ግብጽን በግልጽ ስሟን ጠቀሰው ” የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላት” ሲሉ የተናገሩት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፣ “ህዝባችን የኢትዮጵያን ሁኔታ በደንብ መረዳት አለበት” በማለት አስጠንቀቀዋል። “ባንዳ” በማለት ለውጭ ሃይሎች ያደሩ ታጣቂዎችና የሚዲያ ሰራተኞችን ጠቅሰውም ምን ያህል በአገሪቱ ይ ክህደት እየፈጸሙ እንደሆነ አመልክተዋል።
የአሳብ መተራመስ በመኖሩ፣ የጠቀሷቸው ሚዲያዎች ህዝቡን በስህተት መረጃ ሆን ብለው እያሳከሩ በመሆኑ ህዝቡ እውነታውን በደንብ መመርመር እንዳለበትና ቆቅ ሆኖ የአገሩን ሁኔታ መከታተል እንደሚገባው ሲያሳስቡ፣ በደንብ ያልተረዱ ማንም እንደሚነዳቸው ቀድመው በመጥቀስ።
ባለማወቅና በመረጃ በመጭበርበር ዜጎች የውጭ ኃይላት የተቀነባበረ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ መሳሪያ እንደሚሆኑ ያመለከቱት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፣ ሚዲያው በዚህ ረገድ በባንዳነት ድርሻውን እየተወጣ እንደሆነ አሰራሩንና አካሄዱን ለያይተው ገልጸዋል። “ለውጭ ኃይሎች ተገዝቶና የሚዲያ ሰራተኛ ሆኖ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ይሰራል” ሲሉ ሚዲያዎችና ተቀጥረው የሚሰሩትን ሰራተኞች ስም ስይዘረዝሩ በላቀ ደረጃ ኢትዮጵያን ለማፍረስ አጀንዳ ላላቸው ክፍሎች እንደሚሰሩ አስታውቀዋል።
ከደረግ ዘመን ጀምሮ የሻዕቢያንና የወያኔን የትጥቅ ትግል በማቀጣጠል፣ የውክልናው ጦርነት ኢትዮጵያን ከቀይ ባህር በማግለል ስምምነት ሲጠናቀቅ በተለያዩ የውጭ አገራት ያደራጁቸው ሚዲያዎች ውስጥ ኢትዮጵያዊያን እንደሚሰሩ ይታወቃል። እነዚሁ ሚዲያዎች የኢትዮጵያን መከላከያ ሰራዊት ” የደርግ ጦር” በማለት እንዲፈርስ ሰፊ ፕሮፓጋንዳ ሲሰሩ እንደነበር ሰላባ የሆኑ ወታደራዊ መኮንኖች በተለያዩ ጊዜያት ማስታወቃቸው አይዘነጋም። በውጭ መንግስታት በቀጥታና በተዘዋዋሪ በርዳታ ሳም የሚከፈላቸው፣ የሚደጎሙና ጭራሽ የተሸጡ ሚዲያዎች አሁንም ድረስ እንዳሉ የሚታወቅ ነው።
ፊልድ ማርሻሉ በይፋ ስም ባይዘረዙም ግብጽ የምትከፍላቸውና በተዘዋዋሪ በሻዕቢያ በኩል የመታስተዳድራቸው ” ኢትዮጵያዊያን” የሚዲያ ሰራተኞች ቀደም ሲል ከነበሩት የሚታወቁ ሚዲያዎች ተጨማሪ ሆነው አገሪቱ እንዳትረጋጋ በየቀኑ አጀንዳ እየቀያየሩ መረጃ እንደሚረጩ በጥናት የተደገፈ መረጃ መውጣቱ የሚታወስ ነው።
ለተቀጠሩበት ሚዲያ ዓላማና ሚዲያውን ላቋቋመው አገር አጀንዳ ኢትዮጵያን የሚጎዳ፣ ህዝቧን የሚበትን፣ ብሄራዊ ጥቅሟን የሚጻረር መረጃ የሚያሰራጩት እነዚሁ ወገኖች በቅርቡ ትህነግ መከላከያ ላይ የክህደት ወንጀል ፈጽሞ፣ አማራና አፋር ክልልን ወሮ ወንጀል ሲፈጽም ህዝብ ለህልውናው ያደረገውን ዘመቻ ሲነቅፉ፣ ሲወነጅሉና አውዱን አስተው ሲዘገቡ እንደነበር ታሪክ እንደማይረሳው የውቅቱን የሚዲያ አካሄድ አስመልክቶ አስተያታቸውን የሰጡ አመልክተዋል።
” … የሚያሳዝነው በሚከፍሏቸው ኃይሎች አጀንዳ ሳቢያ ከትህነግ ጋር አብረው ኢትዮጵያ ላይ ሽንፈትና ውድቀት ሲያውጁ የነበሩ ወደ አገር ቤት ሲመጡ ካባ እያለበሱ የሚቀበሏቸው ናቸው” ሲሉ በውቅቱ አቶ ኃይሉ የሚባሉ የአዲስ አበባ ነዋሪ አስተያየት ኢትዮ12 ላይ መስጠታቸው አይዘነጋም። እሳቸው ብቻ ሳይሆኑ በውጭ ኃይሎች በሚመሩ ሚዲያዎች ኢትዮጵያ ላይ ምን ያህል አፍራሽና ዳግም ለመስማት የሚዘገንን መረጃ ይተላለፍ እንደነበር ያወሱ ሌላ አስተያየት ሰጪ ” መንግስት በውጭ አገራት የሚተዳደሩ ሚዲያዎች ውስጥ በሚሰሩ የራሳችን ዜጎች ኢትዮጵያ ላይ ሲረጭ የነበረውን መርዝ ሰብስቦ ለታሪክ እንዲያስቀምጠው ጥሪ አቀርባለሁ። ልጆቻችን ይማሩበታል።፡ከሁሉም አስነዋሪው የሚዲያ ባንዳነት ነው” ብለው ነበር።
“ታጥቆ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ይሰራል” በሚል ከሚዲያው ጎን ለጎን ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ሌት ተቀን ስለሚተጉ ኃይሎች የተናገሩት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፣ እነዚህ ኃይሎችም የተገዙ መሆናቸውን አመልክተዋል። “የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላት ናት” ሲሉ ግብጽን በገሃድ በትክክለኛ ማንነቷ የጠሯት ፊልድ ማርሻሉ፣ የውስጥ ኃይሎች በመጠቀም በኢትዮጵያ ውስጥ ግጭት እንዲፈጠር እንደምትሰራ ይፋ አድርገዋል።
የኢፌድሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ “ግብፅ ሞቃዲሾ ስለመጣች ወደ ኢትዮጵያ ወረራ ይፈጸማል ብሎ የሚያስብ ካለ ሞኝ ነው” በሚል በሰራዊቱ መካከል ቆመው ተናግረዋል። አክለውም “አያደርጉትም” በማለት ግብጽ በእጅ አዙር የመዋጋት ፍላጎት ብቻ እንዳላት ከልምድ ተነስተው ተናግረዋል።
ግብጽ በተዛዋሪ ከምትሄድበት መንገድ ወጥታ ሌላ ነገር ብታስብም ምን ሊሆን እንደሚችል ኤታማዦር ሹሙ ሲያስገነዝቡ፣ “በእጅ አዙርም ይምጣ በቀጥታም ይምጣ የኢትዮጵያ አቅም አሁን ከባድ ነው፣ አይችሉንም” ብለዋል።
መረር ብለው ኤታማዦር ሹሙ ይህን ንግግር ያሰሙት መቀመጫውን ሀረር ከተማ ያደረገው ታሪካዊው የምስራቅ ዕዝ አርባ ሰባተኛ ዓመት የምስረታ ክብረ በዓሉን አስመልክቶ በሀረር ከተማ በተካሄደ የዕዙን ታሪክ የሚዘክር የመፅሀፍ ምረቃ መድረክ ላይ በተገኙበት ወቅት ነው።
አሜሪካ እስከ አፍንጫው ያስታጠቀችው ዜያድባሬ በዕብሪት ተወጥሮ አውሽን ዘልቆ ወረራ ባካሄደበት ወቅት የተቋቋመው ይህ እሳት የሚተፋ ታሪካዊ ጦር በኢትዮጵያዊያን ዘንድ ታላቅ ክብር ያለውና ስሙ ሁሉ ከድል ጋር የሚነሳ የቁርጥ ቀን ልጅ መሆኑ ታሪኩን የሚያውቁ ሲናገሩ መስማት የተለመደ ነው።
በሀረር ከተማ የምስራቅ ዕዝን የጦር ሜዳ እና ተያያዥ ታሪክ በሚያትተው መፅሀፍ ምረቃ ላይ ትናንት ሰፊ ንግግር ያደረጉት ኤታማዦር ሹሙ፣ የረዥም ዘመን ታሪክ ያላት ሀገር እርስ በእርስ በመታኮስ ማሳለፏ የረባ ነገር እንዳይኖራት አድርጓል ብለዋል። ሀገሪቱ በግጭት ውስጥ እንድትቆይ ካደረጉ ታሪካዊ ጠላቶች መክከል ግብፅን በመጥቀስ “የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላት ናት” ሲሉ ለከፈተኛ የጦር መኮንኖቻቸውና ለኢትዮጵያ ህዝብ በይፋ አስታውቀውዋል። ያለ አንዳች ስጋትና ጥርጥር “ግብፅ ሞቃዲሾ ስለመጣ ወደ ኢትዮጵያ ወረራ ይፈፅማል ብሎ የሚያስብ ካለ ሞኝ ነው ፤ አያደርጉትም” ብለዋል።
ይሁን እንጂ የኢፌድሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ ሀገሪቱ ገከተከመሩት የቀደሙ ችግሮች ተላቃ ወደ መረጋጋት እንድትመጣ ሰፊ ስራ መሰራት እንዳለበት ጠቅሰዋል። እናም ሰራዊቱ ለአፍታም መዘናጋት እንደሌለበት አሳስበዋል። ህዝቡም የኢትዮጵያን ሁኔታ በደምብ መረዳት አለበት ሲሉ አስንዖት ሰጥተዋል።
የዚያድባሬ ጦር በኢትዮጵያ ላይ የፈፀመውን ወረራ ለመቀልበስ በወቅቱ በተወሰዱ እርምጃዎች የተመሰረተው የምስራቅ ዕዝ በጅግጅጋ እና ሀረር ከተሞች አርባ ሰባተኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን በተለያዩ መርሀ ግብሮች እያከበረ ይገኛል።
በሀረር ከተማ ስታድየም የዕዙ ምስረታ በዓል ማጠቃለያ ዝግጅት የሀገሪቱ ከፍተኛ ወታደራዊ ሹሞች እንዲሁም የሀረሪ ክልል እና የድሬደዋ መስተዳድር ባለስልጣናት እና የአካባቢው ህብረተሰብ በተገኙበት ተከብሯል።
በሀረር በተካሄደው የበዓሉ የመዝጊያ መድረክ ላይ የኢፌድሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ ተገኝተው በተመሳሳይ ንግግር አድርገዋል። በዚሁ ንግግራቸው በዓለም ቀዳሚና የረዥም ዓመት ታሪክ ላላት አገራችን በእነዚህ ዘመናት ሁሉ “ምን ሰራን ብለን መጠየቅ አለበን” ብለዋል።
እንደ ሰው ይናገራሉ የሚባሉት ኤታማሾር ሹሙ እያንዳንዱ ዜጋ እንዲያስበው ካነሱት ጥያቄ አስከትለው “ሁለት መቶና ሁለት መቶ ሃምሳ ዓመት እድሜ ያላቸው ፣ ትናንትና የተፈጠሩ ዛሬ እኛን እንደፈለጉ ያደርጉናል፣ ቁጭ በሉ ፣ ብድግ በሉ ፣ ወደ ቀኝ እና ግራ ዙሩ እያሉን ነው” ሲሉ በቁጭት “ምን ሰራን” በማለት ጥያቄ ያነሱበትን አሳብ በቁጭት አብራርተዋል።
ብርሃኑ ጁላ ለጥያቄያቸው ምልስ አላቸው። ተነሱ፣ ተቀመጡ፣ ዙሩ ለሚለው የታናናሾቻችን ትዕዛዝ የዳረገንን ምክንያት ሲያስታውቁ ያለምስራት ችግር ያመጣው መዘዝ መሆኑንን ይገልጻሉ። “እንደዛ [ታዛዥ] የሆነው ስላልሰራን ነው ።ያልሰራነው ደግሞ ስንዋጋ ስለኖርን ነው። አጀንዳችን መታኮስ መዋጋት ብቻ ስለነበረ ነው። ከዚህ ግጭት በስተጀርባ ደግም ታሪካዊ ጠላቶች አሉን፤ በተለይ ግብፅ ለምን እንደምንፈራ አላውቅም የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላት ናት” በማለት አስረግጠው ተናግረዋል።
“እኛን በማዳከም በታሪካችን በሙሉ ሁሉንም ስራ የሰሩት እነሱ (ግብፆች) ናቸው ። ከባህር እንድንርቅ ያደረጉ ፣ በአገር ውስጥ የተለያዩ ኃይሎችን የፈጠሩ ፣ ከለውጥ በኃላ በሰሜን ኢትዮጵያ ለነበረው ግጭት መሳሪያ ሲያቀብሉ የነበሩ እነሱ ናቸው ” ሲሉ የቆየውንና የታመቀውን የህዝብ ስሜት በአደባባይ ገልጸዋል።
“ኢትዮጵያ ወደ ኖርማላይዜሽን ወይም ወደ መረጋጋት የምትገባው ገና ነው ። አሁንም ትግል አለ ስለዚህ መዘናጋት አያስፈልግም፤ ሰራዊቱን ማሰልጠን ፣ ሰራዊት መገንባትና ማብቃት ፣ስራዊት ማብዛት ፣ መታጠቅ እና ቆቅ መሆንም ያስፈልጋል ” ሲሉ ማሳሰቢያ ሰጥተዋል። እንደ መሪ መኮንን ግብጽ ታሪካዊ ጠላት መሆኗን ጠቅሰው ” ቆቅ እንሁን” ማለታቸውን ተከትሎ የግብጽ መገናኛዎች ንግግራቸውን እየተቀባበሉ መሚያመቻቸው አግባብ እያዋሉት ነው። በተመሳሳይ ኢትዮጵያዊ የሚባሉ አንዳንድ መዲያዎች መሰረታቸውን ዘንግተው ለግብጽ በሚጠቅም መልኩ እየዘገቡ ነው። መሳሪያና ወታደር አስልተው ” ኢትዮጵያ ትሸነፋለች። ወየውላችሁ” ሲሉ የከረሙም አሉ።
ባዛው ንግግራቸው “ከአሁን በኃላ ኢትዮጵያ እስካሁን እየተንከባለልን በመጣነው መንገድ መቀጠል የምትችል አይመስለኝም” ሲሉ ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ የኢትዮጵያ ህዝብ ማሰብ እንደሚገባው አሳስበዋል። ሰራዊቱም ኢትዮጵያን ለማስቀጠል ከዚህ ቀደም ከከፈልነው መስዋዕትነት በላይ ለመክፈል መዘጋጀት እንዳለበት መመሪያ ሰጥተዋል።
“ሶስቴ አራቴ ሞክረው ልክ ገብተው አይቻልም ብለው ሄደዋል ” ያሉዋቸው የውጭ ኃይሎች ዛሬ በእጅ አዙር ሊዋጉን እንደሚፈልጉ ደጋግመው የተናገሩት የኢፌድሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም፣ ” … በእጅ አዙርም ይምጡ በቀጥታም ይምጡ የኢትዮጵያ አቅም አሁን ከባድ ነው። አይችሉንም” ብለዋል። አያዘው “እኛን ያስቸገረንና እያስቸገረን ያለው የእኛ ባንዳ ነው” ሲሉ ከላይ ስለ ባንዳነት ያነሱትን አሳብ ወደ ማሳረጊያቸው አምጥተዋታል።
እባክዎን በቴሌግራም ገጻችን የከታተሉን – https://t.me/+f_kxmaPjD-9jYTdk