ኦሊምፒክ በተጠናቀቀ በሁለት ሳምንታት በፔሩ ሊማ በተካሄደው የዓለም ከ20 ዓመት በታች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አንደኛ ከዓለም ደግሞ ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቀቀች፡፡ ውጤቱ በኦሊምፒክ ውጤት የተበላሸበትን ቁልፍ ምክንያት ያጋለጠ ሆኗል።
በውድድሩ የተሳተፉ ወጣት አትሌቶች፣ ወደ ውድድር ተሸኙ ተብሎ ከተዘገበው ውጪ ሌላ የተሰማ መረጃ አልነበረም፤ ውድድሩ ከተጀመረ በሁዋ ወርቅ ሲያገኙና የሜዳሊያቸው ብዛት ሲበረከት ዜና ሆኑ። ዜናው ግን መግነን ባለበት ደረጃ በድል ዜናና መዝሙር አልታጀበም። ተተኪ ላይ ትኩረት እንዲደረግ አውቀውም ይሁን ሳያውቁ የጮሁ አልተነፈሱም።
አንዳምዶች እንደሚሉት በኦሊምፒክ ውጤት መጥፋት የተበሳጩ ወይም የተበሳጩ መስለው የነበሩ በዩቲዩብ፣ በማህበራዊ ገጾቻቸው ወይም በዜና አውታሮቻቸው አድናቆት አልሰጡም። እንደውም በኦሊምፒክ ውድድር ወቅት አላማ ይዘው ውድቀትን ስለሰበኩ በተገኘው ውጤት ያዘኑ መስለዋል። ወይም ስድብና ውርጅብኝ ባወረዱ በሳምንቱ ማድነቅ ልፋታቸውን እንደሚያበላሽ ቆጥረውታል።
በሌላ በኩል ሚዲያውም ሆነ አክቲቪስቶች የራሳቸው በሆነ ምክንያት ዝም ማለታቸው፣ ልክ ኦሊምፒክ ተወዳዳሪዎች ላይ እንደሆነው ተጽዕኖ እንዳያሳድርባቸው አድርጓል በሚል እንደ በረከት ተወስዷል። አንዱን ሾሞ ሌላውን ለማውረድ ሲባል ውድድር ሊጀመር ሲል እንደ ባዕድ አገር ወኪል በራሳቸው አገር ሚዲያዎችና ዜጎች ውርጅብኝ የወረደባቸው የኢትዮጵያ ፓሪስ ኦሊፕሚክ ተሳታፊ አትሌቶች ብቃት እንዳላቸው በሳምንት ልዩነት አሳይተዋል። በተመሳሳይ በዲያመንድ ሊግ ውድድሮች ያሳዩት የማሸነፍ ብቃት በጫና ውስጥ እንደነበሩ የሚያረጋግጥ እንደሆነም ተመልክቷል።
ፓሪስ የኦሊምፒክ መንደር ድረስ እየተደወለ ሴራ ሲመረትባቸው የነበሩ አትሌቶች ያሳለፉት የመከራ ጊዜ እንደነበር የጠቆሙ፣ ያሉትን ችግሮች ከውድድር በሁዋላ ወይም፣ አስቀድሞ ገና በጊዜ አንስቶ መነጋገር ሲቻል፣ ውድድር ሲጀመር በዘመቻ መልክ ድርጅት ፈጥሮ የተወዳዳሪዎችን ሞራል መንካት ዛሬም ባይሆን አድሮ በሰለባዎቹ ይፋ እንደሚሆን ፓሪስ ሆነው ህየታዘቡ ገለልተኛ አካላት መናገራቸው ይታወሳል። ይህን ያሉ ወገኖች አንዱን የመደገፍ ወይም የማጣታል ዓላማ እንደሌላቸው ገልጸን በወቅቱ መዘገባችን ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች አትሌቲክስ ብሔራዊ ቡድን በውድድሩ÷ 6 የወርቅ፣ 2 የብር እና 2 የነሐስ በአጠቃላይ 10 ሜዳሊያዎችን ያገኙት ከዓለም አገራት ጋር ተወዳድረው ነው። የተበለጡት በአሜሪካ ብቻ ነው። ይህ ኢትዮጵያ ታላቅ የአትሌት ምንጭ ያላትና አስተዳደራዊ ታታዎች ከተስተካከሉ ወደ ነበርንበት ድል በሁሉም አደባባይ መመለስ እንደምንችል የሚያሳይ ነው። ይህን ውጤት በዘፈንና በልዩ ሁኔታ አድንቆ እውቅና አለመስጠት ንፉግነት ብቻ ሳይህን የቀድሞውን ጪኸት ዋና ምክንያት አጉልቶ ያሳያል። ስልጣን !!
በውጤቱ አትሌት መዲና ኢሳ በ5 ሺህ ሜትር፣ ሲምቦ ዓለማየሁ በ3 ሺህ ሜትር መሰናክል፣ ጀነራል ብርሃኑ በ800 ሜትር፣ አለሺኝ ባወቀ በ3 ሺህ ሜትር፣ ሳሮን በርሀ በ1 ሺህ 500 ሜትር እና አብዲሳ ፈይሳ በ1 ሺህ 500 ሜትር የተሳተፉበትን ውድድር በበላይነት በማጠናቀቅ የወርቅ ሜዳሊያዎችን አስገኝተዋል፡፡
በተጨማሪም አትሌት መቅደስ ዓለምእሸት እና አብዲሳ ፈይሳ በ5 ሺህ ሜትር የብር እንዲሁም አትሌት ማርታ ዓለማየሁ በ3 ሺህ ሜትርና ኃይሉ አያሌው 3 ሺህ ሜትር መሰናክል የነሐስ ሜዳሊያ ለሀገራቸው ማስገኘት ችለዋል፡፡
ከ134 ሀገራት ተሳትፈው 34 ሀገራት ብቻ በሜዳሊያ ሰንጠረዥ በገቡበት ሻምፒዮና÷ ኢትዮጵያ ከዓለም አሜሪካን በመከተል በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ሁለተኛ እንዲሁም ከአፍሪካ አንደኛ ደረጃ በመያዝ ውድድሩን ማጠናቀቅ ችላለች፡፡
ከሁለት ዓመት በፊት በኮሎምቢያ ካሊ በተካሄደው የዓለም ከ20 ዓመት በታች አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ6 ወርቅ፣ 5 ብር እና 1 ነሐስ በአጠቃላይ 12 ሜዳሊያዎችን በማግኘት ከዓለም 3ኛ ደረጃ ይዛ ማጠናቀቋ ይታወሳል፡፡