ከነበረበት አስከፊ የጦርነት ሰቆቃ ሳያገገም ወደ ዳግም ምስቅልቅል የተሸጋገረው የአማራ ክልል ህዝብ ለመታደግ የሚያስችል ተስፋ መኖሩ ተሰማ። የአማራ ክልል የሰላም ካውንስል እንዳለው የሰላም ድርድር ለመጀመር የተስማሙ የፋኖ ኃይሎች አሉ። በቅርቡም ይህንኑ አቋማቸውን በግልጽ በመግለጫ ለሕዝብ ይፋ ያደርጋሉ። ይህን ዜና ተከትሎ የሰላም ንግግር እንዳይደረግ በውጭ የሚኖሩ የተለያዩ የፋኖ አደረጃጀቶችን እንደሚመሩ የሚናገሩ ከወዲሁ ድርድር እንዳይደረግ እየወተወቱ ነው።
በውይይትና በድርድር የሚያምኑ በርካታ ፋኖዎች አሉ እነርሱን አግኝተናል፣ ከእነርሱ ጋር ተነጋግረናል፤ ከአንዳንዶቹ ጋር ደግሞ ለመገናኘት ቀጠሮ ይዘናል፤ እነርሱም አንድ ኾነው አመራር ፈጥረው መግለጫ እንደሚሰጡንም ገልጸውልናል ብለዋል፡፡ አንድ ኾነው እንደሚመጡ የአማራ ሕዝብ ሰቆቃና ችግር መፍታት እንዲቻል የበኩላቸውን አስተዋጽዖ እንደሚያደርጉ የገለጹልንም አሉ
ዝግጅት ክፍላችን ስምምነታቸውን ያሳዩትን የፋኖ አደረጃጀቶች አስመልክቶ መረጃ ቢኖረውም ዝርዝር ከማቅረብ ይቆጠባል። በተለያዩ አደረጃጀቶች ስር በአገር ውስጥና በውጭ አገር ለተለያዩ አካላት ተጠሪ ሆነው የሚሰሩት ሃይሎች መካከል ለድርድር ይሁንታቸውን የገለጹት በመቶኛ ሰባ አምስት ከመቶ በላይ የሚሆኑት ናቸው። ይህ ስሌት ቀደም ሲል “የፋኖ ወኪሎች ነን” በሚል ለመንግስት ደብዳቤ ያስገቡትንና በውጭ የሚኖሩትን አያካትትም። ካውንስሉ እነዚህን ወገኖች ስለመቀበሉም ለጊዜው የታወቀ ነገር የለም።
በቅርቡ ይፋ እንደሆነው በአማራ ክልል ትምህርት መከታተል የቻሉ የክልሉ የነገ ተስፋዎች ሁለት ሚሊዮን አይሞሉም። ከዚህ አስደንጋጭ ዜና ጎንለጎን አምስት ሺህ የሚጠጋ ትምህርት ቤቶች ወድመዋል። ሰዎች በስለማ ወጥተው መግባት አልቻሉም። ግብርና ቀረጥ እየተጣለባቸው ስቃይ ላይ ናቸው። ክልሉ በወያኔ ወረራ ወቅት ከጎጃም በቀር ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ መሰረተ ለማቱ የወደመና ህዝቡ ክፉኛ በህይወትና በንብረት የተጎዳ በመሆኑ ድርድር እንደሚሻል ህዝብ በየመድረኩ ሲጠይቅ እንደነበር የሚታውስ ነው።
የአማራ ክልል እንደ ህዝብ ተፈርጆ ላለፉት ሰላሳ ዓመታት በደል የደረሰበት እንደሆነ ግልጽ መሆኑንን የሚገልጹ አሁን በተጀመረው ባለቤቱና መሪው በውል ያልታወቀ ትግል ይህ ህዝብ ፍትህ ሊያገኝ እንደማይችል ይጠቁማሉ። ይህን ትርምስ ተጠቅመው ሻዕቢያና ሌሎች ኃይሎች አገሪቱን ለማተራመስ እየሰሩ መሆኑንን በማስረጃ የሚጠቁሙ ወልቃይት ጠገዴን ወደ ቀደመው የእስር ዘመን ለመመለስ ያሴሩ የአማራን ክልል መተራመስ አጥብቀው እንደሚፈልጉት በማስረጃ አስደግፈው እየገለጹ ነው።
በበርካታ ምክንያቶች በአማራ ክልል ቅድሚያ ለድርድር የሚሰጥ አካሄድን መከተልና ለውጭ ኃይሎች መጠቀሚያ ከመሆን በመጠንቀቅ የህዝቡን በደል ለመሻር መስራት እንደሚገባ የሚያምኑ እንዳይናገሩ፣ አስተያየት እንዳይሰጡና አቋማቸውን እንዳያራምዱ በተለያዩ ሚዲያዎች “ባንዳ፣ ተከፋይ” የሚል ስም እየተሰጣቸው እንዲሸማቀቁ ማድረግን የትግል ስልት ያደረጉ፣ “የአማራን ህዝብ ሲኦልም ቢሆን ወርደን አመድ እናደርገርዋለን” ካሉ ኃይሎች ጋር አብረው መሰለፍን መርጠዋል። በተለይም የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላት ከሆነው ሻዕቢያ ጋር በቀጥታ ግንኙነት ፈጥረው በወልቃይት ጠገዴ ጉዳይ የክህደት ውል አስረው እየተማማሉ እንደሆነ በመረጃ እየተገለጸ ነው።
በእነዚህና በበርካታ ምክንያቶች ድርድር እንዳይጀመር፣ የአማራ ህዝብ ጥያቄ መልክና ደርዝ ይዞ እንዳይራመድ ውስጡን በአካባቢና በጎጥ በመከፋፈል ክልሉ ተተራምሶ አገሪቱ ወደ መፈረካከስ እንድታመራ ለሚሰሩ መገለገያ የሆኑ “ኢትዮጵያዊያን” መርዶ የሆነው የፋኖ ኃይሎች ለድርድር እየተስማሙ መሆናቸውን የሚገልጸው መረጃ ለመላው የአገሪቱ ህዝብ ተስፋን ይዞ የመጣ ነው።
ምንም ይሁን ምን አስቀድሞ በጠረጴዛ ዙሪያ በመነጋገር በሰጥቶ መቀበል መርህ መነጋገር ለማራ ክልል ወቅታዊ ቀውስ መፍትሄ እንደሆነ የሚያምኑ ዜናውን በበጎ ማየት ብቻ ሳይሆን ድጋፍ እንደሚሰጡትም ካውንስሉ ይፋ አድርጓል። የክልሉ ሚዲያ የሚከተለውን ዜና ዘግቧል።
የአማራ ክልል የሰላም ካውንስል በክልሉ ሰላም ለማምጣት የሚያበረታታ ጉዞ ላይ መኾኑን አስታውቋል፡፡ ካውንስሉ በክልሉ በግጭት ውስጥ የሚገኙ ወገኖችን ወደ ሰላማዊ ውይይት ለማምጣትና ችግሮቻቸውን በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ በሕዝብ የተመረጠና የተቋቋመ ነው፡፡ የሕዝብን ሰቆቃና ችግር ለመፍታት ተፋላሚ ወገኖች ሰላማዊ አማራጮችን እንዲጠቀሙ ጥረት እያደረገ ነው፡፡
የአማራ ክልል የሰላም ካውንስል ሠብሣቢ ያየህይራድ በለጠ የሰላም ካውንስሉ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ በርካታ ሥራዎችን መሥራቱን ተናግረዋል፡፡ የተቋቋመበትና በሕዝብ የተወከለበት ዋናው ዓላማ በመንግሥትና በፋኖ መካከል የተነሳውን አለመግባባትና ግጭት ለማስቆም፣ በግጭት የተጎዳውን ሕዝብ ሰቆቃ እንዲያበቃ ለማድረግ መኾኑን ነው የተናገሩት፡፡
ማኅበረሰቡ ግጭቶችና ጦርነቶች በውይይት ይፈቱ የሚል አቋም በመውሰዱ ሁለቱን ወገኖች ለማቀራረብ ብዙ ጥረት ተደርጓል ብለዋል፡፡ ችግሮችን በውይይት ለመፍታት የአማራ ክልል መንግሥት ርዕሰ መሥተዳድር በጎ ምላሽ መስጠታቸውንም አስታውቀዋል፡፡ የሰላም ካውንስሉ ከሰላም ሚኒስቴር ጋር ባደረጉት ውይይት ድርድሩን እንደሚቀበሉና በሰላማዊ ውይይት እንደሚያምኑ ገልጸውልናል ነው ያሉት፡፡
ችግሮችን በሰላም ለመቋጨት ተነሳሽነት እንዳላቸውና የሰላም ካውንስሉን ጥሪ እንደሚቀበሉ ገልጸውልናል ብለዋል፡፡ ሁለቱም ወገኖች ወደ ድርድር እንዲመጡ ዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ ጫና እንዲያደርግ እየሠሩ መኾናቸውንም አስታውቀዋል፡፡ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የሰላም ካውንስሉን ጥሪ እንዲቀበልና ድጋፍ እንዲያደርጉ ለማድረግ በሠሩት ሥራ ከአሜሪካ ኤምባሲ ጋር መወያየታቸውን ገልጸዋል፡፡ በውይይታቸው መልካም ነገሮችን ማግኘታቸውን እና የሰላም ካውንስሉ ለያዘው በጎ ተግባር ከጎናቸው እንደሚሰለፉ ማረጋገጣቸውን ነው የተናገሩት፡፡
የምሥራቅ አፍሪካ በይነ መንግሥት ድርጅት (ኢጋድ) ጋርም ውይይት ማድረጋቸውን አስታውቀዋል፡፡ ከኢጋድ ጋር ባደረጉት ውይይት ችግሩን ብቻችሁን የማትወጡት በመኾኑ የብዙ ድርጅቶች፣ የብዙ ድጋፍ ሰጪ ኃይሎች፣ የብዙ ተቋማት ድጋፍ ያስፈልጋችኋል፣ እኛም የሰላም ካውንስሉን እንደግፋለን ብለውናል ነው ያሉት፡፡ ከአፍሪካ ኅብረት ጋር ለመወያየት ቀጠሮ መያዛቸውንም አስታውቀዋል፡፡
ሌሎች ዲፕሎማቶችንና ተቋማትን በማነጋገር በአማራ ሕዝብ ላይ የተከሰተውን ችግር፣ በሕዝቡ ላይ እየደረሰ ያለውን ሰቆቃና መከራ ለመፍታት ሰፊ ሥራ መሥራት ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡ ለሰላም ካውንስሉ ሰፊ ድጋፍ እንደሚያስፈልገውም ገልጸዋል፡፡ የሃይማኖት ተቋማት ማኅበረሰቡን በማስተማር ሁለቱ ኃይሎች ላይም ጫና በማሳደር ለድርድር ዝግጁ እንዲኾኑ ለማድረግ ውይይት አድርገናል ነው ያሉት፡፡ የሰላም ካውንስሉ ከኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ባደረጉት ውይይት ድጋፍ እንደሚያደርጉላቸው፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ችግሩ እንዲፈታ፣ የአማራ ሕዝብ ሰቆቃና ለቅሶ እንዲያበቃ አብረዋቸው እንደሚሠሩ ቃል ገብተውልናል ነው ያሉት፡፡ የሰላም ካውንስሉ ችግሩ እንዲፈታ እየሠራ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡
“ያገኘናቸው የፋኖ ወንድሞቻችን አሉ” ያሉት ሠብሣቢው ያገኘናቸው ወንድሞቻችን ጥሩ ምላሽ ሰጥተውተናል ነው ያሉት፡፡ ሥራቸውን በስፋት እንዲሠሩ ምክረ ሃሳብ የሰጧቸው እንዳሉም ተናግረዋል፡፡ መንግሥት ቁርጠኛ ኾኖ ወደ ድርድር ለመግባቱ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ተወያይታችኋል ወይ? የሚል ጥያቄ ጠይቀውናል፤ እኛም ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በቅርቡ መገናኘት እንድምንችልና ከእርሳቸው ጋር እንደምንወያይ ገልጸንላቸዋል ነው ያሉት፡፡
በውይይትና በድርድር የሚያምኑ በርካታ ፋኖዎች አሉ እነርሱን አግኝተናል፣ ከእነርሱ ጋር ተነጋግረናል፤ ከአንዳንዶቹ ጋር ደግሞ ለመገናኘት ቀጠሮ ይዘናል፤ እነርሱም አንድ ኾነው አመራር ፈጥረው መግለጫ እንደሚሰጡንም ገልጸውልናል ብለዋል፡፡ አንድ ኾነው እንደሚመጡ የአማራ ሕዝብ ሰቆቃና ችግር መፍታት እንዲቻል የበኩላቸውን አስተዋጽዖ እንደሚያደርጉ የገለጹልንም አሉ ነው ያሉት፡፡
በቅርቡ በመግለጫ የተደገፈ ለድርድሩ ይሁንታቸውን እንዲሰጡ ጠይቀናል፤ እነርሱም ይሁንታቸው በመግለጫ አስደግፈው እንደሚገልጹ ይሁንታቸውን ሰጥተዋል፣ በቅርቡም ይህን እንደሚያደርጉ እንጠብቃለን ብለዋል፡፡ የሰላም ካውንስሉ የሚያበረታታ ጉዞ ላይ መኾኑንም አስታውቀዋል፡፡
ውስጣዊ ችግራችንን ፈትተን፣ አንድ ኾነን፣ የአማራ ክልል ምጣኔ ሃብታዊ እና ማኅበራዊ ልማቱን እንዲያመጣ፣ የሕዝብ ስቃይና ጉስቁልና እንዲያቆም መሥራት ይጠበቃል ነው ያሉት፡፡ የአማራ ሕዝብ ቀደም ሲልም ጦርነቶች ያልተለዩት መኾኑን ያነሱት ሠብሣቢው ከነበረበት አስከፊ ጦርነት እና ሰቆቃ ሳይላቀቅ ወደ ሌላ ሰቆቃ ውስጥ መግባቱን ነው የተናገሩት፡፡
አሁን ካለበት ሰቆቃ ማላቀቅ ግድ ይላልም ብለዋል፡፡ ይህ የሚቻለው ደግሞ በልጆቹ፣ ተጽዕኖ በሚፈጥሩ ኃይሎች፣ ወጣቶች፣ ምሁራንና ሌሎች ትብብር መኾኑን ነው የተናገሩት፡፡ ችግሩን በውይይት እና በንግግር መፍታት እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል፡፡ ችግሩ የአንድ ወቅት ችግር ብቻ አለመኾኑንና ቀጣዩን ትውልድም የሚፈታተን መኾኑን ነው ያመላከቱት፡፡ ችግሩን ለመፍታት የሁሉንም ወገን ርብርብና ድጋፍ እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል፡፡ ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የሃይማኖት ተቋማት በአስተምህሮቶቻቸው መሠረት መገሰጽ፣ ያጠፋን መቆጣት፣ አስተምህሮቱን በሚገባ ማስረጽ መገዳደልን ማውገዝና ሰላምን መስበክ ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት፡፡ መገዳደል እንደቀላል፣ ፋሽን የሚታይበት፣ በአንጻሩ እንደነውር የማይታይበት ወቅት መኾኑን ገልጸዋል፡፡ “በማኅበረሰቡ ውስጥ ያለውን ሰቆቃ እንደቀላል ማየት ተገቢ አይደለም” ብለዋል፡፡ የሃይማኖት ተቋማት ግዴታቸውን መወጣት እንደሚጠበቅባቸውም አመላክተዋል፡፡
ያለፈው ችግር፣ ያለፈው ሰቆቃ፣ ለቅሶና ውድመት ይብቃ ብለዋል፡፡ ችግሮቹን ለመፍታት ነገሮችን በሰፊው ማየት እንደሚያስፈልግም አመላክተዋል፡፡ የአማራ ክልል ችግር ታሪካዊ ጠላቶች ጭምር እጃቸውን ዘርግተው የሚጠብቁት፣ የአማራ ሕዝብ እርስ በእርስ እንዲዋጋ፣ የአማራ ወጣት እንዲያልቅ የሚፈልጉት መኾኑንም አመላክተዋል፡፡ ሁሉም ሰው የመፍትሔው አካል እንዲኾን ደጋግመን ጥሪ እናቀርባለን ነው ያሉት፡፡