የኢራን አብዮታዊ ዘብ ፔጀር እና ዎኪ ቶኪ የተባሉት የአሌክትሮኒክስ መሳሪያዎች በአባላቱ ጥቅም ላይ እንዳይውሉ ማገዱ ተገለፀ፡፡ ክልከላው በግንኙነት መሳሪዎች ፍንዳታ ምክንያት በርካታ የሂዝቦላህ ታጣቂ ቡድን አባላትና አመራሮች ለሞት እና ለአካል ጉዳት መዳረጋቸውን ተከትሎ መሆኑ ተነግሯል።
የኢራን ከፍተኛ የደህንነት ባለስልጣናት ለሬውተርስ እንደተናገሩት÷ በሀገር ውስጥ የተመረቱ እንዲሁም የቻይና እና ሩሲያ ሰራሽ የግንኙነት መሳሪያዎች በኢራን አብዮታዊ ዘብ ጥቅም ላይ ይውሉ ነበር፡፡
ለእስራኤል የሚሰሩ ሰዎች ወደ ኢራን ሰርገው ሊገቡ እንደሚችሉ እና ይህም የኢራን የደህንነት ስጋት በመሆኑ የመገናኛ መሳሪያዎቹን የመፈትሽ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በተጨማሪም የአብዮታዊ ዘቡን አመራሮች መሰረት ያደረገ ፍተሻ እየተከናወነ ጠቅሰው÷ አባላቱ በሀገር ውስጥ እና በውጭ ያላቸውን የባንክ ሂሳብ፣ የጉዞ ታሪክ እና የቤተሰቦቻቸውን ሁኔታ የመመርመር ስራ እየተከወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ቀደም ሲል በሂዝቦላህ አባላት በብዛት ጥቅም ላይ ይውሉ የነበሩት የፔጀር እና ወኪ ቶኪ የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎች በተመሳሳይ ሰዓት በሊባኖስ መፈንዳታቸውን ተከትሎ 12 የሂዝቦላህ አባላትን ጨምሮ 39 ሰዎች ለህልፈት ተዳርገዋል፡፡
በሌባኖሱ ታጣቂ ቡድን ሂዝቦላህ ላይ ያነጣጠረው የመገናኛ ሬዲዮ እና የኤሌክትሮኒክስ መሳሪዎች ጥቃት በመካከለኛው ምስራቅ ቀጣና አዲስ ውጥረት መቀስቀሱ አይዘነጋም።
በሌባኖስ ፔጀርና ዎኪ ቶኪ የተሰኙ ሂዝቦላህ በብዛት የሚጠቀማቸው መገናኛ መሳሪያዎች መፈንዳታቸውን ተከትሎ ከ20 በላይ ሰዎች ሲሞቱ ከ3 ሺህ በላይ የሚሆኑት ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡
ከሞቱት ውስጥ ከ8 በላይ የሚሆኑት የሂዝቦላህ አባላት ሲሆኑ÷በሌባኖስ የኢራን አምባሳደር ሞይታባ አሚኒ በፍንዳታው አንድ አይናቸውን ማጣታቸው ተሰምቷል፡፡
በደህንነት ካሜራዎች የተቀረፁ ምስሎች በሌባኖስ፣ ሶሪያና ቤሩት በእንቅስቃሴ ላይ የነበሩ ሰዎች ሲጠቀሙባቸው የነበሩት የፔጀርና ወኪ ቶኪ መሳሪያዎች በድንገት ሲፈነዱ ያሳያሉ፡፡
ጥቃቱን ፈጽማለች በሚል የተወነጀለችው እስራኤል እስካሁን ስለ ጉዳዩ ያለችው ነገር አለመኖሩ የተመላከተ ሲሆን÷ ለአሜሪካ ግን በጥቃቱ ዙሪያ ገለጻ ማድረጓ ተጠቁሟል፡፡
በአንጻሩ የሌባኖስ የደህንነት ምንጮችየእስራኤሉ የስለላ ተቋም ሞሳድ በኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎቹ ላይ በቀላሉ የማይመረመር እና ኮድ የሚቀበል ፈንጅ ቀብሮ ነበር ሲሉ ወንጅለዋል፡፡
የምርቶቹ ባለቤት የሆነው የታይዋኑ ጎልድ አፖሎ ኩባንያ በበኩሉ ከፍንዳታው በስተጀርባ እጁ እንደሌለበት ገልጾ÷የፔጀርና ዎኪ ቶኪ ምርቶች መቀመጫውን ቡዳፔስት ባደረገው የቢኤሲ ኩባንያ የተመረቱ መሆኑን አስታውቋል፡፡
ይሁን እንጂ ኩባንያው ይህን ያለው የሂዝቦላህን ቁጣ ለማብረድና የኤሌክትሮኒክስ ምርቶቹ ከገብያ እንዳይወጡ በመስጋት ነው መባሉን አረብ ኒውስ ዘግቧል፡፡