አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ዛሬ የአዲስ የተማሪዎች ቅበላን በተመለከተ አሰራሩን ግልጽ አድርጓል። ዩኒቨርሲቲ ከ2017 ዓ.ም የአዲስ የተማሪዎች ቅበላ አሰራርን ይፋ ያደረገው ዛሬ ባዘጋጀው ጋዜጣዊ መግለጫ ነው።
ዩኒቨርስቲው የላቀ ውጤት ያስመዘገቡ እና ልዩ ብቃት ያላቸው ተማሪዎችን አወዳድሮ እንደሚቀበል በዚሁ መግለጫ አስታውቋል። የዩኒቨርስቲው ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ እንዳሉት፣ ራስ ገዝ ሆኖ የተቋቋመው ዩኒቨርሲቲው ተቋማዊ ነጻነት፤ አስተዳዳሪዊ ነጻነት፤ የፋይናንስ ነጻነት እና አካዳሚክ ነጻነት አለው። መብቱ ” ዩኒቨርስቲው መምህራኑን ሆነ ተማሪዎችን የመምረጥ መብት አጎናጽፎታል”
አዲስ ይተገበራል በተባለው የቅበላ አሰራር በ2014፤ 2015 እና 2016 ዓ.ም የትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ የመልቀቂያ ፈተና ወስደው የማለፊያ ነጥብ ያገኙ ተማሪዎች የሚወጣውን መስፈርት ታሳቢ አድርገው በዩኒቨርሲቲው ፖርታል https://portal.aau.edu.et መመዝገብ የሚችሉ መሆኑን ዩኒቨርስቲው አስታውቋል።
በመግለጫው ላይ ተገኝቶ የዘገበው ቲክቫህ እንደዘገበው የመመዝገቢያ መስፈርቶቹን ዶ/ር ሳሙኤል ዘርዝረዋል። ቀዳሚ የሆነውና ዶክተሩ የገለጹት አንዱ መስፈርት የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተናን 50 በመቶ በላይ ውጤት ማምጣት ነው። ይህ መስፈርት የተመዝጋቢዎችን ቁጥር ባገናዘበ መልኩ 60 ወይም 70 በመቶ ድረስ ከፍ ሊል እንደሚችል ጠቁመዋል።
በመቀጠልም ዩኒቨርስቲው በራሱ የሚያዘጋጀው የመግቢያ ፈተና (Undergraduate Admission Test) የሚኖረው ሲሆን ይህንን ፈተና ማለፍም ሌላው ዩኒቨርሲቲው ያስቀመጠው መስፈርት ነው ብለዋል።
ፈተናው ምን መልክ ይኖረዋል ?
በዩኒቨርስቲው መማር ለሚፈልጉ ተማሪዎች የሚቀርበው የፈተና ይዘት ምን መልክ አለው በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ ዶ/ር ሳሙኤል ፈተናው የአፕቲቲውድ (Apptitude) መልክ የሚኖረው እንደሆነ ጠቅሰው የተማሪዎችን የቋንቋ፤ የማመዛዘን እንዲሁም የቀመር አቅማቸውን የሚለካ እንደሚሆን ጠቁመዋል።
ፈተናው ከሌሎች የመግቢያ ፈተና ጋር ተመሳሳይነት ሊኖረው እንደሚችል ያነሱት ፕሬዝዳንቱ ሆኖም የሚወጣው ፈተና ሙሉ በሙሉ የዩኒቨርስቲው እንደሚሆን አስረድተዋል።
የክፍያ እና የስኮላር ሺፕ ሁኔታ በተመለከተ
በዩኒቨርስቲው ለመማር ጥያቄ የሚያቀርቡ ተማሪዎች በሁለት አይነት መንገድ እንደሚስተናገዱ ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል።
አንደኛው መስፈርቱን አሟልተው እና ሙሉ ክፍያ ከፍለው የሚማሩ ተማሪዎች ሲሆኑ ሌላው መንግስት ስፖንሰር ሺፕ እንዲሰጣቸው የሚጠይቁ ተማሪዎች ናቸው።
ይህን በተመለከተ የተቀመጠ ኮታ እንደሌለ የገለጹት ዶ/ር ሳሙኤል እንደ እቅዳቸው ግን 50 በመቶ በመንግስት 50 በመቶ በግል ወጪያቸው የሚሸፈንላቸውን ተማሪዎች ለመቀበል እንደሆነ ገልጸው ካልሆነም ቁጥሩ በተወሰነ መልኩ ልዩነት ሊኖረው እንደሚችልም ጠቁመዋል።
መንግስት ከፍተኛ ብቃት ያላቸውና ተወዳዳሪ የሆኑ ተማሪዎችን ለሀገር በሚፈለጉ የስልጠና መስኮች ወጪን ጭምር በመሽፈን የሚያስተናግድበት ሥርዓት እንደሚኖር እና ለሴቶች ለአካል ጉዳተኞች እና ከታዳጊ ክልል ለሚመጡ ተማሪዎች ልዩ ትኩረት እንደሚሰጥም ተመላክቷል።
ተማሪዎች በሚያመለክቱበት ወቅት ብዙ ቅጾችን እንደሚሞሉ ፤ ስኮላርሺፕ የሚጠይቁ ተማሪዎች ከፍለው መማር እንደማይችሉ የሚያሳይ ማስረጃ ከሚመለከተው አካል ማሟላት እንደሚጠበቅባቸው እና የሚያስገቡት መረጃ ትክክለኛነቱ እንደሚጣራና ሐሰተኛ ሆኖ ከተገኘ የህግ ተጠያቂነት እንደሚያስከትል ጭምር አንስተዋል። ተጨማሪ መረጃዎችን ዩኒቨርስቲው በተከታታይ እንደሚሰጥ አረጋግጧል።
ኢትዮ ሪቪውን በቴሌግራም ይከተሉ https://t.me/+f_kxmaPjD-9jYTdk