አይተ ኢሣያስ አፈወርቂ፣ በወታደራዊው ደርግ መንግሥት ውድቀት ማግሥት በቪኦኤ ላይ “ነፃነት ወይስ ባርነት” ብላችሁ ሪፈረንደም ማካሄድ ተገቢ ነው ወይ? ለምን ከኢትዮጵያ መገንጠል ወይስ በአንድነት መቀጠል ወይም በፌዴሬሽን መቀጠል የሚሉ አማራጮችን አላቀረባችሁም ለሕዝብ? ተብሎ ሲጠየቅ የሰጠው መልስ አጭር ነበር።
እኛ ከኢትዮጵያ ጋር አንድላይ የነበርንበት ታሪክ የለም ነው የምንለው፣ በግድ የተያዝን ሕዝቦች ነን፣ ከእናት ሀገራችን ስለመገንጠል ልናነሳ አንችልም፣ ቅኝ ተገዢዎች ነበርን፣ አሁን በዚያ መቀጠል ትፈልጋለህ? ወይስ ነፃነትህን ትፈልጋለህ? የሚል ምርጫ ለሕዝባችን ማቅረባችንም ተገቢ ነው። አማራጩ ምንም ቢደረግም ኖሮ፣ ሕዝባችን ይሄንኑ መምረጡ ደግሞ አይቀርም ነበር።
ሳስበው ኢሣያስም በአምሣሉ እንደፈጠራቸው እንደ ወያኔ መሪዎች ሁሉ፣ የታሪክ ጨዋ ነው። እነዚህኞቹ አክሱምንና ላሊበላን፣ ራስ አሉላና አፄ ዮሐንስን፣ አጠገባቸው ቁጭ አድርገው ታሪካችን የመቶ ዓመት ታሪክ ነው አሉ።
አይተ ኢሣያስ ደሞ የእነ ራስ አሉላና ሌሎች ሀገራችን ኢትዮጵያ ነች ብለው ከጣልያን ጋር ሊፋለሙ ከእነ አሉላም በፊት የተነሱ የኤርትራ አርበኞችን ታሪክ ሙልጭ አድርጎ ይክደዋል።
ለመሆኑ ከአድዋ በፊት ኢጣልያ በኤርትራ ለመጀመሪያ ጊዜ እግሯን የረገጠችው መቼ ነበር? በ1869 እኤአ ነበር። ማለትም ከአድዋው ጦርነት 26 ዓመት በፊት ማለት ነው። ያውም እሱም አንድ ለስብከት መጣሁ የሚል የጣልያን ሚሲዮናዊ ነው። ጁሴፔ ሳፔቶ የሚባል የካቶሊክ ቄስ።
በምፅዋ ተቀምጦ ሲያበቃ፣ የሆነ ማን እንደፈረመው የማይታወውል ይዞ ወደሀገሩ ተመለሰ። እና በሮማ ሰነድ ግምጃ ቤት ቀርቦ ምፅዋን በ6ሺ ሊሬ ከአንድ የአካባቢው ሡልጣን ላይ ገዛሁ ብሎ ወረቀቱን አስገባ።
ቆየና በ13ኛ ዓመቱ ላይ፣ ውሌን ለኢጣልያ የመርከብ ድርጅት (ሶሲየታ ሩባቲኖ) አስተላልፌያለሁ ብሎ በ1882 ላይ ገዝቼያታለሁ የሚላትን አንዲቷን ክፍል ምፅዋን ለኢጣልያ ሰጠ ተባለ።
ወዲያው በዚያው ዓመት፣ በኢስት ኢንዲያ ካምፓኒ ስም ሀገርን በቅኝ መያዝ የለመዱት እንግሊዞች፣ ከግብፅ ጋር ከነበሩበት የባህር ጠረፍ ኦቶማኖችን ፈርተው በመልቀቅ፣ አጠቃላዩን የቀይ ባህር ዳርቻና ምፅዋን ጨምሮ ለጣልያን ሰጥተናል የሚል ቡራኬ ሰጡ። ይሄ የሆነው በ1882 ላይ ነው።
ይህን ባሉ በሁለት ዓመቱ (በ1884) በሱዳን ማህዲስቶች በጭንቅ የተያዙት እንግሊዞች፣ ኢትዮጵያ ተደርባ እንዳትወጋቸውና የባህር ጠረፏን እንዳታሰከብር፣ ጄነራል ሄዊት ተንደርድሮ መጥቶ ከአዮሐንስ ጋር በሄዊት ትሪቲ (ስምምነት) ፈረመ። ኢትዮጵያ ከሱዳን የሚሸሹ እንግሊዞችን በመሐዲስቶች ከመሠልቀጥ ካተረፈች፣ የኤርትራን ዳርቻ ለእናት ሀገሩ ለመልቀቅ።
አፄ ዮሐንስ ተሸወደ። እንግሊዞቹ ከሱዳን ከመሠልቀጥ ተረፉ። መሃዲስቶቹ ኢትዮጵያ ላይ ዘምተው ጎንደርን አወደሙ። አቃጠሉ። ዘረፉ። አፄ ዮሐንስ ያንን ሊበቀል ዘምቶ ሞተ። እንግሊዞቹ ቃላቸውን አጥፈው፣ መጀመሪያ ኦሪየንታል አፍሪካ፣ ከዚያም ኤርትራ ያሉትን የኢትዮጵያን ታሪካዊ የባህር ጠረፍ ግዛት ለጣልያን ፈረሙላት። የራሳቸው ባልሆነ መሬትና ውሃ ላይ ሲፈርሙ ይሉኝታ አይይዛቸውም! ይገርመኛል ሁሌ።
ይሄ ሁሉ ሲሆን ጣልያኖቹ አፄ ዮሐንስ ይሄን እንደማይቀበልና እንደሚወጋቸው ስለሚያውቁ፣ ምኒልክን በአፄ ዮሐንስ ላይ እንዲነሳላቸውና የኢጣልያን የባህር ጠረፍ መብት እንዲያውቅላቸው ሲያግባቡት፣ በመሣሪያ ሲደልሉትና የተለያየ ውል ሲያስፈርሙት ቆይተዋል።
አፄ ምኒልክም ግን አልተዋቸውም። ስድስት ዓመትም አልሞላው ከአፄ ዮሐንስ ሞት በኋላ ኢጣልያኖቹን ለቃችሁ ውጡልኝ ሲልና ሲያስለምን፣ ሲያስጠነቅቅ፣ ሲያሰልል ከነበረ። ግን ምላሻቸው ኢትዮጵያን በሁሉም አቅጣጫ መክበብና ለመውረር መዘጋጀት ነበር።
ፈረንሳይ በጅቡቲ በባቡር ሃዲድ ስም ጅቡቲን ለመቶ ዓመት ኮንትራት ፈርማ ነው የወሰደቻትና ያስቀረቻት። በሶማሌና በኬንያ በኩል እንግሊዝ በየቀኑ አጥር እየፈለፈለች ድንበር ታሰፋለች። ጀርመኖችን ከጣልያን በተጨማሪ በሶማሊያ ሊያመጡም ተስማምተዋል።
ይህ ሁሉ አልበቃ ብሎ፣ ምኒልክ በአድዋው የክተት አዋጅ ላይ በትክክል እንደፃፉት፣ ሀገሩ ደክሟል፣ ሕዝቡ በረሃበበሽታ ተጎድቷል ብለው ጦርነትን ለማስቀረት ቢታገሱት፣ ጣልያን ግን እንደ ፍልፈል በየቀኑ መሬት እየሠረሰረ ከጠረፍም አልፎ ወደ መሐል ሀገር ድንበር ማስፋቱን ቀጠለ። ያም አልበቃ ብሎት መላዋን ኢትዮጵያም ሊይዝ ከጀለ።
እንግዲህ የአድዋ ጦርነት በ1896 እኤአ የተካሄደው በእነዚህ ሁሉ ሂደቶች ውስጥ ነው። የጣልያን ሚሲዮናዊ ቄስ ምፅዋን በ6ሺ ሊሬ ገዛሁ ካለበት ከ1869 የአድዋ ጦርነት እስከተነሳበት የ25ዓመት ታሪክ ነው ያላት ጣልያን በኤርትራ ላይ። ይኸው ነው አጠቃላይ ታሪኩ።
ሌላ ቀርቶ አንዳንድ የባህር ጠረፎችን ለሲራራ ነጋዴዎቻቸው ማሣረፊያ ይጠቀሙ የነበሩ የኦቶማን ጋሻጃግሬዎችና አልፎ አልፎ አገልግሎት እየሰጡ ገቢ የሚሰበስቡ ግብፆች እንኳ፣ ኢትዮጵያውያንን በግዛታችሁ አትተላለፉም የማለት ድፍረቱ ኖሯቸው አያውቅም።
በታሪክም፣ በባህልም፣ በማንነትም ባህረነጋሽ የሚባለው የቀይ ባህር ጠረፍ ሁሉ የኢትዮጵያ አካል እንደሆነ አሳምረው ያውቃሉ።
የግብፆች በሄሮግሊፊክስ የተፃፉ የጦርነት ገድሎች በሙሉ የሚያትቱት ከናይል ማዶ ያሉትን ኢትዮጵያውያንን እንዴት ተዋግተው ወይም ወግተው እንደተመለሱ ነው። እንጂ የኛ ነው፣ ግዛታችን ነው ብለው አያውቁም፣ እንግሊዝ እስክትመጣና በማያገባት ቃሏንና ስምምነቷን ሰብራ፣ ለጣልያኖች ሰጪና ነሺ፣ ካርታ አስማሪ እስከትሆን ድረስ።
ለማንኛውም ኤርትራም ከእናት ሀገሯ ተቆርሳ ለጣልያን አደረች። ሕዝቧም በቅኝ ግዛት ቀንበር ሥር ተላልፎ ተሰጠ። የረዥም ዘመን ታሪካችንና የአንድነታችን ገመድ ሁሉ እንዲበጣጠስ ቅኝ ገዢዎቹ ያልሠሩት ተንኮል፣ ያልጎነጎኑት ሴራ የለም። ደሞ ከኛ በላይ ለኤርትራውያን የሚያስቡ ይመስል እኮ ነው።
ዳን ኮናል በ1993 ባሳተመው መጽሐፉ ሲጠቅስ፣ ጣልያን ከሀገሯ ነጭ ገበሬዎችን አምጥታ ለም መሬቱን ሁሉ ከኤርትራውያን ነጥቃ ለጣልያኖች በሰጠችበት አዋጅ በተመሣሣይ ቀን፣ የነፍስ አድን መድሃኒቶችን ለኤርትራ ተወላጆች መስጠት የሚከለክል አዋጅም ያወጣች አረመኔና ክፉ ቅኝ ገዢ ሀገር መሆኗን ማስረጃ እየጠቀሰ ያጋልጣታል።
ግን ዳን ኮኔል ደሞ የጣልያኑን ውል ፈረምኩ የሚለውን ወስላታ ቄስ ጁሴፔ ሳፔቶን፣ በኤርትራ የኖረበትን ጊዜ ወደ 1937 ያረዝምለትና ከምፅወደ መሐል ስቦ በከረን የኖረ ሰው ያደርገዋል።
ከዚያ ደሞ የዩኔስኮ የታሪክ ሰነድ፣ የፕ/ር ሪቻርድ ፓንክረስት ጥናት ሁሉ በማስረጃ ያረጋገጠውን ጁሴፔ ከአረብ ሡልጣን ምጽዋን ገዛሁ የሚለውን ውል፣ ዳን ኮኔል ልክ በሣርዲኒያ ንጉሥና በኢትዮጵያ መሐል በ1859 የንግድ ውል እንደተፈረመ፣ ቄስ ሳፔቶም የአሰብን ባህር ዳርቻ የጣልያኑን የመርከብ ካምፓኒ በመወከል እንደተረከቡ ይተረተራል።
ይሄም በባህር ጠረፍ አዲስ የጦር ሠፈር ለማቆም አጋጣሚው በተፈጠረለት የኢጣልያ መንግሥት የውስጥ አዋቂ ይሁንታ እንዳገኘ ይናገራል። ዳን ኮኔል የሚለው ሁሉ የተምታታ ነው። ሆነ ብሎም ነው። የሚሲዮኖቹን እኩይ ሥራ ለመሸፈን፣ እና የንግድ ውጤት ለማስመሰል። የእንግሊዝን ስም ከጨዋታው ንባብ ለመፋቅ።
ደዳን ኮኔል የሌለ ታሪክም ይፈጥራል። በገፅ 51 እና 52 ላይ፣ የኤርትራ ሕዝብ በአዲሷ ቅኝ ገዢ ጣልያን የሚደርስበት መከራ አንሶት የትግራይ ጦረኞችም ወደ ኤርትራ እየዘመቱ ከብቶቹንና ያመረተውን በተደጋጋሚ ይዘርፉበት ነበር፣ በማለት የኢጣልያንን አገዛዝ እያብረከረኩ የነበሩ የኢትዮጵያን ሠራዊቶች ዘራፊ ሽፍቶች አድርጎ ያቀርባቸዋል።
ግን ደግሞ ለምሳሌ ከአድዋ ሶስት ዓመት በፊት (ማለትም በ1893 እኤአ ላይ) ከኢትዮጵያ ጋር በማበር ለነፃነታቸው የተነሱ ቁጥራቸው ከደርዘን የሚበልጥ የኤርትራ አርበኞችን፣ ከ800 ተከታዮቻቸው ጋር በጣልያን ጦር እንደተደመሰሱም ደሞ አይክድም።
ዳን ኮኔል ከሻዕቢያዎች ጋር ጫካ የገባ የሲአይኤ ኤጀንት እንደመሆኑ፣ እና በነፃነት ማግሥት የአዲስ የነፃነት ታሪክ ፀሐፊነት (የፀሐፌ ትዕዛዝነት) ማዕረግ የተቸረው ሰው ስለሆነ፣ አጥብቆ የሚፈልገው፣ የኢትዮጵያኖችና ወገኖቻቸው የሆኑት በጣልያን እጅ የገቡት ኤርትራውያን ዝምድናና የዓላማ አንድነት፣ መረዳዳትና በጋራ ጠላታቸው ላይ መነሳት፣ የቆየ ታሪካዊ አንድነታቸው እንዳይነሳበት ነው።
ለማንኛውም በኤርትራም ሆነ በኢትዮጵያ ያሉ ብዙ ታሪካዊ ቅርሶች፣ ሰነዶች፣ የሰዎች ታሪኮች፣ የነገሥታት እንቅስቃሴዎች፣ ባህሎች፣ እና ለቁጥር የሚያታክቱ ማስረጃዎች ሁሉ የሚያሳዩት የኤርትራንና የኢትዮጵያን ሕዝብ አንድ መሆንና በአንድ ግዛት ሥር ሲተዳደሩ የቆዩ ሕዝቦች መሆናቸውን ነው።
እነ አይተ ኢሣያስ ያንን የረዥም ዘመን ታሪክ ክደው፣ ልዘለዓለም ዓለማቸውን በጣልያን ሥር ሲገዙ እንደኖሩ፣ ሲገልፁ ሳይ እገረማለሁ። ደሞ የሚክዱት ተቃራኒ በሆነ መንገድ ነው።
አንደኛ ምኒልክ በውል ተስማምቶ ለጣልያን ሸጠን ይላሉ። ልክ እንደ ፕሪምየር ሊግ ተጫዋች ዝውውር ያደርጉታል ራሳቸውን። ምኒልክ መቼም ከሸጠ፣ የራሱ ያልሆነውን አልሸጠም። እነሱም ሲሸጡ፣ ሲለወጡ ኖረዋልም ማለነው።
ግን እንዲህ ብለን እንዳንወስደው ደሞ፣ በኢትዮጵያ ሥር ተዳድረን አናውቅም፣ የኢትዮጵያ አካል ሆነን አናውቅም፣ የጋራ ያደረገን ታሪክም የለም፣ በፌዴሬሽን ተዋሃዱ የተባልነውም፣ ፓርላማችን ራሱን አፍርሶ በንጉሠ ነገሥቱ ሥር የገባነውም በጉልበት ነው ይላል። ግራ የገባው ቅጥፈት። እሺ እኛ የትኛውን እንመን?
በጣም የሚያስገርመኝ፣ አውሮፓውያኑ ቅኝ ገዢ ሴረኞች እና የአረብ ጋሻ ጃግሬዎቻቸው (“ኢምፔሪያሊስቶቹ ኃይሎችና ቅጥረኞቻቸው” ይላቸዋል ማሞ ውድነህ ሁሉንም አጠቃልሎ)፣ ኢትዮጵያውያንን እርስ በርስ ለመበታተንና ለመለያየት ያለ የሌለ የውሸትና የእውነት ታሪክ መዓት ሲገምዱ፣ ከዓለም ጦርነት ማብቃት መግሥት “ኢትዮጵያውያን ናችሁ? ወይስ የተለያችሁ ኤርትራውያን?” የሚል ሴረኛ ጥያቄ ይቀርብላቸው የነበሩ ኤርትራውያን ወጣቶች ግን፣ አደባባይ ይዘው ይወጡ የነበሩት መፈክር፦ “ኢትዮጵያውያን መሆናችንን ታውቁታላችሁ፣ ለምን ትጠይቁናላችሁ?” የሚል ነበር።
ለማንኛውም አጠገባቸው የቆመውን የአክሱም ሀውልትና የፅዮን ማርያም ቤተመቅደስ ከነታሪካቸው ክደው፣ ታሪካችንን በመቶ ዓመት ያሳጠሩትም ሆኑ፣ በሌባ ሚሲዮናዊ ቄስ የተጭበረበረ ሰነድ ታሪካቸውንና ማንነታቸውን ለጣልያን አስረክበናል ያሉትም፣ ሁለቱም፣ ሀገርን ጎነዳደሹ፣ ለውጭ ጠላቶች መጠቀሚያ የትሮይ ፈረሶች ሆኑ፣ ዓለም ኮስተር ብሎ ለሕዝቡ ለውጥ ያመጣዌን ሥራ በሠራበት ክፍለዘመን፣ ሀገራችንን በጦርነት ጠምደው ሕዝባችንን እርስ በርሱ አጫረሱ፣ አሁንም አባልተውን እየተባሉ ነው፣ እንጂ ማናቸውም ሆነ ማናችንም ያተረፍነው ነገር የለም። አልነበረም። ሊኖርም አይችልም።
ይሄን እውነት የሚረዱ የወደፊት ትውልዶች የሸፍጥና የመለያየት ታሪካችንን ይቀይሩት ይሆናል። የወደፊቷ ምድራችን እርሰበርስ የተያያዙ መጪውን ያዩ፣ የቀደመውንም ያልረሱ ነቄ ትውልዶች የሚነሱባት ምድር ትሆን ይሆናል።
ዛሬ አብረው፣ ጠንክረው የተገኙት ቻይኖች ሆንግኮንግን የመቶ ዓመት ኮንትራቷ ሲያበቃ፣ ከእንግሊዝ ላይ መንጭቀው አስተፍተዋታል። እኛ በወያኔና ሻዕቢያ፣ በዚያድባሬና በኢህአፓ፣ በመንግሥቱ ኃይለማርያምና በሺዓይነት መዓተኛ ቅርቃሮች ተቸንክረን፣ ለመቶ ዓመት ለፈረንሳይ የሰጠናትን ጂቡቲን ተቀምተን ቀረን።
“ቸንክሮ የያዘሽ ካስማውና አዉታሩ
ዓይነቱ ብዙ ነው ባድባሩ ባውጋሩ
ከቶ እንዴት እናርጊሽ ልንፈታሽ ከሥሩ።”
– ገሞራው (ኃይሉ ገብረዮሐንስ)
ቸንክሮ የያዘን ካስማውና አውታሩ ብዙ ነው። አውጋራችንን አድባራችንን የተተበተብንበትን ስንክሣር ሁሉ አንስተንም አንጨርሰው። ይህን የተተበተበ ቋጠሮ የሚፈታልን አንድ ነቄ፣ ብልህ፣ አዋቂ፣ ብርቱ ትውልድ እንዲያስነሳልን ብቻ እመኛለሁ ለዚህች ያልታደለች ምስኪን ሀገር። እና ሕዝቧ!
አበቃሁ Assad Hailu