– ሲጥል ላይ ያለውን ሁሉ ጣለ
ሲጥልን አነበብኩት። ተገርሜም ተደንቄም አድንቄም አልበቃኝ። ደራሲው አልሰሰተም። ከጎረምሳነቴ ጀምሮ የማውቀው ደራሲ ነው። በግልም አውቀዋለሁ። እንደ ሰው። ንግግሩ ብዙ ፍሬ እንዲሁም ጨዋታና ቁምነገር አዘል ነው። ብዕሩን ከሞላ ጎደል ሁሉንም አንብቤያለሁ። ከምንም በላይ ‘በዐሉ ግርማ ሕይወቱና ስራዎቹ” ግርም ድንቅ ብልበትም ከ”ጥቁር ሰማይ ስር” ስስቴ ነው። ይህን ስል ከጣት ጣት ይበልጣል ለማለት ነው። ግን ሌላ የሚበልጥ ጣት አገኘሁ። ሲጥል!
በግል የማውቀውን እንዳለጌታን አየሁት። እንዳለጌታ ስስታም አይደለም። ለታናናሾቹ ትሁት ነው። ወዳጅ ነው። ሳይሰስት ይሰጣል። ያማክራል ይመክራል። እውነት ለመናገር በአንዳንድ የእሱ ዘመነኞች ቅሬታዎች አሉኝ። እሱ ከዘመነኞቹ ከሚለዩት አንዱ ይህ ነገሩ ነው። የ”ያ ትውልድ” ጥላ በደንብ ያረበባቸው ትምክህተኞች ይበዙበታል። በረኝነት። ማለፉ ላይቀር መተሻሸት። ማሸት። ደባሪ ሙድ! “አናስገባም ሰርገኛ እደጅ ይተኛ” ነገር። እንዳለጌታ ጋ ፒስ ነው። ግን እውቀቱን ማካፈሉ አይደለም ለጋስነቱ። ካለው ያለውን ሁሉ ይሰጣል። መጽሐፍ ይለግሳል። ለተማሪዎች ገንዘብ፣ ቀለብ ይሰፍራል። ነድያንን ያበላል። የሰርጉእለትም ቢሆን።
ሲጥል ላይ ያለውን ሁሉ ሲጥል አየሁት። እንደ ደራሲ ለነገ የሚባል ሃሳብ አለ። የዛሬው ይበቃል። ደግሞ ለነገዬ ይባላል። ደንብ ነው። ደራሲ ሰው አይደለ? ለደራሲም ነገ አለው።
ሲጥል ላይ ለነገ አልነበረም። ለነገ ሳይል ሳይሰስት ነበር ያስነበበን። ልክ እንደ ባለጠገ ቤት ማዕድ። ዞረው ዞረው የማይጨርሱት የታሪክ ብፌ ያቋደሰን። ደራሲው ፈጣሪን ካልፈራ ሦስት ደንበኛ ልብወለድ ሊጽፍባቸው የሚችሉ ታሪኮችን ነው አንድ ያደረጋቸው።
የቤርሳቤህ እና የምንተስኖት ታሪክ፣ የኢዮኤልና የመሪጌታ ሐብቴ ታሪክ እና የአቶ ስዩምና የተቀሩት ሰዎች ታሪክ ብቻ ብቻውን መጽሐፍ መሆን ይችላል።
እነዚህ ሶስት ትልልቅ ልብወለድ የሚወጣቸውን ግብብዳ ገጸ ባህሪያትና ታሪኮች አንድ ሲያደርጋቸው ግን አንረበሽም። በምን ተገናኙ አንልም። ምን እግር ጣላቸው ብሎ መጠየቅ መብት ቢሆንም። እግር ይጥላል። ሲገናኙ ግን ግጥም ይላሉ። ጸባቸውም ፍቅራቸውም ምክንያታዊ ነው። ይህን ነው ቴክኒክ የሚሉት።
የስነ ጥበብ ሰዎች አንድን የሥነጥበብ ውጤት በሁለት አይን ያዩታል። ቅርጽና ይዘት (form and content)። ምንም የኪነጥበብ ስራ ከዚህ አያልፍም ይላሉ ሊቃውንቱ። ይዘቱና አቀራረቡ።
አንዳንዶች ቅርጽን እንደ ጆግ፤ ይዘትን እንደ ውሃ ያዩታል። እናም ውሃው እንጂ ጆጉ ምንድነው ይላሉ። አ አ….ግን ቅርጽ በጆግ አይመሰልም። ብዙ ቁምነገር፤ ብዙ ሃሳብ ቢታጨቅ ያለ ቅርጽ ያለ ማቅረቢያው ውሃውስ በምን ሊያዝ ሃሳብስ በምን ሊቀነበብ?
ሲጥል ውስጥ አንድ ነው የሚባል አጻጻፍ የለም። አጻጻፉም እንዲህ ነው የሚባል አይደለም። በአንድም በሦስተኛውም መደብም ይተረካል። ዛሬም፣ ነገም፣ ትናንትም አለ።
“…ትናንትናን ያየ ስለ ነገ ያውቃል
ታሪክ ያስተዋለ ከጠቢብ ይልቃል…” ትላለች በዛወርቅ አስፋው ። ” if you want to hear deeply melacholic version of Tezeta listen to Bezawerke’s…” የተባለላት ነች። ያውም ቢቢሲ ዶክመንተሪ ላይ።
እና ሲጥል ላይ በእውን አለም ላይ የምናውቃቸው ሰዎች በገጸ ባህሪያት ይጠቀሳሉ። ራሱ ደራሲውም “የትምጌታ” በሚል ስም ተጠቅሷል (ይቺን ስታይል “ልጅ ማይክ፣ ሮፍናን ድሮፕ ኢት አጌይን፣ ቴዲ አፍሮ ማሚላ ኪችን ምናምን ምናምን…” ሲሉ ነው የማውቀው። ኦው ደራሲውም ፈታ እያለ ነው። እንዳለጌታም ስሙን ጠርቷል ደራሲ በሚለው ቦታ አላልኩህም ደግሞ። በፈጠራቸው ገጸባህሪያት ነው እንጂ። “የትም ጌታ” የሚሉት ጋሽ ኃይለመለኮት ናቸው። ሲባል ሰምቻለሁ። አዳም ረታም ስሙ ተነስቷል። ዶክተር በድሉ፣ ዶክተር በላይ አበጋዝ እና ዶክተር ፈቃደ አግዋር (እኒህ የልብ ሐኪምች ናቸው። በእውኑ ዓለም ያሉ የምናውቃቸው፤ የመጀመሪው የስነ ጽሁፍ ሰው ናቸው።)
ደራሲው የእነዚህን ሊቃውንት ስም በልብወለዱ ጠቅሷል። እና ይጠራአ ምን ይጠበስ? አይባልም። አባዬ ይጠራአ ምናምን ብለህ እንዳታቃልል። ምን ሆነሃል? ትላልቅ ዘፋኝና ደራሲ ስምህን በስራው ላይ ሲጠራህ በትንሹ ሰባና መቶ አመት ስምህ ከአየሩና ከሼልፉ ላይ አይጠፋም። ማነው ምንድነው ይልሃል? ትውልዱ። አትናቀው የስምን ነገር። ጥቅሙን ዶክተር አብይን ጠይቃቸው። ቴዲ አፍሮ ለምሳሌ “ጎንደር ጎንደር ” ባለ አንደበቱ “አብይ አብይ አሻገርን ንጉስ የበላይ ነውና” ቢል… ቢል? አባዬ የጫካ ሲሶ የእሱ ነበር። ከጫካ ፕሮጀክት በላይ የልጁ ዘፈን ዘመን ይሻገራላ።
“ነይ እንሳፈር ነይ እንሳፈር
የምድር ኃላፊ ነው በሰማይ ባቡር
እድሜ ለተፈሪ አሳየን ታምር
ከተወለድን ቆየን ከቆየን ዘገየን
እድሜ ለተፈሪ አውሮፕላን አየን” አሁን ይሄ ስንኝ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ስም ቀድሞ ተፈሪ መሆኑ። አውሮፕላን ለኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በታሪክ ማመጣታቸው ከሚነግርህ በላይ አየር መንጉዱ ላይ በእግር በፈረስ ብትለፋ የቱጋ ነው የቀኃስ ታሪክ አይደለም ፎቶ የምታገኘው? እና ዘፈን ድንቅ ነው ነው ምልህ።
ከፈለክ ጠቢቡ ሰለሞንንም ስለ ስም ጠይቀው። በነገራችን ላይ ዶክተር አብይና ጠቢቡ ሰለሞን ሊዮ ናቸው። ነሐሴ ወር ነው የተወለዱት። እና ጠቢቡ ሰለሞን “መልካም ስም ከብዙ ባለጠግነት ይሻላል፤ መልካም ስምም ሞገስ ከብርና ከወርቅ ይበልጣል” ይላል። እስቲ ሂሳቡን ስራው አለ አማክሮ ኗሪው ሰውዬ።
ብቻ ምን አለፋህ ይህንን አጻጻፍ ነው ሊቃውንቱ ድህረ ዘመናዊነት (Postmodern literature) የአጻጻፍ ዘዬ ‘ሚሉት። የምናውቀውን የልምድ ነውን የእውኑን አለም ማፋለስ። ልብወለድ ነው ሲሉ እውን እውን ነው ሲሉ ልብወለድ (metafiction)።
ሀገር እንዲህ ነው ሚሰራው። ቴዲ አፍሮ እንዲህ ነው ትላልቅ አድባር እየሳበ ሀገሪቱን ባንድ ሊያስር ሁለት አስርት አመታትን ያሳለፈው። ጥበብ መከራ ነው። ቀንበር ያሸክማል። እዳ አለበት ዋጋ ታስከፍላል። እንዳለ ጌታ ይህንን ጠንቅቆ ያውቃል። የበአሉን የሕይወት ታሪክ መጻፍ ብቻውን ብዙ ያስተምራል።
የኪነጥበብ ሰው በግል ሳይሆን እኛ እያሉ ማሰብ የሚያስገድድ ሙያ ነው። የኪነጥበብ ሰው ይታመናል። ሕዝብ ያምነዋል። ተደራሲ ይከተለዋል። እምነት ካለ ጥንቃቄ ግድ ነው። የጋራ የሆነ ነገር ውስጥ መሳቀቅ አለ። እንደ እኛ ያለ ሀገር። ሁሉ ፖለቲካ ለሆነ ማኅበረሰብ። ሁሉ ጽንፍ። ሁሉ “አዋቂ” ለሆነበት ሀገር ረባሽ ነው። ጥበብ ትጨነቃለች። ጠቢብም ይሳቀቃል።
እንዳለ ጌታን ደብረ ሰምራን በዛጎል ጀምሮ በሲጥል ያቆያት፤ አሊይን በሲጥል ያመጣት። እንደ ልቡ ለመናገር ይሆን? ወይስ ስልት?
ደራሲው ሲኒየር ነው። እንደልቡ መናገር ፈልጎ አይደለም። ልክ በሙያው እንደሸበተ ካፒቴን ያለመንገራገጭ ነው ታሪኩ ላይ ቁጭ የሚያደርግህ። የት ጀምረህ የት እንደምታርፍ በጥንቃቄ ካልተከታተልክ እየበረርክ ይሁን እንዳረፍክ ምታውቀው ካፒቴኑ በሰላም ደረሰን ካላላ በስተቀር። በማይክ።
ሲጀመር በጥበብ እንደልብ ምናምን ብሎ ነገር የለም። ጥበብ ጥበብ ነው። እና ደራሲው ሲጠበብ ነው አሊይ ደብረሰምራ ምናምን ‘ሚለን። ድኅረ ዘመናዊነት። በቃ ተጠቦ ነው የጻፈው። ሳይሰስት ነው የለገሰን። ሲጥልን ሲጥልህ እጅህ ሲገባ እንደው እንደ አልፎ ሂያጅ አታነበውም። ቀልብ ገዝተህ ነው ሲጥልን ምታነበው። ሲጥል!

Vua – dire tube