በአዲስ ዓመት ወቅቱ ከመዋቡ እንዲሁም አዲስ ተስፋ የመሰነቅ እና ከአሮጌ የመላቀቅ ውብ ስሜት አብሮ ከመምጣቱ ባለፈ የዘመን መለወጫ ሲመጣ ከሚሰሙን ልዩ ልዩ ስሜቶች ጋር ሳይነጣጠሉ የበዓል ሙዚቃዎችም በዓሉን ብቻ ሳይኾን አዲስ ዓመትንም ያበስሩናል፡፡
ዛሬ በመስከረም 01/01/2017 ዓ.ም ከጠዋት ጀምሮ በሬዲዮ፣ በቴሌቪዥን እና በሌሎችም የመገናኛ አውታሮች ስትሰሟቸው የዋላችኋቸው ሙዚቃዎች ዘመን መለወጫ በመጣ ቁጥር ከልባችን የማይጠፉትን እንደኾነ ተስፋ እናደርጋለን፡፡
እኛም በሥራ ላይ ኾነን ግን ደግሞ ከጆሯችን እና ከልባችን የማይጠፉትን ሙዚቃዎች ልናስታውሳችሁ ወደናል፡፡ በድጋሚ መልካም በዓል እንዲኾንላችሁ መመኘታችንን ሳንዘነጋ፡፡
እንቁጣጣሽ- በዘሪቱ ጌታሁን
አዲስ ዘመን በአደይ አበባ ተሞሽሮ ሲመጣ፣ በሬዲዮም ኾነ በቴሌቪዥን ከምንሰማቸው ውብ የዘመን መለወጫ ሙዚቃዎች ውስጥ በብዙዎቻችን ጆሮ ላይ የታተመው የዘሪቱ ጌታሁን እንቁጣጣሽ ዜማ ነው፡፡
እንቁጣጣሽ
እንኳን መጣሽ
በአበቦች መሐል
እንምነሽነሽ
ይሄን ዜማ አላውቀውም የሚል ብዙም ኢትዮጵያዊ እንደማይኖር ተስፋ እናድርጋለን፡፡
በብዙኃኑ ዘንድ ተወዳጅ የኾነው የዚኽ ሙዚቃ ግጥም እና ዜማ ደራሲ ክቡር ዶክተር አርቲስት ተስፋዬ አበበ (ፋዘር) ናቸው፡፡ ይኼው ዜማ ከአደይ አበባ እኩል ለኢትዮጵያውያን የእንቁጣጣሽ በዓልን ብስራት መናገሩን ይዞ ዘመናትን መሻገሩን ቀጥሏል።
በዚኽ ዜማ ውስጥ ስለመስከረም እና አደይ አበባ ቁርኝት የተባሉትን ትተን “ኢትዮጵያ ሀገሬ የምመኝልሽ፣ በአዲሱ ዓመት እንዲያምርብሽ” እያለች ዘሪቱ ሁሌም መስከረም ሲጠባ እኛ ኢትዮጵያውያን ለሀገራችን ያለንን መልካም ምኞት እንድንገልጽ ታግዘናለችና አመስግነናት ወደ ሌሎቹ ዜመኞች እንሸጋገር፡፡
ክቡር ዶክተር አርቲስት ጥላሁን ገሰሰ – “የ13 ወር ፀጋ”
“በፀሐይ ብርሃን ደምቃ ክረምትና በጋ
የትውልድ ማገር ያላት የ13 ወር ፀጋ
ወግና ልማዳችን የወረስነው ካበው
የአውደ ዓመቱ ትዝታ አይጠፋም ህያው ነው…”
በ1980 ዓ.ም የወጣው ይኽ ሙዚቃ ግጥሙ በክፍለ እየሱስ አበበ እና ታምራት አበበ ሢሰራ ዜማው ደግሞ በታምራት አበበ የተደረሰ ነው።
“ግንቦት ሰኔም አለፈ ዳመና አያለበሰ
ሐምሌም በክረምት ዝናብ መሬቱን አያራሰ
ልጆች በየቤታቸው ለሆታ ሲጠራሩ
ከጅራፉ ጩኸት ጋር የቡሔን በዓል ሲያከብሩ” ሲልም ጋሽ ጥላሁን ከትውልድ ትውልድ የተላለፈውን የልጅነት ባሕል ከወቅቱ መለዋወጥ ጋር አዋዝቶ በዜማ ይናገራል።
በዚኽ ሙዚቃ ውስጥ ብዙ ስንኞች ስለ ዓውደ ዓመት እና አከባበሩ ከምናደምጠው በላይ ምስል የሚከስቱ ናቸውና ትውስታችን በጆሮ የማድመጥ ብቻ ሳይኾን የማየት ያኸል ነው፡፡
ሰለሞን ደነቀ ” ሥርቅታዬ”
በየዓመቱ ከቡሔ እስከ እንቁጣጣሽ ባለው የአዲስ ዘመን መቀበያ ጊዜ ‘ሥርቅታዬ’ በተሰኘው እና
“… ትምህርት ቤት ተከፍቶ፣ ሁሉም ረፍት ጨርሶ
ለእንቁጣጣሽ ዝግጅት፣ ቅዱስ ዮሐንስ ደርሶ
ሁሉም ብቅ ብቅ ሲል፣ አዳዲስ ልብስ ለብሶ
ቤቱ ተጎዝጉዞ በለምለም ቄጤማ
ታስነኪው ነበረ እንዲህ በሚል ዜማ
አበባይሆሽ
ለምለም…”
እያለ በሚቀጥለው የተወዳጁ ድምፃዊ ሰለሞን ደነቀ ሙዚቃ የበዓል አከባበሩን ድምቀት እና የልጅነት ጣፋጭ ጊዜን ፍንትው አድርጎ የሚያስታውሰን አይረሴ ዜማ ነው።
ከነሐሴ እስከ መስከረም ባለው ወቅት መገናኛ ብዙኃንም በዚኸ ሙዚቃ ብዙኃኑን “ስቅ” እያስባሉ ወደ ኋላ በትዝታ ማስኮብለላቸውን ይያያዙታል።
ሥርቅታዬ ዜማ እና ግጥሙ የራሱ የሰለሞን ደነቀ ሲኾን በድምጻዊት የሺእመቤት ዱባለ እና ጥቂት ድምጻውያን ተቀባይነት ለአድማጭ ጆሮ የበቃ ውብ የበዓል ሙዚቃ ነው፡፡
አስቴር አወቀ – እዮሃ አበባዬ
“እዮሃ አበባዬ
መስከረም ጠባዬ
መስከረም ሲጠባ
ወደ ሀገሬ ልግባ
ወደ አዲስ አበባ…” እያለች በተስረቅራቂ ድምጿ ስታዜም አብሯት የሚያዜመው ሰው ስፍር ቁጥር የለውም።
ይኼን ዘፈን በተለያዩ የሚዲያ አማራጮች ዛሬ ስንት ጊዜ ሰምታችሁታል? ይኽ ዘፈን እንቁጣጣሽ በመጣ ቁጥር ሴቶች በየቤቱ እየዞሩ ሚዘፍኑት አበባየሁሽ ግጥም በአስቴር ተውቦ ስለሚቀርብ ድምጻዊቷ እንቁጣጣሽ በመጣ ቁጥር ጆሯችን ላይ ታዜምልን ዘንድ ፈቅደንላታል፡፡
ሀመልማል አባተ- እንኳን አደረሳችሁ
“የክረምቱ ወር አልፎ የበጋው መጥቷል
ሜዳው ሸንተረር ጋራው በአበቦች ደምቋል
ሸመንሟናዬ ውብ ሽቅርቅሩ
ድረስ ለዓውድ ዓመት በአገር መንደሩ”
የሚለው ሙዚቃ መግቢያዋ ላይ ከምታስቀድመው እልልታ ጋር የሰዉ ጆሮ ሲደርስ አዲስ ዓመት አዲስ ዓመት መሽተቱ ያይላል። ይኽን ዜማ የበዓል አከባበርን ወግ እና ባሕል ከሚያሳየው የሙዚቃ ቪዲዮው ጋር ከዋዜማው ጀምሮ የማያስተላልፍ ቴሌቪዥን ጣቢያ የለም ለማለት ያስደፍራል።
“እንኳን አደረሳችሁ እንኳን አደረሳችሁ
እስኪ እልል እልል እንበል እስኪ እልል በሉ ሁላችሁ” እያለች በዜማ የምታደርሰው መልካም ምኞት ሙዚቃው ባልተከፈተበት ኹናቴ ውስጥ ሁሉ ዓውደ ዓመት ስለኾነ ብቻ በጆሮ ያቃጭላል።
ቴዎድሮስ ካሳሁን – አበባየሁሽ
የኢትዮጵያ ሚሊኒየምን ተከትሎ በአዲስ ዓመት ከተለቀቁ ሙዚቃዎች መካከል አንዱ ነው። አዲስ ዘመንን ተከትለው የሚመጡ ተስፋዎችን ሰንቆ ይዞ በአዲስ ዓመት መባቻ ሲሰማ መጪው ዓመት ጥሩ ይኾናል የሚል መልዕክት በውስጣችን እንዲሰርጽ ያደርጋል።
“ምልኤላዊው ዘመን
የአምላክ በረከቱ
በኢትዮጵያ ትንሳኤ
ዘመነ ሁለቱ
ስትሰሙ መለከት
ወደ ምሥራቅ ተመልከቱ…”
በማለት ለስለስ አድርጎ ጀምሮ አበባየሁሽ በመባል የሚታወቀውን የሴቶች ዜማ መነሻ በማድረግ ሞቅ አድርጎ የምርቃት እና የተስፋ ግጥሞቹን በውብ ዜማ ያወርደዋል።
በዚኽ ሙዚቃ ቴዲ ከአዲስ ዓመት ጋር አያይዞ ለሀገሩ ትንሳኤ መድረሱን፣ መሰናክሎቿን ሁሉ አልፋ እና ጠላቶቿን አሸንፋ ልክ እንደ ዘመኑ ታሪኳ የሚታደስ፣ ታሪኳ የሚዘከር፣ የጀግኖች ሀገር እንዳለችን ይነግረናል፡፡
“ሰለሞን አለ ጊዜ ለኩሉ
ይሰግዱልሻል የናቁሽ ሁሉ”
እያለ ለሀገር ያለውን ህልም ይናገራል።
ሀሊማ አብዱራሕማን- እዮሃ አበባ
“አበባው አበበ ፣ እዮሃ አበባ
ላየው መጥቻለሁ፣ እዮሃ አበባ
ከአፋፍ ከገደሉ፣ እዮሃ አበባ
አብሬህ እውላለሁ ፣ እዮሃ አበባ
ካጎረሰኝ እጅህ ፣ ርቄ ሰንብቻለሁ
አበይ ያደግኩበት ፣ ናፍቆኛል መንደሩ
እንዴት ከርሞ ይሆን፣ ወገን ገራገሩ …”
እያለች ሆድ በሚያባባ ዜማ እና ግጥም በአባቷ የመሰለችውን ሀገሯን ለአዲስ ዓመት የምትጎበኝበትን መንገድ ታወጋለች። ይኽ ሙዚቃ በተለይ በስደት ላይ ሲኮን ስሜቱ እንደሚልቅ ተሰዳጆች አብነት ናቸው፡፡
ከአዲስ ዓመት እና ከዓውደ ዓመት ሙዚቃዎች ጋር ብዙ ነገሮችን ማንሳት ቢቻልም ለዛሬው እነዚሁ ይብቁን፡፡ ሙዚቃ እንደ አድማጮች ፍላጎት የሚፈረጅ በመኾኑ ከላይ ያቀረብናቸው ሙዚቃዎች የብዙዎቹን ጆሮ የሳቡ እንጂ ብቸኞቹ አይደሉም፡፡
ለዓመት በዓል ከተዜሙ ሙዚቃዎች ውስጥ አንዳንድ ስንኞችን እየነቀስን ተመራርቀን በድጋሚ አዲሱ ዓመት የመልካም ነገሮች ሁሉ ብስራት እንዲኾንልን እንመኝ፡፡
ዓመቱ ግጥማችን ይሁን፤ እማይበጀን ገለል ይበል፤ ለከርሞ በአማን ያድርሰን ፤ ለሀገርና ለሕዝብ ደግ ደጉን ያምጣልን፤ እንደ በሬ ሻኛ ከሰው በላይ ያውላችሁ፤ የዕድሜ ጎዳና ይስጥልን፤ ሀገሩን ጥጋብ ቀዬውን ሰላም፣ አውድማውን ፍሬያማ ያድርግልን!
አሜን! አላችሁ?
መልካም አዲስ ዓመት! via AMC