ጫካ ያለውና ራሱን የኦሮሞ ነጻ አውጪ እያለ የሚጠራው ታጣቂ ቡድን ለሁለት መሰነጠቁን የአንደኛው ቡድን መሪ የሆኑት ጃል ሸኚ ይፋ አደረጉ። ቀደም ሲል ጀምሮ መግባባት እንዳልቻሉ በተለያዩ ጊዜያት ሲነገር ነበር። ውዝግባቸው በስልክ የቃል ልውውጥ ሳይቀር ይፋ መደረጉና ወገን ለይተው መዋጋታቸውም ይታወሳል።
” በኦሮሚያ ያለውን ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት እኛ ዝግጁ ነን ”
” በጃል መሮ (ኩምሳ ድሪባ) ከሚመራው የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ራሳችንን አግልለናል ” ሲሉ የማዕከላዊ ዞን የቀድሞ አዛዥና የድርጅቱ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ጃል ሰኚ ነጋሳ በይፋ ያስታውቁት ለቪኦኤ አማርኛ ነው። የኦሮሚያ ክልል ሸኔ የሚለው ይህ ታጣቂ ቡድን ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ እንደ ድርጅት መንቀሳቀስ በማይችልበት ደረጃ መድረሱንና በወራት ዕድሜ ውስጥ ሙሉ በሙሉ እንደሚከስም ሰሞኑን ማስታወቁ አይዘነጋም።
ከተመረጡ መገናኛ ብዙሃን ጋር በስልክ ቆይታ ያደረጉት ጃል ሰኚ ባለፈው ረቡዕ ዕለት ወጥቶ ሲዘዋወር የነበረው የማዕከላዊ ዞን ዕዝ በጃል መሮ ከሚመመራው ቡድን መነጠሉን የሚገልጸው መግለጫ አስመልክቶ ” አዎ የኛ የቡድናችን ነው ” ሲሉ ማረጋገጫ ሰጥተዋል። ቪኦኤ የተመረጡ የተባሉት መገናናዎች ግን አልተዘረዘሩም።
ጃል ሰኚ ፥ ” የኦሮሞ ነጻ አውጪ ሰራዊት ህግና ደንብ መተዳደሪያ ደንብ የሌለው ድርጅት ነው ” ብለዋል። “ጥፋት ሲሰራ ተጠያቂነት የሌለበት ድርጅት ነው፣ ህግና ደንብ ሲኖር አንዱ ሲያጠፋ ለማስተካከል የሚያስችል ህግ ይኖራል ግን አሁን በአንድ ሰው የሚመራ መሆኑን አይተንና ተረድተን እንዲሁም ወደ ድርጅቱ ህግና ደንብ ተመልሰን እርስ በእርሳችን እናስተካክል ብለን ለኦሮሞ ህዝብ ባለን ክብር ባህልና ወጉን ጠብቀን ነው በህዝቡ ውስጥ የምንቀሳቀሰው ከዚህ ባለፈ በህግ ሊታይ ይገባል፤ በድርጅቱ ጠቅላላ ጉባኤ በ2017 በተደነገገው ህግና ደንብ መመራት አለብን ብለን ከኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት አመራር ጋር መቀጠል አንችልም ብለን ነው መግለጫ ያወጣነው ” ሲሉ ተናግረዋል።
” አሁን ዋና አዛዥ የምንለውን ወደፊት ኦሮሚያ ውስጥ ከሚንቀሳቀሱ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት አባላት ጋር ተነጋግረን ነው የምንመርጠው ፤ ስለዚህ ከዚህ በኃላ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት አይወክለንም ” ብለዋል። ጃል ሰኚ በኦሮሚያን ያለውን ግጭት በሰላም ለመፍታት ፈቃደኛ መሆናቸውን ሲገልጹ ” እኛ ዝግጁ ነን” በማለት ነው።
” በሰላማዊ መንገድ ስንል በድርጅቱ ፕሮግራም የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር የቀጠለውን አለመግባባት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ሁሉም ይታትራል። ስለዚህ መንግሥት ከሰላማዊ መንገድ ከእኛ ጋር ለመነጋገር ዝግጁ ከሆነ እኛም ለመነጋገር ዝግጁ ነን ፤ እንዴት ነው የምንነጋገረው ? የት ነው ? ከማን ጋር ? የሚለውን የውይይቱ ጊዜ ሲደርስ ይገለጻል ” ብለዋል።
አሁን ላይ ከመንግሥት ጋር ድርድር እየተደረገ እንደሆነ ተጠይቀው ” አሁን ከመንግሥት ጋር የጀመርነው ግንኙነት የለም ” ሲሉ መልሰዋል። ቪኦኤአፋንኦሮሞ