የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የተበላሸ የብድር መጠንን ከነበረበት 57 በመቶ ወደ 6 ነጥብ 5 በመቶ ማውረድ መቻሉን የባንኩ ፕሬዚዳንት ዮሀንስ አያሌው (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ውጤቱ ባለፉት 5 ዓመታት በተሰሩ የሪፎርም ስራዎች እውን መሆኑን ጠቅሰው፤ ከዚህ ቀደም የነበሩበት ጣልቃ ገብነቶች፣ ብልሹ አሰራር፣ በሲስተም የታገዘ የአሰራር ስርዓት አለመኖር እና የሰው ሀይል ችግሮች ባንኩን ለኪሳራ ዳርገውት እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
ባንኩ ሁለት ጊዜ ካፒታሉ እንዲያድግ ቢደረግም ተከታታይ ኪሳራ ማስመዝገቡን ገልጸው÷ በወቅቱ የባንኩ የተበላሸ ብድር ክምችት 27 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ደርሶ እንደነበር ተናግረዋል፡፡ መንግስት ባንኩ እንዳይዘጋ ሪፎርም መደረግ አለበት የሚል ትልቅ ውሳኔ አሳልፎ ህልውናውን የማስቀጠል ትልቅ እርምጃ መውሰዱን ገልጸዋል፡፡
እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ታዳጊ ሀገራት ያለ ልማት ባንክ የረዥም ጊዜ ኢንቨስትመንትን ፋይናንስ ማድረግ እንደማይቻልም አስረድተዋል፡፡ ባንኩ ከዚህ ቀደም የነበረውን ፍትሃዊ ያልሆነ የብድር አሰጣጥ ለማስቀረት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ምክክር አድርጎ ወደ ሪፎርም መግባቱን ተናግረዋል፡፡
በዚህም የባንኩ የተበላሸ ብድር መጠን እየቀነሰ መምጣቱን የገለጹት ፕሬዝዳንቱ÷ ይህም ከ57 በመቶ ወደ 6 ነጥብ 5 በመቶ ዝቅ ማድረግ መቻሉን ጠቅሰዋል፡፡
ከ6 ነጥብ 5 በመቶው የተበላሸ ብድር ውስጥ 3 ነጥብ 9 በመቶ የሚሆነው ከጋምቤላ እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ላይ ከእርሻ ጋር የተያያዘ ችግር መሆኑን ፕሬዚዳንቱ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል።
የባንኩን የተበላሸ የብድር መጠን እንደ ንግድ ባንኮች ጤናማ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።
የመንግስት ልማት ድርጅቶች የይዞታና አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር አቶ ሃብታሙ ኃ/ሚካኤል በበኩላቸው÷ መንግስት የወሰደው የመጀመሪያው ዙር የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ለባንኩ ትልቅ ትንሳኤ በመሆኑ ባንኩ አሁን ጤናማ ጉዞ ላይ ይገኛል ብለዋል።
ከሪፎርሙ በፊት ከ3 ቢሊየን ብር በታች የነበረው የባንኩ የተጣራ ሃብት አሁን 40 ቢሊየን ብር መድረሱንም ተናግረዋል፡፡ አጠቃላይ የባንኩ ካፒታልም 182 ቢሊየን ብር መድረሱን ዳይሬክተሩ ጠቅሰው የመንግስት ሚዲያዎች አመልክተዋል።