የማሻከር እቅዳቸው ይሳካላቸዋል። ይህ በጦር ሳይሆን የተለያየ አይነት ጫና በመፍጠር የሚደረግ ጦርነት ነው ሲሉ ያብራራሉ፡፡
ማኅበራዊ ድረ ገጾችን እና የተለያዩ የቴክኖሎጂ አውታሮችን በመጠቀም የሚደረገውን ዘመቻ መከላከል የሚቻለው ደግሞ የተሻለ የደህንነት አቅምን በመገንባት ነው፡፡
በቴክኖሎጂ በሚደረገው ውጊያ በተለያዩ ጊዜያት ተቋማቶቻችን በርካታ የሳይበር ጥቃት ሙከራ እንደሚደረግባቸው ያስታወሱት ገመቹ (ዶ/ር)፤ ይህ ጥረት ምንጊዜም የተሳካ እንዳይሆን የመከላከሉን ሥራ የበለጠ አጠናክሮ መቀጠል እንደሚያሻ ይናገራሉ፡፡
ጤናማ አስተሳሰብ ያለውና ሀገሩን የሚወድ ሁሉ በርካታ ዓመታትን ፈጅተው፣ ብዙ ትውልድ ዋጋ ከፍሎባቸው ዛሬ ላይ የደረሱ ተቋማቶቻችንን ላይ የሚደረጉ ዘመቻዎችን የሚቀባበሉ ዜጎች ከዚህ ድርጊት ቢቆጠቡ መልካም እንደሆነ የሚመክሩት ገመቹ (ዶ/ር) ፤ ከጠላት ጋር ከመዝመት መታቀብ ብቻ ሳይሆን ዜጎች በራሳቸው ተቋማት የገጽታ ግንባታ ላይ ተሳትፎ እንዲያደርጉም ይጠበቃል የሚል አስተያየት ሰጥተዋል፡፡
እነዚህ ተቋማት የአሰራርና ሌላም ክፍተትና ችግር ቢኖርባቸው እንኳ የራሳችን ተቋማት በመሆናቸው ቅሬታችንን ስናቀርብ ለሌሎች ተጻራሪ ኃይሎች አሳልፎ በመስጠት ወይም ለእነዚህ አካላት ምቹ ሁኔታ በሚፈጥር መልኩ መሆን እንደሌለበት ይመክራሉ፡፡
የታሪክ ምሁሩ አቶ አህመድ ዘካሪያ በበኩላቸው፣ በአጠቃለይ የኢትዮጵያ ጂኦፖለቲክስና ስትራቴጂካዊ አቀማመጧ ለዚህ ሰለባ ያደርጋታል። ቀይ ባህርም ሆነ ህንድ ውቅያኖስም ለንግድ ቀጣናው ከፍተኛ መተላለፊያና የዓለምን ንግድ የሚያስተናግዱ በመሆናቸው በዚህ ምክንያት ሀገራችን ላይ ብዙ ጫና ይደረጋል።
ኢትዮጵያ በዓለም ደረጃ የነጻነት ተምሳሌት መሆኗ ተፃራሪ አካላት ይህንን ገፅታዋን ለማበላሸትና ግፊት እንዲበረታባት ለማድረግ ምክንያት እንደሆነ ያነሱት አቶ አህመድ፤ የእኛ መተባበር የሚፈጥረው ጥንካሬ የትኛውንም ጫና ለመመከት ወሳኝ አቅም ነው በማለት አስረድተዋል።
ምሁራኑ እንዳስረዱት፤ ከኢትዮጵያ በተፃራሪ የሚሰሩ አካላት አንድም ፖለቲካዊ ኪሳራን ለማስከተል፣ አንድም ኢኮኖሚያዊ ጫናን ለመፍጠር በሌላ በኩል ደግሞ ለዝርፊያ አላማ ጠንካራ ተቋማቶቻችንን ኢላማ ያደረጉ ጥቃቶችን ለመፈፀም ይተጋሉ፡፡
ይህ እኩይ አላማን ያነገበ ዘመቻ እውን እንዳይሆን ተቋማቶቻችንም በጥንካሬያቸው እንዲዘልቁ እንደ ሀገር በቴክኖሎጂ የበለፀገ ደህንነትን የማስጠበቅ ሥራ ለብሔራዊ ጥቅም በአንድነት የመሰለፍ አቋም ያስፈልገናል።
ዮርዳኖስ ፍቅሩ