የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ክስ እንደተመሰረተበትና የባንክ አካውንቶቹ እንደታገዱበት ተገልጾ ዜና መሰራስጨቱን ተከትሎ ” ከሳሾች በውሸት ቃለመሀላ ፍርድ ቤት ያሳሳቱ በመሆናቸው ራሳቸው በህግ የሚጠየቁበት ጊዜ ሩቅ እንደማይሆን እንረዳለን” ሲል መግለጫ አሰራጨ። ጉዳት አደረሱብኝ ያላቸውን ጠቅሶ በህግ እንደሚጠያቃቸውም አስታስውቋል።
ኦሊምፒክ ኮሚቴው መግለጫ ከማሰራጨቱ ቀደም ብሎ በሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ ሆቴል ጠበቆችና ከሳሾቹ እነ ኃይሌ ባሉበት መግለጭ ሰጥተው ነበር። በዚሁ መግለጫ ጠበቆቹ ዝርዝር ክሱን አስረድተዋል።
እነ አትሌት ኃይሌና ገዛኸኝ አበራ የሚመሩት ክስ ከእግድ ውጤቱ ጋር አብሮ ይፋ ከሆነ በሁዋላ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ለሚዲያዎች ባሰራጨው መግለጫው የክስ አግባብ እንዴት መከናወን እንዳለበት የራሱንና ዓለም ዓቀፉን ህግ ጠቅሶ ለማስገንዘብ ሞክሯል።፡
“ትዕግስቴ አልቋል” ያለው ኦሊምፒክ ኮሚቴ መረጃ እንዳለው ጠቅሶ ሚዲያዎች ላይ ክስ እንደሚመሰርት ይፋ አድርጓል። በዛውም የተሳሳተ መረጃ የሚያሰራጩ ሙያዊ ክብራቸውን እንዲጠብቁ አሳስቧል።
” …ምርጫ ታገደ ለሚባለው የደረሰን ነገር ባይኖርም በውሸት ቃለመሀላቸው የተሳሳተ ዳኛ ካለ በህግ አግባብ እናስቀለብሳለን። ከሁሉም በላይ እነዚህ ከሳሾች በውሸት ቃለመሀላ ፍርድ ቤት ያሳሳቱ በመሆናቸው ራሳቸው በህግ የሚጠየቁበት ጊዜ ሩቅ እንደማይሆን እንረዳለን” ሲል ክሱን አጣጥሏል።
…ለህብረተሰቡ የተዛቡ እና ሚዛናዊ ያልሆኑ የአንድ ወገንን መረጃ ብቻ በማቅረብ የስፖርት ቤተሰቡን እያሳሳቱት ይገኛሉ። እስካሁን በሆደ ሰፊነት ሁሉንም ችለን አልፈነው የነበረ ቢሆንም ከዚህ በላይ መጓዝ ተቋሙን እና አገርን አደጋ ውስጥ ሊከት ስለሚችል እያንዳንዱን ድርጊታቸውን በማጋለጥ በህግ የምንጠይቃቸው መሆኑን እንገልፃለን። ከህገ ወጥ ድርጊታቸውም እንዲቆጠቡ ስንል በዚሁ አጋጣሚ እናሳስባለን።
ሙሉ መገለጫውን ያንብቡ
- የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ እንኳን ለ2017 አዲስ አመት በሰላም በጤና አደረሳችሁ ይላል !!
የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ በተሰጠው ስልጣን እና ተግባር መሰረት ሀላፊነቱን በአግባቡ እየተወጣ ይገኛል ። ይሁን እንጂ በተቋሙ አሰራር የሚረካ እንዳለ ሁሉ ደስተኛ ያልሆነ ወይም ቅሬታ ያለው አካል ሊኖር ይችላል። ይህ በየትኛውም ድርጅት ያለና የሚኖር ነው። ተቋሙ በስፖርት መድረክ አለመግባባቶች እና ቅራኔዎች ሲኖሩ የሚስተናገዱበት መንገድ በመተዳደሪያ ደንቡ በግልፅ አስቀምጧል። አንቀፅ 38 ላይ ” በኢትዮጵያ ብሔራዊ የኦሊምፒክ ኮሚቴ ውስጥ ወይም በኢትዮጵያ ብሔራዊ የኦሊምፒክ ኮሚቴ እና በአባላቱ መካከል የሚነሱ ማናቸውም ከስፖርት ጋር የተያያዙ ወይም ተቋማዊ ቅራኔዎች በሚመለከታቸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ የኦሊምፒክ ኮሚቴ የአስተዳደር አባላት ( በሜኔጅመንት በቦርድ ወይም በጠቅላላ ጉባኤ ወይም ለዚሁ ችግር አፈታት በሚቋቋም የፍትህ አካል ይፈታል ። ከስፖርት ጋር የተያያዙ ያለመግባባቶችና ቅሬታዎች ከመደበኛ ፍርድ ቤቶች ውጭ ይፈታሉ ።) ጉዳዩ ለስራ አስፈፃሚ ቦርድ እና /ወይም የኢትዮጵያ ብሔራዊ የኦሊምፒክ ኮሚቴ ከፍተኛ የስልጣን አካል ለሆነው ለጠቅላላ ጉባኤው ይመራል። ጠቅላላ ጉባኤው በቀረበው ጉዳይ ላይ የመጨረሻ ውሳኔ ለመስጠት ወይም ቅራኔውን ለመፍታት የእርቅ ፣ የግልግል ወይም የሽምግልና አካል እንዲሰየም ውሳኔ ሊሰጥ ይችላል ። በቀረበው ቅራኔ ላይ የተሰጠ ማንኛውም የመጨረሻ ውሳኔ በአቤቱታ መልክ ብቻ ሉዛን ስዊዘርላንድ ለሚገኘው የስፖርት ዳኝነት ፍርድ ቤት ሊቀርብ ይችላል ። አቤቱታውን ማቅረብ የሚቻለው የሚመለከተው ውሳኔ ከተሰጠ በኋላ በ21 ቀናት ቀነ ገደብ ውስጥ ነው። ” ይላል ።
በዚህ መሰረት :-
1ኛ / የስፖርት ነክ ጉዳዮች በመደበኛ ፍርድ ቤት እንደማይታዩ እና መደበኛ ፍርድ ቤት ስልጣን እንደሌላቸው እየታወቀ ህግና ስርአትን ተከትሎ ጥያቄ ማንሳት ሲገባ የውሸት ቃለመሀላ በማቅረብ እና ተረኛ ችሎቱን በማሳሳት እግድ ያወጡበት መንገድ ከሳሽ ነን የሚሉት ግለሰቦች ተከራክረው ማሸነፍ የሚችሉበት የእውነተኛ የህግ መሰረት የሌላቸው መሆኑን ያሳያል። በተጨማሪም በውሸት ቃለመሀላ ያገኙትን እግድ ልክ ተከራክረው እንዳሸነፉ መግለጫ መስጠታቸው የቱን ያህል በሀላፊነት እና በተጠያቂነት ስሜት እንደማይሰሩ በግልፅ የሚያሳይ ነው። ሀገርን ለማስቀጣት የሚደረገው እንቅስቃሴ በአስቸኳይ ሊቆም ይገባል።
2ኛ/ በአለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ (IOC) ሙሉ በሙሉ የታገደው እና እውቅና በግልፅ የተከለከለው እንዲሁም የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ አባል ያልሆነው በአቶ እያሱ ወሰን የሚመራው የቀድሞው የቦክስ ፌዴሬሽን ከሳሽ ሆኖ መምጣቱ ” እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል ” እንዳለችው እንስሳ ኦሊምፒክ ኮሚቴን ይዤ ልውደቅ ከሚል ክፉ መንፈስ የመነጨ በመሆኑ ይህንን የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲገነዘበው ለመግለፅ እንወዳለን።
3ኛ/ ሻለቃ ሀይሌ ገብረስላሴ የባለፉትን አራት አመታት የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ምክትል ፕሬዝደንት ሆኖ መቆየቱ ይታወቃል። ነገር ግን ራሱን ከደሙ ንፁህ ነኝ በሚል እና ከዚህ ቀደምም የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት በነበረበት ወቅት ለማናጀሮች እና ለስፖርት ትጥቅ አምራች ካምፓኒዎች አሳልፎ በመስጠት ብሄራዊ ቡድን ያፈረሰው ራሱ ሆኖ እያለ የስፖርቱ ተቆርቋሪ ሆኖ መምጣቱ እጅግ አሳዝኖናል። ለመሆኑ ሻለቃ ሀይሌ ገብረስላሴ የባለፉትን አመታት የት ነበር ?
4ኛ/ ጀግናው አትሌት ገዛኸኝ አበራ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዝዳንት እንደሆነ ይታወቃል። በፌዴሬሽኑ ውስጥ ያለበትን የማኔጅመንት ክፍተት ወደ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ይዞ መምጣቱ ” ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ ” የሚባለው ብሂል አይነት ነው።
5ኛ/ ከዚህ ቀደም በኦሊምፒክ ኮሚቴ ውስጥ የስፖርት ትጥቆችን መርካቶ ድረስ ሄደው በመቸብቸብ በፈፀሙት ህገ ወጥ ተግባር በኮሚቴው የታገዱ አካላት ይህንን እንደ መልካም አጋጣሚ በመቁጠር ስልጣን በሌለው መደበኛ ፍርድ ቤት ከሳሽ ሆነው መቅረባቸው እጅግ አሳፋሪ ነው ።
6ኛ/አንዳንድ የሚዲያ ባለሙያዎች ከግለሰቦች ጋር በግልፅ በገንዘብ በመደለል እና በጥቅም በመተሳሰር (ለዚህም በቂ ማስረጃዎች አሉ ) ለህብረተሰቡ የተዛቡ እና ሚዛናዊ ያልሆኑ የአንድ ወገንን መረጃ ብቻ በማቅረብ የስፖርት ቤተሰቡን እያሳሳቱት ይገኛሉ። እስካሁን በሆደ ሰፊነት ሁሉንም ችለን አልፈነው የነበረ ቢሆንም ከዚህ በላይ መጓዝ ተቋሙን እና አገርን አደጋ ውስጥ ሊከት ስለሚችል እያንዳንዱን ድርጊታቸውን በማጋለጥ በህግ የምንጠይቃቸው መሆኑን እንገልፃለን። ከህገ ወጥ ድርጊታቸውም እንዲቆጠቡ ስንል በዚሁ አጋጣሚ እናሳስባለን።
የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ እየተካሄደ ያለውን ግልፅ ህገወጥ ተግባር የስፖርት ቤተሰቡ ግራ ቀኙን አገናዝቦ እንዲመለከተው ጥሪውን ያስተላልፋል። የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ምርጫ ታገደ ለሚባለው የደረሰን ነገር ባይኖርም በውሸት ቃለመሀላቸው የተሳሳተ ዳኛ ካለ በህግ አግባብ እናስቀለብሳለን። ከሁሉም በላይ እነዚህ ከሳሾች በውሸት ቃለመሀላ ፍርድ ቤት ያሳሳቱ በመሆናቸው ራሳቸው በህግ የሚጠየቁበት ጊዜ ሩቅ እንደማይሆን እንረዳለን ።
ፈጣሪ አገራችንን ይጠብቅልን !!
በድጋሚ መልካም አዲስ አመት እንመኛለን ።
ቀደም ሲል ከሳሾች በሻለቃ ኃይሌ ሆቴል ተገኝተው መግለጫ ሰጥተው ነበር። አዲስ ዘመን ስፍራው ላይ ተገኝቶ እንደሚከተለው አጠናክሮታል
የተለያዩ ብሔራዊ ፌዴሬሽኖችና አትሌቶች በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴና በአመራሮቹ ላይ ከቀናት በፊት በመደበኛ ፍርድ ቤት ክስ መመስረታቸው ይታወሳል። ፌዴሬሽኖቹንና አትሌቶቹን ወክለው ክሱን ያቀረቡት ጠበቆች ከትናንት በስቲያ በኃይሌ ግራንድ ሆቴል በቀረበው ክስ ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል። ይህንን ተከትሎም ኦሊምፒክ ኮሚቴ መግለጫ አውጥቷል።
ጠበቆቹ በሰጡት መግለጫ ከሳሾቹ የኢትዮጵያ ቴኒስ እና ቦክስ ፌዴሬሽኖች ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገ/ስላሴና የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት አትሌት ገዛኸኝ አበራ መሆናቸውና እነሱን ወክለው ችሎት ላይ እንደሚቆሙ አስረድተዋል።
የኢትየጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ እንደ ተቋም፣ በግል ፕሬዚዳንቱ ዶ/ር አሸብር ወ/ጊዮርጊስ፣ ዋናና ምክትል ጸሐፊዎቹ አቶ ዳዊት አስፋውና አቶ ገዛኸኝ ወልዴ እንዲሁም አቃቤ ነዋይ ዶ/ር ኤደን አሸናፊ መከሰሳቸውን የገለጹት ጠበቆቹ፣ አራት ፌዴሬሽኖች ክሱን ለመቀላቀል ጠይቀው ጉዳዩን እያዩ መሆናቸውን ይፋ አድርገዋል። ”አራት ፌዴሬሽኖች የዚህ ክስ አካል ለመሆን ጠይቀውናል እያጠናነው ነው፣ ከማን ጋር ነው የምንጋጨው ብለው የሰጉም አሉ፣ ማንም በህግ አንጻር እኩል ነው ብለን ነው የምናምነው፣ የምንጋጨውም ግለሰብ የለም፣ መንግሥት ጣልቃ ይገባል ብለንም አንሰጋም” ሲሉም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ኦዲት አልተደረገም የሚለውን ጉዳይ አፅንኦት የሰጡት ጠበቆች፣ ተቋሙ ወደ 1 ቢሊዮን ብር በካሽና በአይነት ያለው ሂሳብ ኦዲት እንዲደረግ መጠየቃቸውን ጠቅሰው፤ ወደ 48 ሚሊዮን ብር ለአኖካ ስብሰባ ተብሎ መንግሥት ክፍያ መፈፀሙን፣ እንደ ኢትዮ ቴሌኮምና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከፍተኛ ክፍያ ፈጽመው ኦዲት እንዳልተደረገ፣ ከ400 ሺህ ዶላር በላይ የሆኑ ትጥቆች በየዓመቱ ከአዲዲስ ኩባንያ ቢላክም የት እንደገባ እንደማይታወቅ ገልፀዋል።
“ኦሊምፒክ በተካሄደ ቁጥር ወደ 600 ሺህ ዶላር የሚገመት የስፖርት ትጥቅ ድጋፍ ይደረጋል፤ ለመላው አፍሪካ ወደ 500 ሺህ ዶላር ድጋፍ ተደርጓል፤ ለኦሊምፒክ ውድድር ተሳትፎ 30 ሺህ ዶላር ለስልጠና ተብሎ ደግሞ ከ15-20 ሺህ ዶላር በየዓመቱ ይመጣል፤ 198 ሺህ ዶላር ወጣቶችን ለማትጋት ተብሎ ይሰጣል፤ እስካሁን ግን ምንም ኦዲት አልተደረገም፤ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴርም የሚጠበቅበት ኃላፊነቱን አልተወጣም። በዚህም አዝነናል። ዋናው ጥያቄያችን ከላይ የገለጽናቸው ገቢዎች የት ገቡ ወይም ለምን ወጪ ተደረጉ የሚለው ምላሽ ያስፈልገዋል፣ ችሎቱን የጠየቅነውም ይህንን ነው” ሲሉ አብራርተዋል።
ጠበቆቹ አቶ አያሌው ቢታኒ ፣ አቶ ኃይሉ ሞላና አቶ ጳውሎስ ተሰማ ለመደበኛ ችሎት አቀረብን ባሉት የክስ ማብራሪያ፣ “ግንቦት 5 እና ሰኔ 14/2016 የተደረጉት የኮሚቴው ህገወጥ ጉባኤና ውሳኔዎቹ ይሰረዙ፤ ተገቢ በሆነ አግባብ አጠቃላይ ወጪ ላይ ኦዲት ይደረግ፤ በፓሪስ ኦሊምፒክ ህገወጥ የሰዎች ዝውውር እንደተካሄደ የሚያሳይ ነገር ስላለ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና በፈረንሳይ ኤምባሲ በኩል እነማን ሄዱ እነማን ተመለሱ የሚለው እንዲጣራ ጠይቀናል፤ ኦሊምፒክ ኮሚቴው በ64 ሚሊዮን ብር ወጪ የውሃ ማምረቻ ፋብሪካ ለማሰራት ማሽኖችን ከውጪ አስገብቷል። የገቡት ማሽኖች እውነት ለፋብሪካው ስራ የሚጠቅሙ ናቸው የሚለው ይጣራል” ሲሉም አጠቃላይ የክሱን ጭብጥ አስረድተዋል።
ስፖርቱን በበላይነት የሚመራው መንግሥታዊ ተቋም ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የሚጠበቅበትን ዳኝነት እንዲሰጥ በተደጋጋሚ ያቀረብነው ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ ባለማግኘቱ ጉዳዩን ወደ መደበኛ ፍርድ ቤት እንደ ወሰዱትም ጠበቆቹ አብራርተዋል። በዚህም ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ችሎቱ ፊት ቀርቦ ምላሽ እንደሚሰጥና ለደረሰው ጉዳትም ወጪን እንደሚሸፍን ገልፀዋል።
‹‹በግልና በኦሊምፒክ ኮሚቴ አመራሮች ላይ የተወሰነው የ11 የባንክ ሂሳብ ቁጥር እገዳ ጊዜያዊ ነው። እገዳው እስከ ችሎቱ ውሳኔ የሚሰጥበት ጊዜ ድረስ የጸና ነው” በማለትም ሂደቱን ገልጸዋል።