በድርጅት መከፋፈል ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ መጠነኛ መወነጃጀል ቢኖርም፣ በአሁኑ ሰዓት የሚሰማው መረጃ ግን እየተካረረ ሄዷል። የእን ዶክተር ደብረጽዮንና አቶ ጌታቸው ቡድን መካከል መለያየቱ ይፋ ከሆነ በሁዋላ አንደኛው ቡድን ለማጥቃት ሚስጥር እስከማውጣት ደርሰዋል።
የእነ አቶ ጌታቸው ቡድን የሆኑት አመራር “በጦርነቱ ወቅት ከባንክ ተዘርፎ የነበረ ገንዘብና ወርቅ እነ ደብረጽዮን የት እንዳደረሱት ሊመረመር ይገባል” ሲሉ መናገራቸው የሰሞኑ መነጋገሪያ ቢሆንም፣ ዶክተር ደብረጽዮን ራሳቸውን ለመከላከል ኤአንድ ሚሊዮን ህዝብ ሞተ፣ ጄኖሳይድ ተፈጸመ የሚባለው መረጃ የለውም” ሲሉ በገሃድ መናገራቸው “ጄኖሳይድ ተፈጸመ በሚል ሲሰራ የነበረውን ፕሮፓጋንዳና በተለይም የኤርትራ ወራሪ ሃይል ያደረሰውን ግፍና ጭፍጨፋ ለማድበስበስ ታስቦ የተሰራ ነው” በሚል ትችት አስነስቷል። ከዚያም በላይ እሳቸው የሚመሩት ቡድን ከሻዕቢያ ጋር የጀመረውን አዲስ ግንኙነት የሚያረጋግጥ እንደሆነ እየተገለጸ ነው።
ዛሬ የጀርመን ድምጽ እንደዘገበው ደግሞ ዶከተር ደብረጽዮን የቀድሞውን ሌተናል ጄነራል ጻድቃንን ስም ጠርተው የስልጣን ጥማት ያለባቸውና ስልጣን ለመጠቅለል ብዙ ርቀት መሄዳቸውን በህዝባዊ ወይይት ላይ ተናግረዋሎኦ ከስር ዘገባውን ያንብቡ።
ዶ/ር ደብረፅዮን ገብረ ሚካኤል፣ ጀነራል ፃድቃን ገብረትንሳኤን፥ ስልጣን ለመጠቅለል በማቀድ፣ የቆየ ቂም በመወጣት እና ሌሎች ከዚህ በፊት በይፋ ያልተሰሙ መረጃዎች በመግለፅ ሲተቹ ተደምጠዋል። ዶክተር ደብረፅዮን እርሳቸው የሚመሩት ህወሓት፣ ሰላም የማይፈልግ አድርጎ የማቅረብ የተሳሳተ ፍረጃ ከትግራይ ባለስልጣናት በኩል እየቀረበበት መሆኑን ተናግረዋል
በዶክተር ደብረፅዮን የሚመራው ህወሓት ባሳለፍነው ሳምንት የመጨረሻ ቀናት መቐለን ጨምሮ በተለያዩ የትግራይ ከተሞች ህዝባዊ የተባሉ ስብሰባዎች አካሂዷል። በእነዚህ መድረኮች የፖርቲው አመራሮች ክፍፍል በስፋት መነሳቱ የተገለፀ ሲሆን፥ ህወሓትን ለማጥፋት፣ ስልጣን ለመጠቅለል የሚንቀሳቀሱ ተብለው የተገለፁ አመራሮች በስም እየተጠቀሱ ወቀሳ እንደተሰነዘረባቸው ተሰምቷል።
ከትላንት በስትያ ቅዳሜ በመቐለ በተካሄደ እና የህወሓት ሊቀመንበር ዶክተር ደብረፅዮንን ጨምሮ ሌሎች የፖርቲው አመራሮች እና የተመረጡ በሺዎች የሚቆጠሩ ተሳታፊዎች የታደሙበት መድረክ ላይ ንግግር ያደረጉት ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል፥ የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዝደንት የሆኑት ጀነራል ፃድቃን ገብረትንሳኤን፥ ስልጣን ለመጠቅለል በማቀድ፣ የቆየ ቂም በመወጣት እና ሌሎች በርካታ ጉዳዮች በማንሳት እንዲሁም ከዚህ በፊት በይፋ ያልተሰሙ መረጃዎች በመግለፅ ሲተቹ ተደምጠዋል። ዶክተር ደብረፅዮን በንግግራቸው እርሳቸው የሚመሩትን ህወሓት ሰላም የማይፈልግ አድርጎ የማቅረብ የተሳሳተ ፍረጃ ከትግራይ ባለስልጣናት በኩል እየቀረበበት መሆኑ የገለፁ ሲሆን፥ ይህ ውሸት ነው በማለት ሲያጣጥሉት ተደምጠዋል።
ደብረፅዮን “ለምሳሌ በደቡባዊ ዞን በተደረገ መድረክ ጀነራል ፃድቃን እኛ ሰላም እንፈልጋለን፣ እነሱ የሚሹት ጦርነት ነው ሲል ሰምታችሁታል። በጦርነቱ ወቅት ደሴ ተሻግረን ሰሜን ሸዋ ስንጠጋ፥ ድርድር ያስፈልጋል ወይ ሲባል እኔ አዎን ያስፈልጋል ነው ያልኩት። በሰላም ሊፈታ ስለሚገባው። እሱ ግን ከማን ጋር ነው የምንደራደረው፣ ውጊያው አልቋል ሲል የነበረ ነው። አሁን ግን እኔ ሰላም ነኝ እነሱ ጦርነት ናቸው የሚፈልጉ ማለት ጀመረ” ብለዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር ካቢኔ ካደረገው መደበኛ ስብሰባ በኃላ ትላንት ባሰራጨው መግለጫ፥ በክልሉ ያለው ፖለቲካዊ ችግር በህወሓት እና የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር መካከል የተፈጠረ አለመግባባት አድርጎ ማቅረቅ የተሳሳተ ነው ብሏል። ችግሩ በህወሓት ከፍተኛ አመራሮች መካከል የተፈጠረ ነው ያለው ጊዚያዊ አስተዳደሩ፥ ግዚያዊ አስተዳደሩ የዚህ ውዝግብ አካል እንዳልሆነ ህዝባችን ይገንዘብልን ብሏል። ይሁንና ይህ በህወሓት አመራሮች መካከል የተፈጠረው ክፍፍል የአስተዳደር ስራዎችን እያደናቀፈ ስለመሆኑ አልካደም። ይህን በትግራይ ኮምኒኬሽን ቢሮ በኩል የተሰራጨ መግለጫ የትግራይ ኃይሎች ላይ ያነጣጠረ ስም ማጠልሸት እና ውንጀላ በሕግ ስርዓት እናስይዘዋለን ያለ ሲሆን እነዚህ የፀጥታ ኃይሎች በአስተዳደሩ ስር ሆነው እየተመሩ እና ከፖለቲካዊ አጀንዳዎች ገለልተኛ ሆነው ተልእኮአቸውን እንደሚፈፅሙ ጠቅሷል።
በሌላ በኩል የትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዝደንት ጀነራል ታደሰ ወረደ ቅዳሜ የታሰበውን የዓለም ሰላም ቀን አስመልክቶ በተዘጋጀ መድረክ፥ የፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት ለትግራይ የሰላም ዕድል የፈጠረ ነው ያሉ ሲሆን ከውሉ በኃላ የሚጠበቅ የጦርነቱ መነሻ የሆነ ፖለቲካዊ ምክንያቶችን ለመፍታት የተደረገ ነገር እንደሌለ አንስተዋል።
ጀነራል ታደሰ ወረደ “የፕሪቶርያ ውል ወደ ሰላም አሸጋግሮናል። ወደ ሰላም ተሸጋገርን ማለት ለጦርነቱ ምክንያት የሆነ ነገር በሰላማዊ እና ፖለቲካዊ መንገድ ልትፈታው ግዴታ መግባት ማለት ነው። በትግራይ ስናይ ሰላም እጃችን ላይ አለች፤ ጦርነት የሆነ ፖለቲካዊ መነሻ ያለው እንጂ ዝምብሎ የሚከፈት ስላልሆነ፥ ለጦርነቱ መነሻ የሆኑ ምክንያቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ገና ትግል የሚያስፈልጋቸው ናቸው” ብለዋል።