‘እንከን የሌለው’ የሚባለው የሴት ልጅ የመራቢያ አካል (ብልት) ምን ይመስላል? ጠረኑስ ምን መሆን አለበት? የሚለው ጉዳይ በመላው ዓለም ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ መነጋገሪያ ሆኗል።
በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች የተመለከቷቸው የማኅበራዊ ሚዲያ ምሥሎች እና ተንቀሳቃሽ ምሥሎች የሴቶች ብልት ቅርፅ እና ጠረን ለመለወጥ ጥቅም ላይ መዋል ያለባቸው ምርቶችን ያስተዋውቃሉ።
የሴቶች የሥነ ተዋልዶ ጤና ባለሙያዎች እነዚህን ምርቶች ሴቶች እንዳይጠቀሙ እያስጠነቀቅ ነው።
እነዚህ ምርቶች በሴቶች ብልት ላይ ያለውን ተፈጥሯዊ ጤናማ ይዘትን (ፒኤች) እንደሚያዛቡ እና ለኢንፌክሽን እንደሚያጋልጡ ባለሙያዎቹ ተናግረዋል።
የሴቶች ብልት የራሱ የሆነ ተፈጥሯዊ አቀማመጥ ያለው ሲሆን፣ ሰው ሠራሽ ንጥረ ነገሮችን መጠቀም ይህንን እንደሚያዛባ የሴቶች የሥነ ተዋልዶ ሐኪም ሙጅድጉል ዛይፎግሉ ካራካ ትናገራለች።
“ለመጀመሪያ ጊዜ ‘የብልት ሽቶ’ የሚባል ስሰማ ደነገጥኩ። ለወንዶች ብልት ሽቶ የለም። ለምን ለሴቶች ብልት ብቻ ሽቶ አስፈለገ?” ስትልም ትጠይቃለች።

በኢስታንቡል ተማሪ የሆነችው ኢዩል ጉልስ ካራ፣ ሴቶች በማኅበራዊ ሚዲያ አማካይነት በሚደረግባቸው ጫና ተሰላችታለች።
“ማኅበረሰቡ የሚጠብቅብንን እንድናደርግ በየጊዜው ጫና አለ። አሁን ደግሞ ብልታችሁ ‘በጣም ጠቁሯል’ እየተባል ነው?” ትላለች።
‘የተስተካከለ የሚባል ብልት የለም’
የሕክምና ባለሙያዎች ‘የተስተካለ’ ወይም ‘ፍጹም’ የሚባል የሴት ልጅ ብልት ዓይነት እንደሌለ ይናገራሉ።
ለንደን ውስጥ በሚገኘው ጠጽንስ እና የማህጸን ሮያል ኮሌጅ የሚሠሩት ቤሪን ታዝካን፣ “የሁሉም ሴት ብልት የተለያየ ነው” ይላሉ።
“የየትኛዋም ሴት ብልት ከሌላ ሴት ብልት ጋር በቅርፅ፣ በመጠን እና በጠረን የተለያየ ነው” ሲሉም ያስረዳሉ።
ታካሚዎች ‘ብልቴ የሆነ ችግር አለበት’ ብለው ወደ ሕክምና እንደሚሄዱ ገልጸው፣ “ታካሚዎች ብልቴ የሆነ ችግር አለበት ብለው ሲመጡ ምንም ችግር እንደሌላቸው እነግራቸዋለሁ። ሰውነታቸው አንዳችም ችግር እንደሌለበት ሲሰሙ 90 በመቶው እፎይታ ይሰማቸዋል” በማለት ያብራራሉ።
በአንዳንድ አገሮች ግን ሴቶች የሥነ ተዋልዶ ጤና ባለሙያ ማማከር የማይችሉበት ሁኔታ ውስጥ ይገባሉ።
ለምሳሌ በኢራን የሴቶች የሥነ ተዋልዶ ጤና ክትትል ማድረግ እንደ አሳፋሪ ነገር ይወሰዳል። ስለዚህም ስለ ሴቶች ብልት ማውራት አይዘወተርም።
አንዳንድ የጤና ባለሙያዎች ሴቶችን ሀፍረት እንዲሰማቸው በማድረግ ይወቀሳሉ።
አንድ የኤክስ ተጠቃሚ “አንድ ጓደኛዬ የብልትን ውስጣዊ ከንፈር የሚቀንስ ቀዶ ሕክምና (labiaplasty) አድርጋለች። ለምን እንደዚህ ዓይነት ምቾት የሚነሳ ቀዶ ሕክምና አደረግሽ? ብለን ጠይቀናታል” ስትል አስተያየቷን ሰጥታለች።
ቀዶ ሕክምናውን ያደረገችው ጓደኛዋ “ቀዶ ሕክምናውን ያደረግኩት የሥነ ተዋልዶ ጤና ሐኪሜ የብልቴ ውስጣዊ ከንፈር ለምን አስቀያሚ እንደሆነ ስለጠየቀኝ ነው። የብልትሽ ውስጣዊ ከንፈር ትልቅ እና አስቀያሚ ነው አለኝ። ለምን የማህጸንሽ በር ትልቅ ሆነ? ብሎኛል። በተፈጥሯዊ መንገድ መውለድ ከፈለግሽ ቀዶ ሕክምና አድርጊ አለኝ” ስትል ነበር ምላሽ የሰጠችው።
ይህ የቀዶ ሕክምና የሴት ልጅ ብልትን ለማስተካከል የሚደረግ ሲሆን፣ በተለይም በወጣቶች ዘንድ በፍጥነት እየተስፋፋ መጥቷል።
የብልት ከንፈር ቆዳን ማጠፍን ጨምሮ የተለያዩ የብልት ክፍሎችን ቅርፅ የሚለውጥ ቀዶ ሕክምና ነው።
ብልት መጠኑ እያደገ ስለሚሄድ ከ18 ዓመት በታች ያሉ ሴቶች ይህንን ቀዶ ሕክምና እንዲያደርጉ አይመከርም።
ከንጽህና እንዲሁም የግብረ ሥጋ ግንኙነት ሲፈጸም ወይም አካል ብቃት እንቅስቃሴ ሲደረግ ምቾት የማይሰማቸው ሴቶች እንደ ሕክምና አማራጭ የሚወስዱት ነው።
ሆኖም ግን የብልት ቅርፅን ለመለወጥ በሚል ምክንያት ብቻ ቀዶ ሕክምናውን የሚያደርጉ እየተበራከቱ መጥተዋል።
የብልት ቅርፅን ‘የሚያስተካክለው’ ቀዶ ሕክምና
በቅርቡ በወጣ ሪፖርት መሠረት በአውስትራሊያ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ሰዎች ይህንን ቀዶ ሕክምና አድርገዋል ወይም ለማድረግ አስበዋል።
ዊሜንስ ኽልዝ ቪክቶሪያ የተባለው መጽሔት ባለፈው ሰኔ ወር ከ18 እስከ 50 ዓመት ያሉ 1,030 ሴቶችን መረጃ ተመርኩዞ ዘገባ አውጥቷል።
ዘገባው እንደሚለው፣ ሴቶች ይህንን ቀዶ ሕክምና እንዲያደርጉ ጫና የሚያሳድሩት ልቅ የወሲብ ፊልሞች እና ማኅበራዊ ሚዲያ ናቸው።
“የሴቶች ብልት ምን መምሰል አለበት የሚለውን የተዛባ ምልከታ እየፈጠሩ ያሉ ምሥሎች እና ቪድዮዎች ሴቶች ቀዶ ሕክምናውን ለማድረግ እንዲነሳሱ አድርገዋል” ይላል ዘገባው።

ዓለም አቀፍ ቀዶ ሕክምናዎችን የሚመዘግበው ኢንተርናሽናል ሶሳይቲ ኦፍ ኤስተቲክ ፕላስቲክ ሰርጀሪ ባወጣው ሪፖርት መሠረት፣ የብልት ቅርፅ ማስተካከያ ቀዶ ሕክምና እአአ በ2019 ከነበረው በ2023 ዓመት በ14.8% ጨምሯል።
ከፍተኛ ቁጥር የተመዘገበው በብራዚል ሲሆን፣ 28,000 ሰዎች ቀዶ ሕክምናውን አድርገዋል።
የቀዶ ሕክምና ባለሙያ ረኔታ ማጋላህስ “ብራዚላውያን ሴቶች ስለ ገፅታቸው በመጨነቅ ቀዶ ሕክምና ያደርጋሉ” ትላለች።
የ27 ዓመቷ ብራዚላዊት የጡንቻ ማፈርጠም አትሌት ቫል ሳንታና የብልት ቀርፅ ማስተካከያ ቀዶ ሕክምና አድርጋለች።
“ቀዶ ሕክምናውን ለማድረግ የወሰንኩት ከስድስት ዓመት በፊት በገጠመኝ ነገር ምክንያት ነው። በወቅቱ የጡንቻ ማፈርጠም ስፖርት ጀምሬ ስቴርዮይድ እወስድ ነበር” ትላለች።
ቦልዴኖን እና ኦክሳንድሮልን በተባሉት መድኃኒቶች ምክንያት ብልቷ ላይ የመጠን መጨመር እንደተከሰተ እና በዚህ ምክንያት የግብረ ሥጋ ግንኙነት ስትፈጽም ምቾት ይነሳት እንደነበር ተናግራለች።
የቀዶ ሕክምና ተሞክሮዋን በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ስትገልጽ ቀዶ ሕክምናው በራስ መተማመን እና የተሻለ ሕይወት እንደሰጣት ተናግራለች።
ስጋቶች
ይህንን ቀዶ ሕክምና ከማድረግ በፊት ከግምት ውስጥ መግባት ያለባቸው ነጥቦች እንዳሉ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
የዩናይትድ ኪንግደም ብሔራዊ ጤና ማዕከል “ቀዶ ሕክምናው ጉዳት ሊያስከትል የሚችልና ውድ ነው። የምትፈልጉትን ውጤት ለማግኘታችሁ ማረጋገጫም የለም። ስለ ሰውነታችሁ ያላችሁን አመለካከት ላያሻሽለው ይችላል” ይላል።
ቀዶ ሕክምናው መድማት፣ ኢንፌክሽን፣ የሰውነት ጠባሳ፣ የብልት ስሱነት እና ሌሎችም ከቀዶ ሕክምና ጋር ተያይዘው የሚመጡ የደም መርጋትና አለርጂን የመሰሉ ጎንዮሽ ጉዳቶችን ሊያስከትል እንደሚችል ተገልጿል።
“አንዳንድ ሴቶች ቀዶ ሕክምናውን የሚያደርጉት የብልታቸውን ቅርፅ ስለማይወዱት ነው። ሆኖም ግን ብልት ላይ የቆዳ መሸብሸብ ወይም ሌላም ቅርፅ ፍጹም ተፈጥሯዊ ነው” ሲልም ተቋሙ ያስጠነቅቃል።
የሥነ ተዋልዶ ሐኪም ሙጅድጉል ዛይፎግሉ ካራካ፣ ሴቶች ስለ ብልታቸው ማወቅ እንዳለባቸው እና ብልታቸው በተፈጥሮው ባለው ሁኔታ መቀበል እንዳለባቸው ትናገራለች።
ተማሪዋ ኢዩል ጉልስ ካራም በዚህ ትስማማለች።
“የሴት ብልት ቀዶ ሕክምና ወይም ቅባት የሚያስተዋውቁትን በመቃወም፣ ማኅበራዊ ሚዲያን በመጠቀም ስለ ሴቶች የሥነ ተዋልዶ ጤና ግንዛቤ መፈጠር አለብን። ከሴቶች ላይ አላስፈላጊ ጫናን ማስወገድ አለብን” ትላለች።
ዘገባው BBC Amharic