ከሳሾች ከተስሳሾች ላይ የሚጠይቁት የገንዘብ ክፍያ በሌለበት ሁኔታ በ1ኛ ተከሳሽ (የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ) ስም የተከፈተው የባንክ ሂሳብ ታግዶ የሚቆይበትም ሆነ በተካሄደው ምርጫ መነሻ ተቋሙን እንዳይነቀሳቀስ ለማገድ በቂ የሆነ ህጋዊ ምክንያት እንዳልተገኘ ጠቅሶ ፍርድ ቤቱ የቀደመውን ውሳኔ መገለበጡን አስታወቀ።
ክሱን የመሰረቱት እነ ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ፣ አትሌት ገዛኸኝ አበራ፣ በዓለም ዓቀፉ የኦሊምፒክ ኮሚቴ የታገደው የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን እና የኢትዮጵያ ቴኒስ ፌዴሬሽን እንደነበሩ ይታወሳል። ክስ የተመሰረተባቸው የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት፣ ጸሃፊ፣ ዶ/ር ኤደንና አቶ ገዛኸኝ ነበሩ።
በእነ ኃይሌ ክስ የተመሰረተባቸውና ሙሉ እግድ የተጣለበት የኦሊምፒክ ኮሚቴ ከሳሾች ላቀረቡት የእግድ ክስ ቀርበው ጭብጡን እንዲያስረዱ፣ ባቀረቡት የክስ መቃወሚያና “የእግድ ይነሳልን” ጥያቄ መሰረት ዛሬ ባስቻለው ችሎት ላይ ከሳሾች አለመገኘታቸውን ከውሳኔው በሁውላ የተበተነው የብይን ደብዳቤ አመልክቷል።
ፍርድ ቤቱ በብይኑ ይፋ እንዳደረገው ተከሳሾች 1ኛ- የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ፣ 2ኛ ዶ/ር አሸብር ወ/ጊዮርጊስ ቀረቡ፣ 3ኛ ዶ/ር ኤደን አሸናፊ ፣ 4ኛ – አቶ ዳዊት አስፋው አልተጠሩም፣ 5ኛ እቶ ገዛኽኝ ወልዴ አልተጠሩም፣ የፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት ቀርበዋል። የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴን ወክለው የቀረቡት ጠበቃዎች መኮንን አምባና አንዱዋለም አሰፋ ናቸው።
ከሳሽ ወገኖችን ወክለው የቀረቡት ጠበቆች አንደኛ ተከሳሽ / ኦሊምፒክ ኮሚቴ ባቅረቡት አቤቱታ ላይ አስተያየት እንዲሰጡ ጠይቋል። ይሁን እንጂ ከሳሾችን ወክለው የቀረቡት ጠበቆች “ጉዳይ የከሳሾችን መብትና ጥቅም ብቻ የሚመለከት ሳይሆን የሰፊው ህዝብ መብት እና ጥቅም ጋር የተያያዘ በመሆኑ 1ኛ ተከሳሽ ያቀረቡት አቤቱታ ላይ ተገቢውን አስተያየት ለመስጠት ጊዜ የሚያስፈልገን በመሆኑ ያለንን አስተያየት በዝርዝር ለማቅረብ ተለዋጭ ቀጠሮ እንዲሰጠን” ብለዋል። ፍርድ ቤቱ ግን የቀደምው የዕግድ ውሳኔና ትዕዛዝና እንደጸና መቀጠል እንደማይችል ምክንያት ዘርዝሮ ጥያቄውን ” ታልፏል” ብሏል።
የቀደመውን ውሳኔውን ሲገለብጥ፣ ቀደም ሲል የጣለው ዕግድ አግባብ አለመሆኑን በማመኑ እንደሆነ ህግ ጠቅሶና ዝርዝር ማብራሪያ ሰጥቶ በብይኑ ያብራራው ችሎቱ ከሳሾች ማብራሪያ እንዲሰጡ ሲጠይቁ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው አስተያየት የመስጠት መብታቸው በታለፉን አመለክቷል።
በዚሁ አግባብ ያስቻለው ችሎት ቀደም ሲል ራሱ ጳጉሜ 04 ቀን 2016 ዓ/ም በዋለው ችሎት በኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቱ ስም በተለያዩ ባንኮች የተከፈተው የባንክ ሂሳብ እና የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ግንቦት 06ንቀን 2016 ዓ.ም እና ሰኔ 04 ቀን 2016 ዓ.ም ባደረጋቸው የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ያስተላለፈው ውሳኔ፣ ያካሄደውን የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ምርጫ፣ በጥቅሉ ሁለት የእግድ ትዕዛዝ የሰጠ ቢሆንም “…ከሳሾች ካቀረቡት የክስ ዓይነት እና ከተጠየቀው ዳኝነት አንጻር ስናየው ከሳሾች ከተስሳሾች ላይ የሚጠይቁት የገንዘብ ክፍያ በሌለበት ሁኔታ በ1ኛ ተከሳሽ ስም የተከፈተው የባንክ ሂሳብ ታግዶ የሚቆይበት በቂ የሆነ ህጋዊ ምክንያት አልተገኘም” ሲል በይኗል።
“1ኛ ተከሳሽ ያቀረቡት የእግድ ይነሳልኝ አቤቱታን መነሻ በማድረግ ኣንዲሁም ከቀረበው የክስ ዓይነት እና ከተጠየቀው የዳኝነት ጥያቄዎች አንፃር በዋናው ጉዳይ ላይ መደበኛ ችሎት ተገቢውን ትዕዛዝ እስከሚስጥ ድረስ ከአሁን ቀደም በዚህ መዝገብ ላይ ተሰጥቶ የነበረው የእግድ ትዕዛዝ ሊነሳ ይገባል ወይስ አይገባም የሚለውን ጭብጥ በመያዝ ከተገቢው የህግ ድንጋጌዎች አንጻር ጉዳዩ ተምክቶታል” ያለው ፍርድ ቤቱ የቀደመውን ውሳኔ ሙሉ በሙሉ ገልብጧል። ለተግባራዊነቱም ትዕዛዝ ሰጥቷል። ፍርድ ቤቱ ” ተቋሙ” ያለው የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ በዓለም ዓቀፉ የኦሊምፒክ ቻርተር መሰረት የተቋቋመ፣ በመንግስት ፖሊሲ የሚደገፍ፣ የአገርን ጥቅምና ክብር የሚያስተብቅ፣ በአህጉርና በዓለም ዓቀፍ ደረጃ የሚሰራ ተቋም እንደሆነ አጽንዖት ሰጥቷል።
ሙሉው የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ከስር ያንብቡ ወይም ፒዲ ኤፍ ላይ የተያያዘውን ያንብቡ።
መዝገቡ የተቀጠረው የከሳሾች አስተያየት ለመጠባበቅ ሲሆን ከሳሾች በጠበቆቻቸው በኩል በችሎት ላይ የቀረቡ ሲሆን፣ ከሳሾችን ወክለው የቀረቡት ጠበቶች የፍርድ ቤቱ መጥሪያ ያልደረስን ቢሆንም የ1ኛ ተከሳሽ ተቋም ፕሬዝዳንት በሚዲያ ላይ የእግድ ትዕዛዙ እንዲነሳ አቤቱታ አቅርቤን ለዛሬ ቀጠሮ መያዙን ሰምተን የቀረብን ቢሆንም የመጥሪያ አደራረስ ላይ ከፍተኛ የስነ-ስርዓት ጉድለት ያለ ሲሆን 1ኛ ተከሳሽ ያቀረቡት አቤቱታ ግልባጭ ላይ ቃለ መሃለ የፈፀመው አካል ስም የማይታወቅና የፍርድ ቤቱ ህጋዊ ክብ ማህተብ የሌለው በመሆኑ በዚህ አቤቱታ ላይ አስተያየት ለመስጠት ስለሚያስቸግረን ፍርድ ቤቱ የቀረበው እቤቱታ በትክክል ከፍርድ ቤቱ የወጣ ስለመሆኑ እንዲያረጋግጥልን ሲሉ አመልክተዋል፡፡
ችሎቱም በከሳሾች ጠበቆች በኩል የቀረበውን የመጥሪያ አደራረስ ስነስርዓት የተመለከተ ሲሆን የፍርድ ቤቱ መጥሪያ ከቴኒስ ፌዴሬሽን ውጪ ለሌሎች ከሳሾች የደረሰበት ማረጋገጫ ሰነድ ባይቀርብም ከሳሾች በጠበቆቻቸው አማካይነት በችሎት ላይ የተገኙ በመሆኑ እና ዋና ጉዳይ ከሳሾች በቀረበው አቤቱታ ላይ ያላቸውን አስተያየት በመስማት ተገቢውን ትዕዛዝ መስጠት መሰረታዊ የክርክር ሃደት ሚዛናዊነት እና ፍትሃዊነት ለመጠበቅ የሚረዳ መሆኑን በመረዳት ምንም እንኳን ለእያንዳንዱ ከፍርድ ቤቱ መጥሪያ የደረሰበት ማረጋገጫ ባይቀርብም፣ ከላሾች በጠበቆቻቸው አማካይነት በችሎት ላይ ስለተገኙ ከመጥሪያ አደራረስ ጋር በተያያዘ ከከሳሾች ጠበቆች በኩል የተሰጠውን ቅሬታና ጥያቄ ፍርድ ቤቱ ሳይቀበለው አልፎታል።
በሌላ በኩል ከሳሾችን ወክለው የቀረቡት ጠበቆች ጉዳይ የከሳሾችን መብትና ጥቅም ብቻ የሚመለከት ሳይሆን የሰፊው ህዝብ መብት እና ጥቅም ጋር የተያያዘ በመሆኑ 1ኛ ተከሳሽ ያቀረቡት አቤቱታ ላይ ተገቢውን አስተያየት ለመስጠት ጊዜ የሚያስፈልገን በመሆኑ ያለንን አስተያየት በዝርዝር ለማቅረብ ተለዋጭ ቀጠሮ እንዲሰጠን ሲሉ የጠየቁ ቢሆንም፣ ከሳሾች የፍርድ ቤቱ መጥሪያ ከ3ኛ ከሳሽ ውጪ ለእያንዳንዳቸው የደረሰ መሆኑን የሚስረዳ ማስረጃ ባይቀርብም በጉዳዩ ላይ ያላቸውን አስተያየት ይዘው እንዲቀርቡ በአንድም ሆነ በሌላ አግባብ ቀጠሮ መያዙን አውቀው እስከቀረቡ ድረስ ክጉዳይ ውስብስብነት እና አንገብጋቢነት አንፃር የከሳሾች ጠበቆች በአንደኛ ተክከሳሽ በኩል የቀረበው የእግድ ይነሳልኝ አቤቱታ ግልባጭ በችሎት ላይ ከደረሳቸው በኋላ በቀረበው አቤቱታ ላይ ያላቸውን አስተያየት በቃል እንዲሰጡ በችሎት ላይ እድል የተሰጣቸው ቢሆንም፣ ያላቸውን አስተያየት በቃል ለመስጠት ባለመፈለጋቸው ምክንያት ከሳሾች በጉዳዩ ላይ አስተያየት የመስጠት መብታቸው ታልፋል። ችሎቱም 1ኛ ተከሳሽ በቀን 02/01/2017 ዓ.ም ጽፈው ያቀረቡት የእግድ ትዕዛዝ ይነሳልኝ አቤቱታ መሰረት በማድረግ እንዲሁም ከሳሾች በተሳሽ ላይ የመሰረቱት የክስ ይዘትና የተጠየቀው ዳኝነት አንጻር የቀረበለትን አቤቱታ በመመርመር ተከታዩን ብይን ሰጥታል።
ብይን
ለዚህ ብይን መሰረት መነሻው የሆነው ጉዳይ 1ኛ ተከሳሽ ያቀረቡት የእግድ ትዕዛዝ ይነሳልኝ አቤቱታ ሲሆን ይዘቱም በአጭሩ 1ኛ ተከሳሽ በዓለም ዓቀፍ ኦሊምፒክ ቻርተር እና ቻርተሩን ተክትሎ በጸደቀው የተቋሙ መተዳደሪያ ደንብ መሰረት የተቋቋመ በመንግስት የስፖርት ፖሊሲ መሰረት ስፖርቱን የሚመራና በምንግስት ድጋፍ የሚተዳደር ተቋም ሲሆን የኮሚቴው አባላት ባልሆነ እና ይሄንን አቤቱታ ለማቅረብ መብትና ጥቅም በሌላቸው ሰዎች አማካይነት የቀረበውን አቤቱታ መሰረት በማድረግ ፍርድ ቤቱ ጷግሜ 04 ቀን 2016 ዓ.ም በዋለው ችሎት በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ስም በተለያዩ ባንኮች የተከፈተው የባንክ ሂዳብና የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ግንቦት 06 ቀን 2016 ዓ.ም ባደረጋቸው የጠቅላላ ጉባዔ ስብሰባዎች ላይ ያስተላለፈው ውላኔ እና ያከናወነው የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ምርጫ ታግዶ እንዲቆይ የሰጠው የእግድ ትዕዛዝ የተቋሙን ሀገራዊ፣ አህጉራዊ እና ዓለም እንቅስቃሴዎች የሚገድብና የተቋሙን ሀገራዊ፣ አህጉራዊና ዓለም ዓቀፋዊ እንቅስቃሴዎችን የሚገድብና የተቋሙ ቢሮ ሙሉ በሙሉ እንዲዘጋ የሚያደርግ በመሆኑ እግዱ እንዲነሳልኝ በማለት አመልክተዋል።
ከሳሽ በ1ኛ ተከሳሽ በኩል የቀረበው የዕግድ ትዕዛዝ ይነሳልኝ አቤቱታ ላይ ያላቸውን አስተያየት እንዲያቀርቡ እድል የተሰጣቸው ቢሆንም፣ ቀደም ሲል የተሰጠው የእግድ ትዕዛዝ ሊነሳ ይገባል ወይስ አይገባም የሚለው አጭር ጉዳይ ላይ በቃል ያላቸውን አስተያየት መስጠት እየቻሉ ያለ በቂ ምክንያት ተለዋጭ ቀጠሮ መጠየቃቸው ተገቢ አለመሆኑን እንዲሁም ከጉዳዩ አጠቃላይ ሁኔታ እና አንገብጋቢነት አንጻር በጉዳዩ ላይ ተገቢው ትዕዛዝ መሰጠት ያለበት መሆኑን በመረዳት ከሳሾች በጉዳዩ ላይ ያላቸውን አስተያየት የማቅረብ መብታቸው ታልፎ ጉዳዩ ታይቷል።
በዚሁም መሰረት 1ኛ ተከሳሽ ያቀረቡት የእግድ ይነሳልኝ አቤቱታን መነሻ በማድረግ ኣንዲሁም ከቀረበው የክስ ዓይነት እና ከተጠየቀው የዳኝነት ጥያቄዎች አንፃር በዋናው ጉዳይ ላይ መደበኛ ችሎት ተገቢውን ትዕዛዝ እስከሚስጥ ድረስ ከአሁን ቀደም በዚህ መዝገብ ላይ ተሰጥቶ የነበረው የእግድ ትዕዛዝ ሊነሳ ይገባል ወይስ አይገባም የሚለውን ጭብጥ በመያዝ ከተገቢው የህግ ድንጋጌዎች አንጻር ጉዳዩ ተመርምሯል።
እንደተመረመረውም መሰረት በፍ/ብ/ስ/ስ/ህግ ቁጥር 151፣ 152 እና 154 (1) መሰረት ፍርድ ቤቱ የያዙትን የፍታብሄር ጉዳዮች ላይ የመጨረሻ ፍርድ እስከሚሰጥ ድረስ ለክርክሩ ምክንያት የሆነው ንብረት ወይም ክርክር የቀረበበት ጉዳይ ላይ የሚስጥ ፍርድ የሚፈጸምበት ንብረት እንዳይበላሽ፣ እንዳይጠፋ እና ሌላ አላስፈላጊ ጉዳት እንዳይደርስበት ወይም ክፍርድ በፊት ባለበት ሁኔታ ተከብሮ እንዲይ ለማድረግ የሚሰጡት ዋስትና የማቅረቢያ፣ የማስከበሪያ፣ የመያዣ እና የጊዜያዊ ማገጃ ትዕዛዞች በዋናው ጉዳይ የመጨረሻ ፍርድ እስከሚሰጥ ድረስ በተከራከሪ ወገኖች ላይ ወይም በአንደኛው ወገን ላይ የሚደርስን ወይም ሊደረስ የሚችልን ጉዳት እና እንግልት ለመቀነስ እና የፍትህ አሰጣጥን ሃደቱ’ን ለማቀላጠፍ ዓላማ ያላቸው መሆኑ ግልዕ ነው።
ሆኖም ግን ፍርድ ቤቱ በራሳቸው ምክንያት አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኙት ወይም ከላይ በተጠቀሱት የፍትሐ ብሔር ስነ-ስርዓት ህጉ ድንጋጌዎች መሰረት ከፍርድ በፊት የተሰጡትን የማገጃ ትዕዛዞች ላይ ቅሬታ የተሰማው ወይም ያላግባብ ነው የሚለው ወገን እግዱ እንዲነሳ፣ እንዲሻሻል ወይም እንዲሰረዝ ለፍርድ ቤቱ አቤቱታ ለማቅረብ ህጋዊ መብት ያላቸው ስለመሆኑ እና ፍርድ ቤቱም የቀረበው አቤቱታ በበቂ ምክንያት የተደገፈ መሆኑን በተረዳ ጊዜ ፍርድ ቤቱ ራሱ አስቀድሞ ሰጥቶ የነበረውን የእግድ ትዕዛዝ እንዲሻሻል፣ እንዲነሳ ወይም ጨርሶ እንዲሰረዝ ለማድረግ ስልጣን ያለው ስለመሆኑ በፍ/ብ/ስ/ስ/ህግ ቁጥር 158 ስር በግልጽ ተደንግጓል።
በመሆኑም ይህ ፍርድ ቤት ቀደም ሲል ጳጉሜ 04 ቀን 2016 ዓ/ም በዋለው ችሎት በኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቱ ስም በተለያዩ ባንኮች የተከፈተው የባንክ ሂሳብ እና የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ግንቦት 06ንቀን 2016 ዓ.ም እና ሰኔ 04 ቀን 2016 ዓ.ም ባደረጋቸው የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ያስተላለፈው ውሳኔ እና ያከናወነው የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ምርጫ ታግዶ እንዲቆይ የእግድ ትዕዛዝ የሰጠ ቢሆንም ከሳሾች ካቀረቡት የክስ ዓይነት እና ከተጠየቀው ዳኝነት አንጻር ስናየው ከሳሾች ከተስሳሾች ላይ የሚጠይቁት የገንዘብ ክፍያ በሌለበት ሁኔታ በ1ኛ ተከሳሽ ስም የተከፈተው የባንክ ሂሳብ ታግዶ የሚቆይበት በቂ የሆነ ህጋዊ ምክንያት አልተገኘም።
ከዚህ በተጨማሪም ከሳሾች ካቀረቡት የዳኝነት ጥያቄ አንጻር የኮሚቴው ጠቅላላ ጉባዔስብሰባ አጠራር ሕጋዊነትና ተቀባይነት፣ የውሳኔ አስተላለፍ ወይም አሰጣጥ ህጋዊና ተቀባይ እንዲሁም የተደረገው የኮሚቴው ስራ አስፈፃሚ አባላት ምርጫ ህጋዊነትና ውጤት በተመለከተ ወደፊት ጉዳዩን የሚመለከተው አካል አይቶ ተገቢውን የመቸረሻ ውሳኔ እስከሚሰጥ ድረስ በ1ኛ ተከሳሽ ስም በተለያዩ ባንኮች የተከፍተው የባንክ ሂሳብ ታግዶ እንዲቆይ መደረጉ የተቋሙ ህልውና መቀጠል እና አለመቀጠል ላይ የሚያስከትለው አሉታዊ ውጤት እንደተጠበቀ ሆኖ ተቋሙ የአገሪቱን መንግስትና ህዝብ በመወከል በተለያዮ መድረኮች ላይ በመገኘት የሀገሪቷን መብትና ጥቅም ለማስጠበቅ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ የሚከለከል በመሆኑ እና እግዱ ተነስቶ በጉዳዩ ላይ የቀረበው ክርክር መታየት የሚከለክለው በቂ የሆነ ህጋዊ ምክንያት የሌለ መሆኑን መረዳት ተችሏል፡፡
በአጠቃላይ 1ኛ ተከሳሽ ባቀረበው አቤቱታ ላይ የተጠቀሱትን ምክንያቶች ስናየው ተቋሙ በዓለም ዓቀፍ ኦሊምፒክ ቻርተርና ቻርተሩን ተከትሎ በጸደቀው የተቋሙ መተዳደሪያ ደንብ መሰረት የተቋቋመ እና ሀገራዊ የስፖርት ክንውኖችና እንቅስቃሴዎችን በበላይነት የሚመራ ነፃና ገለልተኛ ተቋም መሆኑን፣ እንዲሁም ተቋሙ በሀገር፤ በአህጉር እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ህገሪቷን በመወከል የሀገሪቷን ጥቅምና ጥሩ ስም ከፍ ለማድረግ የተጣለበት ኃላፊነት ለመጠጣትም ሆነ አጠቃላይ የዕለት ዕለት አስተዳደራዊ ስራዎችን እንዳይሰራ የሰራተኞች ደመወዝ፣ የተለያዩ አገልግሎት ክፍያዎች እንዳይፈፀም የሚያደርግ የእግድ ትዕዛዝ መሆኑን በመረዳት በአጠቃላይ በከሳሾች የቀረበው የክስ አቤቱታ በተመለከተ ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን ተቀብሎ የማየት ስልጣን ያለው መሆን አለመሆኑ፣ ከሳሾች ክሱን ለማቅረብ የሚያስችላቸው ህጋዊ ችሎታ፣ መብት እና ጥቅም ያላቸው ስለመሆነ እና አለመሆን እንዲሁም ጉዳዩ የክስ ምክንያት ያለው መሆን አለመሆኑ ፍርድ ቤቱ መደበኛ ስራው ሲጀምር በመደበኛ ችሎት ታይቶ ተገቢው ትዕዛዝ ወደ ፊት የሚሰጥበት መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ከዚህ ቀደም በ1ኛ ተከሳሽ ስም በተለያዩ ባንኮች የተከፈተው የባንክ ሂሳብ ላይ እንዲሁም ተቋሙ ከዚህ በፊት ግንቦት 6 ቀን 2016 ዓ.ም እና ሰኔ 04 ቀን 2016 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ ባስተላለፋቸው ውሳኔዎች እና ባደረጋቸው ምርጫዎች ህጋዊነት እና ተቀባይነት ጉዳዩ በሚመለከተው እና ስልጣን ባለው አካል ታይቶ የመጨረሻ ውሳኔ እስከሚሰጥ ድረስ ተቋሙ እና ተቋሙን የሚመሩ አካላት ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ እንዳያደርጉ እንዲሁም በተቋሙ ስም የተከፈተውን የባንክ ሂሳቦች እንዳያንቀሳቅሱ የተቀመጠው ክልከላ ከአጠቃላይ የሀገሪቷ እና የህዝቦቿ ጥቅምና ሙበት አንጻር አሉታዊ ተፅእኖ ያለው ሆኖ ስለተገኘ ይህ ፍርድ ቤት ከዚህ ቀደም የተሰጠው የእግድ ትዕዛዝ ቢነሳ በከሳሾች መብትና ጥቅም ወይም በክርክሩ አመራር ላይ የሚያስከትለው አሉታዊ ጉዳት አለመኖሩን መረዳት ተችሏል፡፡
በመሆኑም 1ኛ ተከሳሽ ባቀረቡት አቤቱታ ላይ የጠቀሷቸው ምክንያቶች በቂ እና ተቀባይነት ያላቸው ከመሆኑም በላይ ከሳሾች ካቀረቧቸው ዳኝነቶች አንጻር ገንዘብ ነክ የሆነ ለከሳሾች ሊክፈል የሚገባ የገንዘብ ጥያቄ በሌለበት ሁኔታ እንዲሁም ተቋሙ ያደረገው ስብሰባ ያስተላለፈው ውሳኔ እና ያከናወነው የስራ አስፈጻሚ አባላት ምርጫ ህጋዊነት፣ ተቀባይነት እና ውጤት አግባብ ባለው አካል ውሳኔ እስከሚሰጥበት ድረስ እንዲሁም በዋናው የክስ አቤቱታው ላይ በመደበኛ ችሎት ተገቢው ትዕዛዝ እስከሚሰጥ ድረስ ወይም በአጠቃላይ ጉዳዩ ላይ መደበኛ ክርክር ተደርጎ የመጨረሻ ዕልባት አስከሚሰጥበት ድረስ የእግዱ ትዕዛዝ ከፍተኛ የሆነ አሉታዊ ውጤት አለመኖሩን በመረዳት ይህ ፍርድ ቤት ቀደም ሲል ጳጉሜ 04 ቀን በዋለው ችሎት ያስተላለፋቸው ሁለቱም የማገሻ ትዕዛዞች በፍ/ብ/ስ/ስ/ህግ ቁጥር 158 መሰረት ሊነሳ ይገባል ተበሎ ብይን ተሰጥቷል።
ትዕዛዝ
- በዚህ መዝገብ ላይ ጳጉሜ 04 ቀን 2016 ዓ/ም በዋለው ችሎት በ1ኛ ተከሳሽ ስም በተለያዩ ባንኮች የተከፈቱት የባንክ ሂሳቦች ላይ እንዲሁም የተቋሙ አስተዳደራዊ ተግባራት እና እንቅስቃሴዎች ላይ የተላለፈው የእግድ ትዕዛዝ ሙሉ በሙሉ ተነስቷል። ይህ ትዕዛዝ እግዱ ስለመነሳቱ እንዲያውቁት እና ተገቢውን እንዲፈጽሙ ጉዳዩ ለሚመለከተው አካል ይተላለፍ፡፡
- በተሰጠው ብይንና ትዕዛዝ ላይ ቅሬታ ያለው ይግባኝ ማለት በህግ እንደተጠበቀ ነው
- ከሳሾች ያቀረቡት ዋናው የክስ አቤቱታ በተመለከተ ፍርድ ቤቱ መደበኛ ስራውን ሲጀምር መዝገቡ ለመደበኛ ችሎት ይቅረብ
- መዝገቡ ተዘግቷል። ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ።
የማይነበብ የዳኛ ፍርማ አለበት