“ኖላዊት ዘገየን ገደሏት፤ ከሞቷ አማሟቷ ልብ ይሰብራል” ቤተሰብ
ከእናቷ ጡት እና ጡጦ በቀር የምታውቀው የሌላት የሁለት ዓመት ህጻን ናት፤ ኖላዊት ዘገየ። ይህችን የዚች ዓለም እንግዳ በሰው እጅ መገደል ሌላ ትርጉም መስጠት እንዴትስ ይቻላል?
አባቷ በግል ድርጅት የተቀጠሩ ሾፌር፤ እናቷ ደግሞ ፀጉር ቤት ውስጥ የሚሠሩ ምስኪን ናቸው ይላሉ ለአሚኮ መረጃውን የሰጡት ቤተሰብ።
አርብ በ24/12/2016 ዓ.ም ረፋድ 3:30 ሰዓት አካባቢ ከግቢ ውስጥ እያለች ተሰወረች። ህጻኗ ከግቢ የመውጣት አቅም እንደሌላት በመሰወሯ ቤተሰብ፣ ዘመድ አዝማድ እና ጎረቤት ተጨንቀዋል።
የፍለጋው ሂደት ከላይ ከታች እየተባለበት ነበር የሚሉት ቤተሰብ ባነር ተዘጋጅቶ በከተማዋ ሁሉ ተሰራጨ። በመካከል ግን ለአባቷ የስልክ ጥሪ መጣ “ልጅቷን አግተናት ከእኛ ጋ ነች፤ የተሰበሰበውን ሰው በትኑ፤ ለፖሊስ ከተናገራችሁ ግን እንገድላታለን” የሚል ማስፈራሪያም፤ ማስጠንቀቂያም ደረሰ ይሉናል።
የተያዘችው ህጻን በመኾኗ “አለች” የሚለው መረጃ የደረሳቸው ቤተሰቦች ህጻኗን በሕይዎት የማግኘት ተስፋ አድሮባቸዋል የሚሉት አስተያየት ሰጪው ቀጣይ የሚመጣውን የስልክ መረጃ በጭንቀት እየጠበቅን ነበር ይላሉ።
የሚጠበቀው ስልክ ድጋሜ ተደወለ፤ አጋች ተብየዎቹም ህጻኗን ለቤተሰቦቿ ለማስረከብ 1ሚሊየን ብር ጠየቁ። ይህ ለድሃ ቤተሰብ ያውም በድንገት የሚቻል ብቻ ሳይኾን የሚታሰብም አልነበረም። ድህነታቸውን ገልጸው እንደማይችሉ የጠየቁት አባት ቢያንስ የገንዘብ መጠኑን እንዲቀንሱ እና ህጻኗን እንዲለቋት እየተማጸኑ ነው።
አጋቾቹ ከአንድ ሚሊየን ብር ወደ 5 መቶ ሺህ ብር ዝቅ አሉ። አሁንም የተጠየቀውን ብር መክፈል ያልቻሉት ቤተሰቦች በአንድ በኩል የተጠየቀው ብር እንዲቀንስላቸው፤ በሌላ በኩል ደግሞ ገንዘቡን የማሰባሰብ ሥራ ላይ ናቸው። በመጨረሻም 2 መቶ ሺህ ብር በእጃቸው እንደያዙ ገልጸው፤ የያዙትን ብር ተቀብለው ህጻኗን እንዲለቁ ተማጽኖ ላይ ናቸው።
በመጨረሻም የቀረበላቸውን ብር በባለሦስት እግር ተሽከርካሪ (ባጃጅ) የተቀበሉት አጋቾች ህጻኗን ከእነ ነብሷ ይመልሷታል ተብለው ሲጠበቅ ገድለው በወላጇቿ ጓሮ ዛሬ ጥለዋት ተገኙ ይላሉ።
“ኖላዊት ዘገየን ገደሏት፤ ከሞቷ አማሟቷ ልብ ይሰብራል” የሚሉት ለአሚኮ በስልክ መረጃ የሰጡን ቤተሰብ የህጻኗ አስከሬን በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል ምርመራ እንደተደረገለት ነግረውናል። ዛሬ ምሽት አካባቢ ሥርዓተ ቀብሯ ተፈጽሟል ብለውናል።
መንግሥት ጉዳዩን ተከታትሎ ፍትሕ እንዲያሰፍንም አስተያየት ሰጪው ቤተሰብ ጠይቀዋል።
(አሚኮ)