ለሰው ሰው ነው መድኃኒቱ በሚባልባት ሀገር፣ የአንደኛው ነውር ሌላኛው በሚሸፍንበት ምድር፣ አንደኛው ለሌላኛው ጥላና ከለላ፣ መሰሶና ባላ በሚኾንባት ሀገር ወንድም በወንድሙ ላይ ስለ ምን ተነሳ?
ለሰው ሰው ነው መድኃኒቱ ይባል እንዳልነበረ ለሰው ሰው ለምን አጥፊው ኾነበት? ያሳደጉትን እንስሳ አንሸጥም፣ አንለውጥም፣ ወደ ገበያ አንወስድም እያሉ በሚሳሱ ደጋጎች ምድር ስለ ምን የሰው ልጅ ታፍኖ ለገበያ ወጣ? ለምንስ ገንዘብ ተጠየቀበት?
ፍቅር የሞላባት፣ ሰላም የበዛባት፣ ፍትሕ የሰፈነባት የተባለች ሀገር ስለ ምን ሰላም አጣች? የተቅበዘበዙትን የሚረጋጉባት፣ የተራቡ የሚጠግቡባት፣ የታረዙ የሚለብሱባት፣ መጠጊያ ያጡ የሚጠጉባት፣ ሀገር እና ወገን ያጡ ባሕር አቋርጠው መጥተው እንደ ሀገራቸው የሚኖሩባት ሀገር ዛሬ ላይ ስለ ምን ለልጆቿ የፈተና ምድር ኾነች?
ልጆች ቦርቀው የሚያድጉባት፣ አረጋውያን በደስታ የሚያመሹባት፣ ታሪክ እያስተማሩ ትውልድ የሚመርቁባት በተባለች ምድር ስለ ምን ሕጻናት መውጫ መግቢያ አጡ? ለምን የሚቦርቁባቸው ሜዳዎች አስፈሯቸው? ለምንስ ከቤት ለመውጣት ሰጉ?
መታገት በዝቶባቸዋል፤ እየታሰሩ ገንዘብ አምጡ መባል ሰልችቷቸዋልና ዛሬ ላይ ሕጻናት በአንድነት አይጫወቱም፡፡ ወላጆች ያለ ስጋት ተኝተው አያድሩም፡፡ ከአንደኛው አካባቢ ወደሌላኛው አካባቢ በነጻነት አይጓዙም፡፡ ባለሃብቶች በሃብታቸው አያጌጡም፡፡ በሃብታቸው አይደሰቱም፡፡ ይልቅስ ሃብታቸው እየተቆጠረ ገንዘብ አምጡ እየተባሉ ይሳደዳሉ፣ ይንገላታሉ፤ አንስጥም ሲሉ ይገደላሉ እንጅ፡፡ አያሌ ችግሮችን በጋራ ያለፉ ይሄን መከላከልና ማስቀረትስ ለምን ተሳናቸው?
በአማራ ክልል የእገታ ወንጀል ከጊዜ ወደጊዜ እየተባባሰ መጥቷል፡፡ በክልሉ የተፈጠረው ግጭት ደግሞ እንዲባባስ አድርጎታል፡፡ በክልሉ እየታገቱ ገንዘብ የሚጠየቅባቸው ወገኖች በዝተዋል፡፡ የጸጥታ ኀይሎች እገታን ለማስቀረት በየቀኑ ጥረት ያደርጋሉ፤ ነዋሪዎችም እንዲኹ፡፡ ነገር ግን የእገታ ወንጀልን መቋቋም አልተቻለም፡፡
የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የሚዲያ ኀላፊ ምክትል ኮማንደር መሳፍንት እሸቴ በአማራ ክልል የለየለት ግጭት ከተነሳ ጊዜ ጀምሮ የሕግ አስከባሪ ተቋማት ሁለት ዓይነት ፈተናዎች ገጥመዋቸዋል፣ አንደኛው ሕግ እና ሥርዓትን በማስከበር ኅብረተሰቡ በሰላም ወጥቶ እንዲገባ ማድረግ፣ ሁለተኛው ደግሞ የታጠቁ ኀይሎች የሚከፍቱበትን ጥቃት መመከት ነው ይላሉ፡፡ የገበያ ግርግር ለሌባ ይመቻል እንዲሉ በክልሉ የተፈጠረው ግጭት ወንጀሎች እንዲበራከቱ አድርጓል ነው የሚሉት፡፡
የተፈጠረውን ግጭት ምክንያት በማድረግ ገንዘብ የሚፈልግ ሁሉ የተለያዩ የወንጀል ድርጊቶችን ይፈጽማል ይላሉ፡፡ በክልሉ እያገቱ ገንዘብ የመቀበል ወንጀል ሥር እየሰደደ ነው፣ ለሕጻናት ሁሉ የማይራራ አስከፊ ወንጀል እየተፈጠረ ነው፣ በርከታ ሰዎች በየቀኑ ለእገታ ወንጀል ሰለባ ይኾናሉ ነው ያሉት፡፡ የጸጥታ ተቋማት ከሚቀርቡ ጥቆማዎች እና ከሚደርሱ ወንጀሎች ባለፈ ኅብረተሰቡ በራሱ መንገድ ለማስለቀቅ ጥረት የሚያደርግባቸው በርካታ ወንጀሎች መኖራቸውን አንስተዋል፡፡
የእገታ ወንጀል የጸጥታ ችግሩ ከመፈጠሩ አስቀድሞ መጀመሩን የሚያስታወሱት ኀላፊው በተለይም ግጭቱ ከተነሳ ወዲህ እንዲህ ዓይነት ድርጊቶች በሁሉም የክልሉ አካባቢ የብር ማግኛ መንገድ ኾነው ማኀበረሰቡን እያማረሩ ነው ይላሉ፡፡ የእገታ ወንጀሉ ፖለቲካዊ ጥቅም ለማግኛ ይኹን የግል ጥቅምን ለማሳካት ለሕዝቡ ግን ሰቃይ ኾኗል ነው የሚሉት፡፡
እገታ ከመፈጸሙ አስቀድሞ፣ በመፈጸም ሂደት ላይ፣ ከተፈጸሙ በኋላ በክትትል የጸጥታ ኀይሉ በየቀኑ የእገታ ወንጀሎችን እና ሌሎች ወንጀሎችን ያከሽፋል፤ ነገር ግን ይሄም እየኾነ ሙሉ ለሙሉ መቆጣጠር አልተቻለም፡፡ ይሄን ያመጣው ደግሞ በፖለቲካው ብልሽት ምክንያት የጸጥታ ኀይሉ ከማኅበረሰቡ ጋር የነበረው ግንኙነት ሻክሯል፤ ኅብረተሰቡ ከፖለቲካ እና ከፖለቲከኛው ጋር ችግር ሊኖርበት ይችላል፤ ይህ ደግሞ የጸጥታ ተቋሙን ከነካ ሌላ ችግር እንዲመጣ ያደርጋል ነው ያሉት፡፡ የፍትሕ ሥርዓቱን የሚጠብቅ ተቋም መፍጠር ካልተቻለ ማንም ጉልበተኛ እየመጣ በየቤቱ ዘግናኝ ወንጀሎችን ይፈጽማል ይላሉ፡፡
በፖለቲካው ችግር ምክንያት ኅብረተሰቡ ሕግ አስከባሪውን ጠቅሎ የፖለቲካ አሥፈጻሚ አድርጎ በማሰብ አብሮ ያለመሥራት ችግሮች ተፈጥረዋል፤ ከዚያም አልፎ በጸጥታ ኀይሎች ላይ የተለያዩ ጥቃቶች ተፈጽሞባቸዋል፤ በማኅበረሰብ አቀፍ የፖሊስ አገልግሎት የነበረው ጥብቅ ግንኙነት ተቋርጧል፤ ቁሳቁስ አሟልቶ ፖሊስ መድቡልን ሲል የነበረው ልምድ ቀርቷል ነው የሚሉት፡፡ አንድ ፖሊስ የጦር መሳሪያ ሳይዝ ከኅብረተሰቡ ጋር ሰላምን የሚያስከብርበት ጊዜ ነበር፣ ይህ ግንኙነት በፖለቲካው ችግር ምክንያት እየተበጣጠሰ ሲሄድ ግጭት እየጠመቁ ገንዘብ ለሚሠበሥቡ አካላት የተመቸ ኾነ ይላሉ፡፡ ይሄም የጸጥታ ኀይሉ በየቀኑ የሚያከሽፈው ወንጀል የበለጠ እንዳይጎላ አድርጎታል ነው ያሉት፡፡
በተለይም በክልሉ ግጭት እንደተከሰተ ለፀጥታ ኀይሉ ሲሰጥ የነበረው እይታ የተዛባ ነበር፤ በማኅበረሰቡ እና በፀጥታ ኀይሉ መካከል ያለው ክፍተት ደግሞ ወንጀልን በተሟላ መንገድ ለመከላከል አላስችል አለ ይላሉ፡፡ አሁን አሁን ግን ለፀጥታ ኀይሉ ሲሰጥ የነበረው የተዛባ አመላከከት እየተስተካከለ መጥቷል፤ ከፀጥታ ኀይሉ ጋር አብሮ የመሥራት ፍላጎቱ እና ሂደቱ እየጨመረ መጥቷል፤ ይህ ደግሞ ለፀጥታ ኀይሉ ጉልበት ነው ብለዋል፡፡
ፖለቲካን ከተቋማት ጋር የማቀላቀል ልምምድ መቀየር መቻል አለበት፤ በዚህ ምክንያት የፀጥታ ኀይሉ ዋጋ እየከፈለ ነው ኅብረሰተቡ ይሄን ሊያውቅ ይገባል ነው የሚሉት፡፡ ሥነ ምግባር የፖሊስ ኮሚሽን የመጀመሪያው ተግባር ነው የሚሉት ኀላፊው የፖሊስ ሙያዊ ሥነ ምግባር የተስተካከለ እንዲኾን በትኩረት ይሠራል፤ ከሥነ ምግባር ባፈነገጡ አባላት ላይም ርምጃ ይወስዳል ነው ያሉት፡፡
ችግሮችን ለመፍታት ስክነት ያስፈልጋል፤ ኅብረተሰቡ ፍትሕን የመፈለግ ስሜቱን በተግባር ማሳየት አለበት፤ ለፍትሕ የሚከፈለውን ዋጋ መክፈል ይጠበቃል ብለዋል፡፡ በጋራ መሥራት፣ ተቋምን ከግለሰቦች የመነጠል ልምምድ ሲያድግ ችግሮችን መፍታት እንደሚቻልም አንስተዋል፡፡ በጉቦ አገልግሎት የሚሰጡ፣ ሥልጣንን ያለ አግባብ የሚጠቀሙ የፀጥታ አካላት አሉ፣ በተደረሰባቸው እና በተረጋገጠባቸው ጊዜ ያለ ምንም ማቅማማት ርምጃ ይወሰድባቸዋል ነው ያሉት፡፡
ማኀበረሰቡ በእገታ እና በሌሎች ወንጀሎች እየተማረረ መምጣቱ፣ ፍትሕን መፈለጉ እና ከጸጥታ ኀይሉ ጋር መቆሙ ሥራዎችን እያቀለለ፣ ወንጀል የመከላከል አቅምን እያሳደገ እና እያሰፋ ይሄዳል ብለዋል፡፡ ፖሊስ በእገታ ወንጀል የተጠረጠሩ አካላትን በቁጥጥር ሥር በማዋል ፍርድ እንዲሰጥባቸው ማድረጉንም አንስተዋል፡፡ በርካታ ወንጀሎችንም ማክሸፋቸውን ነው የተናገሩት፡፡ ማኅበረሰቡን ተቋሙን ማገዝ፣ ሙያተኞችን ማጎልበት ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡ ዘመኑን የዋጀ ተቋማዊ አሠራር እንዲኖር እየተሠራ መኾኑንም አመላክተዋል፡፡
የማኅበረሰብ አቀፍ የፖሊስ አገልግሎት ሥራዎችን እንደገና መጀመር፣ ማጠናከር፣ ኅብረተሰቡ ፖሊስን ከፖለቲካው ነጥሎ ማየት አለበት ነው ያሉት፡፡ ኅብረተሰቡ ሕግ እና ሥርዓት ሲጠፋ የሚፈጠረውን ማወቅ አለበት የሚሉት ምክትል ኮማንደር መሳፍንት በአንድ ግለሰብ ጥፋት ተቋሙን መወንጀል አይገባም፣ ተቋሙ ለሕዝብ ያስፈልጋል፣ ተቋምን መፍጠር እና መጠበቅ ደግሞ ከኅብረተሰቡ ይጠበቃል ብለዋል፡፡
ሕግ አስከባሪ ያስፈልገኛል፤ ፖሊስ ከየትኛውም ወገን ነጻ ነው፣ አብሬ መሥራት አለብኝ የሚል የአመለካከት ለውጥ ያስፈልጋል፤ የአመለካከት ለውጥ ከመጣ ችግሩ እየተፈታ ይሄዳል ነው ያሉት፡፡
አሚኮ