ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) ሠራተኞች ከኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ጋር የተራዘመ የብድር አቅርቦትን በተመለከተ የመጀመሪያ ደረጃ ስምምነት ላይ መድረሳቸው ተገለጸ።
አይኤምኤፍ ባወጣው መግለጫ፣ ድርጅቱ በአራት ዓመታት የሚያቀርበው የ3.4 ቢሊዮን ዶላር የተራዘመ የብድር አቅርቦትን (Extended Credit Facility) በተመለከተ የመጀመሪያ ደረጃ ስምምነት ላይ ከኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ጋር ተደርሷል።
ስምምነቱ በይፋ በዓለም አቀፉ ገንዘብ ተቋም ዋና የአመራር ቦርድ ከታየ በኋላ ኢትዮጵያ ወደ 345 ሚሊዮን ዶላር ገደማ እንደምታገኝ ተገልጿል።
“በገበያ ሥርዓት ላይ የተመሠረተ የውጭ ምንዛሪ ግብይት ተመንን ጨምሮ ኢትዮጵያ አገር በቀል የምጣኔ ሃብት ፖሊሲ ማሻሻያ ማድረጓ በጥሩ ሁኔታ ውጤት እያሳየ ነው” ብሏል በመግለጫው።
በገበያ ሥርዓት ላይ የተመሠረተ የውጭ ምንዛሪ ግብይት ተመን መተግበሩ በትይዩና በይፋዊ ገበያ መካከል ያለውን ልዩነት በስፋት እያጠበበ እንደሆነም ተገልጿል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ያለፈው ዓመት ሐምሌ ላይ በገበያ ሥርዓት ላይ የተመሠረተ የውጭ ምንዛሪ ግብይት ተመንን ለመተግበር ውሳኔ አሳልፎ ተግባራዊ ማድረግ መጀመሩ ይታወሳል።
ከዚህ ቀደም ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም የብድር ስምምነት ላይ ሳይደርስ በኢትዮጵያ ለሳምንታት የዘለቀውን ቆይታውን ማጠናቀቁ ይታወሳል።
የድርጅቱ ተወካዮች አዲስ አበባ ሄደው በብድር ጉዳይ ውይይት ሲያደርጉ የቆዩት ኢትዮጵያ አገር በቀል የምጣኔ ሃብት ዕቅዷን ለመተግበር የሚያስችላትን የገንዘብ ድጋፍ ከተቋሙ መጠየቋን ተከትሎ ነበር።
ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ትናነት መስከረም 18፣ 2017 ዓ. ም. ባወጣው መግለጫ፣ ኢትዮጵያ “ስኬታማ ለውጦችን ማድረጓ የማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋትን የሚፈጥር፣ የውጭ ምንዛሬ አቅርቦትን አስተማማኝ የሚያረግና ለዘለቄታዊ የምጣኔ ሃብት እድገት የሚረዳ ነው” ብሏል።
የዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ሠራተኞች ቡደን የተመራው በአልቬሮ ፒሪስ ሲሆን እአአ ከመስከረም 17 እስከ 26፣ 2024 በኢትዮጵያ ቆይታ ማድረጋቸውን መግለጫው ይጠቁማል።
ያለፈው ዓመት ሐምሌ ላይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ ላይ የብድር ስምምነት ሊያጸድቅ መሆኑ መዘገቡ ይታወሳል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚያጸድቀው የብድር ስምምነት የትኛው እንደሆነ ይፋ ባይደረግም በወቅቱ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ለኢትዮጵያ በተራዘመ የብድር አቅርቦት የ3.4 ቢሊዮን ዶላር ብድር ማጽደቁን ማስወቁ አይዘነጋም።
ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ትናንት ባወጣው መግለጫ በአልቬሮ ፒሪስ የተመራው የልዑካን ቡድን በድርጅቱ ዋና የአመራር ቦርድ ይሁንታ ያገኘውን የ3.4 ቢሊዮን ዶላር የተራዘመ የብድር አቅርቦት በተመለከተ ከኢትዮጵያ አመራሮች ጋር የመጀመሪያ ደረጃ ስምምነት ላይ ደርሷል።
አልቬሮ ፒሪስ “የአይኤምኤፍ ሠራተኞችና የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣኖች ስምምነት በተቋሙ ዋና የአመራር ቦርድ በቀጣይ ሳምንታት የሚታይ ይሆናል።
ቦርዱ ከተመለከተው በኋላ ኢትዮጵያ በመጀመሪያ 345 ሚሊዮን ዶላር ታገኛለች” ማለታቸውንም ተቋሙ አስታውቋል።
“የኢትዮጵያ የምጣኔ ሃብት ማሻሻያ በተለይም በገበያ ሥርዓት ላይ የተመሠረተ የውጭ ምንዛሪ ግብይት ተመን መተግበሩ በትይዩና በይፋዊ ገበያ መካከል ያለውን ልዩነት በስፋት እያጠበበ ነው” ማለታቸውም ተገልጿል።
ለውጡ የውጭ ምንዛሬ አቅርቦት መጠንን በመጨመር ለአገሪቱ ምጣኔ ሃብት ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳደረገም ተናግረዋል።
“ወደፊት የአገር በቀል ምጣኔ ሃብት ፖለሲ ለውጡ የማክሮኢኮኖሚ መረጋጋትና የምጣኔ ሃብት እድገት ያመጣል” ብለዋል በአልቬሮ ፒሪስ።
የፖሊሲ ማሻሻያው በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ያለውን የፋይናንስ ሥርዓት በመለወጥ የዋጋ ንረትን እንደሚያረጋጋና ምጣኔ ሃብታዊ እንዲሁም ማኅበራዊ ጠቀሜታ እንዳለውም ገልጸዋል።
“ገቢ መጨመርና በመንግሥት ይዞታ ሥር ያሉ ተቋማትን ለማጠናከር የሚደረጉ የፋይናንስ ዘርፍ ለውጦች መንግሥት የሚያወጣውን ወጭ ቅደም ተከተል ለማስተካከልና ዘላቂነትን ለማረጋገጥ ይረዳሉ” ሲሉም አክለዋል።
በአልቬሮ ፒሪስ፣ የዓለም የገንዘብ ተቋምን የምጣኔ ሃብት ፕሮግራም በስኬታማነት በማስተግበር ነገር የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናትን አመስግነዋል።
በአልቬሮ ፒሪስ እና ቡድናቸው ንግግር ያደረገው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዢ አቶ ማሞ ምሕረቱ፣ ከገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ እና ከገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ኢዮብ ተካልኝ ጋር ነው።
ዘገባው የቢቢሲ ነው