የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኤርትራ / አስመራ የሚያደርገውን በረራ ከነገ ነሐሴ 28 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ማቋረጡን ይፋ ሲያደርግ እንዳስታወቀው ኤርትራን እያስተዳደረ ያለው ሻዕቢያ በአስመራ ባንክ ያስቀመጠውን ገንዘብ እንዳያንቀሳቅስ እንዳገደው ተናግሯል። ዜናውን የሰሙ ወገኖች ” አየር መነዳችን ተዘረፈ” ሲሉ ድምጻቸውን አሰምተዋል።
አየር መንገዱ በረራውን ያቋረጠው በኤርትራ ውስጥ አገልግሎቱን ለመስጠት ባጋጠመው ከአቅም በላይ በሆነ የአሰራር ችግር ሳቢያ መሆኑን ያስታወቀው በዋና ስራ አስፈጻሚው አቶ መስፍን ጣሰው አማካይነት ነው።
ዋና ስራ አስፈሳሚው ቀንና የደብዳቤ ልውውጥ ይዘቶችን በመዘርዘር ከኤርትራ አቪዬሽንም ሆነ ባንክ ህጋዊ ምላሽ እንዳልተሰጣቸው ያብራሩበት አግባብ እጅግ ጨዋነት የተመላበት እንደሆነ ተመልክቷል።
የአቶ መስፍን ጣሰውን ዝርዝር መግለጫ ያደመጡ “ይህ ወረበላ መንግስት ከፍጥረት እስከ እርጅናው በተራ ማጭበርበርና ዘረፋ ይኖራል?” በሚል የትዝብት አስተያየት እየሰጡ ነው።
ለቀረበላቸው የተለያዩ ጥያቄዎች መልስ ያልሰጡት፣ ህጋዊ የአየር መንገዱን ገንዘብን ለማንቀሳቀስ ያለ አንዳች ህጋዊ ማብራሪያ እገዳ ያጣሉት የኤርትራ ባለስልጣናት አየር መንገዱ ላቀረበው የህግ ጥያቄም በረራውን ማቆም ተከትሎ በይፋ ያሉት ነገር የለም። ይህንኑ ዝምታ “ምን አበሳጭቷቸው ነው በዚህ ደረጃ መንግስታዊ ሽፍታ የሆኑት?” ያሉ አሉ።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ አስመራ የሚያደርገውን በረራ ለማቋረጥ ውሳኔ ላይ ከመድረሱ በፊት በተደጋጋሚ የእንነጋገር ጥያቄ አንስቶ እንደነበር ዋና ስራ አስፈጻሚው ሲገልጹ ድርጅታቸው በውሳኔው ማዘኑን አመልክተዋል። ኤርትራዊ ደንበኞቻቸውንም ይቅርታ ጠይቀዋል።
አየር መንገዱ በኤርትራ አገልግሎቱን ለመስጠት ባጋጠመው ከአቅም በላይ በሆነ የአሰራር ችግር ከዚህ ውሳኔ ላይ መድረሱ ተገለጋዮችን አሳዝኗል። ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ግብጽና ሶማሌን እጅበው በይፋ ጸረ ኢትዮጵያ እንቅስቃሴ ውስጥ መግባታቸው ይፋ እንደሆነ ነበር አየር መንገዱን መጎንተል የጀመሩት።
በኢትዮጵያ አየር መንገድ ለመብረር ትኬት የቆረጡ መንገደኞች ያለምንም ተጨማሪ ወጪ በሌሎች አየር መንገዶች ጉዟቸውን እንዲያደርጉ ጥረት እንደሚያደርግ ያስታወቀው አየር መንገዱ፣ ” የትኬት ገንዘብ ይመለስልን ” የሚሉ ካሉም ገንዘባቸውን ተመላሽ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ገልጿል። ወደ አስመራ በረራ በማቋረጡ ምክንያት ለሚፈጠረው መጉላላት አስቀድሞ ይቅርታ ጠይቋል።
ቤተሰቦቻቸውን አዲስ አበባ አስቀምጠው የሚረዱ የኤርትራ ተወላጅ ዴያስፖራዎች አስቀድሞም ቢሆን ፍርሃቻው እንደነበራቸው ገልጸው በሰሙት ዜና ማዘናቸውን አመልክተዋል። በይፋ አስተያየት ለመስተት ግን አልፈለጉም።
ከአዲስ አበባ ወደ አስመራ የሚጓዙ የኤርትራ ተወላጆች የምግብ ፍጆታን ጨምሮ ቁሳቁስ በስፋት ወደ አስመራ ያግዙ እንደነበር የጉምሩክ ሰራተኞች ይገልጻሉ።
ኢትዮሪቪውን በቴሌግራም ይከተሉ – https://t.me/+f_kxmaPjD-9jYTdk‘