ዝርዝሩ ይፋ ባይሆንም የግብጽ አውሮፕላኖች መሳሪያ ጭነው ሶማሊያ መድረሳቸውን ዓለም ዓቀፍና በቀጣናው ያሉ ሚዲያዎች ማስታወውቃቸው አይዘነጋም። ኢትዮጵያም አካሄዱ ብሄራዊ ስጋት መሆኑን ጠቅሳ ተቃውማ ነበር። ዛሬ ሮይተርስ እንዳለው የግብጽ መርከብ መሳሪያ ጭና ሞቃዲሾ ማድረሷን ባለስልጣን ጠቅሶ ማረጋገጫ ዜና አሰራጭቷል።
ግብጽ የጦር መርከቧን ትርጠቅማ ወደ ሶማሊያ ያገባችው የጦር መሳሪያዎች ፀረ አውሮፕላን ሚሳኤሎች፣ መድፎች እና ሌሎች አነስተኛ የጦር መሳሪያዎች መሆናቸውንና ሌላም ተጨማሪ እንደሚጠብቁ ባለስልጣኑ አስታውቀዋል።
ለቢቢሲ ሶማሊኛ የተናገሩት ባለሥልጣን ባለፉት ቀናት በመርከብ ተጭነው ወደ ሞቃዲሾ ወደብ የደረሱት የጦር መሳሪያዎች የሶማሊያ መንግሥት ጦር የሚታጠቃቸው መሆኑን አመልክተዋል።
ኢትይጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የባህር በር ስምምነት ካደረገች በሁዋላ ግብጽ አጋጣሚውን ተጠቅማ የሞቃዲሾን መንግስት ለመርዳት ወታደራዊ ስምምነት ካደረጉ በሁዋላ መሳሪያ በይፋ ወደ መሞቃዲሾ ሲገባ በሚታወቅ ደረጃ ይህ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።
ይህንን ከፍተኛ መጠን ያለውን የጦር መሳሪያ በሞቃዲሾ ወደብ በኩል ወደ ሶማሊያ መግባቱን በተመለከተም የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን እየዘገቡ ሲሆን፣ በተለያዩ የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች ላይም ይህንን የሚያሳዩ ምሥሎች ተሰራጭተዋል።
በርካታ የሶማሊያ መገናኛ ብዙኃን የጦር ማሳሪያዎቹ ወደ ሞቃዲሾ ወደብ ደርሰው የተራገፉት በግብፅ መርከብ አማካኝነት መሆኑን ዘግበዋል። በማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች ላይ ከትናንት እሁድ ጀምሮ የተለያዩ ዓይነት ያላቸው ከባድ መሳሪያዎች እና በጭነት መኪና ተሸፍነው የሚጓዙ ወታደራዊ ቁሶች በሞቃዲሾ ጎዳናዎች ላይ ሲተላለፉ ታይተዋል።
ቢቢሲ ሶማሊኛ ያነጋገራቸው የሶማሊያ መንግሥት ባለሥልጣን አሁን ከገባው የጦር መሳሪያ ጭነት በተጨማሪ በቀጣይነት ታንኮችን እንደሚጠብቁ ገልጸዋል።