አብይ አህመድ አስረግጠው “እዚህ እሺ፣ እዛ ስትሄዱ ጽንፈኛ ትሆናላችሁ። ጽንፈኝነት ዞሮ ዞሮ ራስን ያጠፋል። ይህ በተደጋጋሚ የታየ እውነት ነው። መጥፋት ከፍለጋችሁ ቀጥሉበት” ሲሉ ስም እየጠሩ ነው ያስጠነቀቁት። ለወትሮው አድርገውት በማያውቁት መልኩ ከፍተኛ አመራሮችን ስም እየጠሩ በዚህ ደረጃ የመናገራቸው ሚስጢር ምን ይሆን?
ሁለት አበይት ጉዳዮች አሉ። አንደኛው በተጀመሩ ልማቶችና ፍጻሜ ባገኙ ፕሮእጀክቶች ካድሬው ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ የአተያይ ለውጥ አድሮበታል። ዋናው ምክንያት ግን መንግስት ኃይሉ መጠንከሩና አስፈላጊ ሲሆን እርምጃ የመውሰድ አቅም እንዳለው፣ በየአቅጣጫው ባሉ ትርምሶች ውስጥ ገባ ወጣ የሚሉት ይህንኑ የመንግስት ጥንካሬ አይተው ተስፋ መቁረጣቸው እንደሆነ መረጃውን የግል እየታቸው መሆኑን ገልጸው ነግረውናል።
ባለፈው ረቡዕ የተጠናቀቀው የብልጽግና ጉባኤ ብዙ አልተነገረለትም። እንደ ወትሮው ጉባኤዎች ሁሉ በቪዲዮ ይፋ ሆኖ ውይይቱ ይህ እስከተጻፈ ድረስ ከዜና በስተቀር በመገናኛዎች አልተሰራጨም። ምን አልባትም ሰፊ የአርትኦት ስራ ጠይቆ ይሆናል።
አብይ አሕመድ “ባለፈው ታሪክ ሕዝብን አታወዛግቡ” ሲሉ የቀድሞውን ትርክት በማንጠልጠል ትርምስ የሚፈጥሩና ሁለት ቦታ የሚረግጡትን ከምክርም፣ ከማስተንቀቂያም በዘለለ ተናግረዋቸዋል። ” ዛሬ የናንተ ነው። ነገም የናንተ ነው ስሩበት” ሲሉ አሳበው ያለፈው ታሪክ ራሱ ጊዜውን ጠብቆ እንደሚስተካከል አመልክተዋል።
በቋንቋ መጣላት አስገራሚ መሆኑንን ባነሱበት ወቅት ” ብንግባባ” ሲሉ ቁጭታቸውን አስከትለው የተናገሩት ኮርኳሪ ነበር። አማርኛ ከአገራችን አልፎ የአፍሪቃ ቋንቋ እንደሚሆን ሲጠቁሙ፣ ይህ ሊሆን ያልቻለው ስምምነት በመጥፋቱ እንደሆነ አመላክተዋል።
አገርና ምድሩ፣ አክቲቪስት የሚባሉትና የዩቲዩብ አዝማቾች፣ እንዲሁም በውጭ አገር መንግስታት የሚተዳደሩ ተቋማት ቅርንጫፍ ሆነው በአማርኛ፣ በሶማሊኛ፣ በትግርኛና በኦሮምኛ መረጃ የሚረጩ ሚዲያዎች የግብጽና ሚሳይል፣ታንክና የምድር ኃይል፣ እንዲሁም ጀትና የአየር ኃይሏን እየዘረዘሩ ግብጽ ኢትዮጵያን እንደምታጠፋ በስፋትና በቅብብል ስለሚጽፉት ጉዳይ አብይ አህመድ “አትፍሩ” ነው ያሉት።
ብዙም ቁብ ሳይሰጡት “ግብጽ፣ ኤርትራ ምናምን የሚባለውን ወሬ እርሱትና ስራችሁን ስሩ። የሚያሳስብ ጉዳይ አይድለም። በሶማሌ መጡ…” ሁሉንም እንዲተዉት አሳበው ” ማንም የሚነካን የለም” ሲሉ ለተሰብሳቢዎቹ ማስተማመኛ ሰጥተዋል።
መረጃውን የሰጡን እንዳሉ አብይ አሕመድ ይህን ሲናገሩ ተሰብሳቢዎቹ በመገረም ያዳምጡ ነበር። ከምንም በላይ በእረፍት ሰዓት እርስ በርስ የነበረው ውይይት ፓርቲውን በሚመሩት ፕረዚዳንቱ ላይ ያላቸውን መገረመ መግለጽ በስፋት ይታይ ነበር።
ስብሰባው ከሚካሄድበት አዳራሽ ጎን ባለ አንድ ትምህርት ቤት ጠዋት ጠዋት የኢትዮጵያ ህዝብና የኦሮሚያ ክልል መዝሙር ሲዘመር እንደሚሰሙ፣ በዚህም መገረማቸውን ያጫወቱን እነዚህ ወገኖች፣ በዘንድሮው የብልጽግና ጉባዔ የታየው አዲስ ነገር ከየአቅጣጫው የሚወረወረው አፍራሽ ወሬ መክሸፉንና፣ ተራ አሉባልታ መሆኑን ካድሬው አምኖ የተገኘበት ስብሰባ መሆኑ ነው። ይህም አመራሩም ሆነ ካድሬው በሙሉ ነጻነትና ኩራት እንዲራመድ አድርጎታል። በፍርሃቻ ሁለት ቤት ሲረግጡ የነበሩትም ሚናቸውን የለዩበት መሆኑ ነው።
አሁን ላይ ያለው ብልጽግና የተፈተነበት ወቅት አልፎ ጉልበቱን ያጠነከረ በመሆኑ እንደቀድም ካድሬን እያባበለ የሚሄድበት ጊዜ ማለፉን አባላቱ መረዳታቸውን እንደተገነዘቡ መረጃውን የሰጡን አስታውቀዋል። ለዚህም እንደ ማሳያ ያነሱት ባለፈው ዓመት በተደረገው ጉባኤ ላይ ሰፊ ልዩነት እንደነበረ በመጥቀስ አስረድተዋል።
በስብሰባው ላይ ከተገኙ ተጋባዦች መካከል የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ ዲያስፖራውን ክፉኛ ዘልፈዋል። “ና አገርህ ግባ ሲባል የአንድ ነጠላ ጉዞ ቲኬት ቆርጦ መምጣት የማይችል ሁሉ እዚያ ቁጭ ብሎ አገር ያተራምሳል” በማለት አስተያየት ሲሰጥ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ታዬ አጽቀሥላሴ ሁሉንም በአንድ መፈረጅ አግባብ አለመሆኑን አመልክተው ቀና የሚባሉ ዜጎችም እንዳሉ ለማስረዳት ሞክረዋል። በዲፖሎማሲ ቋንቋ ታዬ አጽቀሥላሴ ለዚህም ሲባል ነው የዲያስፖራ ኤጀንሲ የተቋቋመው ሲሉ አክለዋል።
በስብሰባው በርካታ ብልጽግና ውስጥ የሌሉ ተጋብዘዋል። ስብሰባውን የተካፈሉ እንዳሉት በዓመቱ በውይይት፣ በተቀነባበረ ዘመቻና አመራሩ ሚናውን ለይቶ በጋር በመስራት ሰላም ለማውረድ ጥልቅ አቋም መያዙን አመልክተዋል።
ከሉዓላዊ ሚዲያ ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉት ጊልድ ማርሻል ብረሃኑ ጁላ በ2017 በሁሉም አካባቢዎች የሚነቀሳቀሱ ታጣቂዎች አደብ እንዲይዙ እንደሚደረገና ህዝብ ወደ ላማት እንዲመለስ እንደሚደረግ ከተናገሩት ጋር መረጃው የተዛመደ ሆኗል።
ብልጽግና በማህበራዊ ገጹ ጉባዔው ሲጠናቀቅ የሚከተለውን አትሟል
ሀገራዊ የመሻገር ትልሞችን በታላቅ ርብርብና ቅንጅት በማሳካት የበለፀገች ኢትዮጵያን ለመፍጠር አመራሩ ከምንጊዜውም በላይ የአገልጋይ አመራር ሰብዕናን ተላብሶ በውጤታማነት መስራት አለበት-የብልፅግና ፓርቲ ፕረዝደንት እና የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
ብልፅግና ፓርቲ ላለፉት 12 ቀናት በአዳማ ያካሄደው የከፍተኛ አመራሮች የአቅም ግንባታ የስልጠና መድረክ የፓርቲው ፕሬዚዳንት ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሰጡት አቅጣጫ ተጠናቋል።
ፓርቲው “የህልም ጉልበት ለእመርታዊ እድገት” በሚል መሪ ሀሳብ ከክልሎች፣ ከተማ አስተዳደሮችና ከፌዴራል ተቋማት ለተውጣጡ ከ2000 በላይ ከፍተኛ የአመራር አባላቱ፣ የነገዋን ኢትዮጵያ ብልፅግና በማረጋገጥ የትውልዱን መፃኢ እድል ምቹና ስኬታማ ማድረግ በሚያስችሉ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ባላቸው ሀሳቦች ዙሪያ ስልጠና ሰጥቷል።
የአመራር አባላቱ ጊዜን በአግባቡ በመጠቀም የህዝብ ችግሮችን በየደረጃው በመፍታት በተግባር አንድነት የኢትዮጵያን ከፍታ ለማረጋገጥ በስልጠናው በቂ አቅም ያገኙበትና የነገዋን ኢትዮጵያ መስራት የሚያስችል ግንዛቤ የጨበጡበት እንደነበረ የፓርቲው ፕሬዚዳንትና የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገልፀዋል።
ስልጠናው ሀገር ቀያሪም፣ ሀብት ፈጣሪም ሰው በመሆኑ፣ በሁሉም የሀገሪቱ ክልሎች፣ ከተሞችና የፌዴራል ተቋማት ያለው ከፍተኛ አመራር በተመሳሳይ የፓርቲው ተልዕኮዎች ዙሪያ በቂ ግንዛቤ በመያዝ ለተሻለ ውጤት እንደሚያተጋው አብራርተዋል።
መሪነት ራስን መስጠትን፣ ሆደሰፊነትንና ዓላማን የማሳካት ቁርጠኝነትን እንደሚጠይቅ ጠቁመው፣ ከፍተኛ አመራሩ የወሰደው ስልጠናም የመሪነት ቁልፍ መርሆዎችና ባህሪያትን በአግባቡ እንዲገነዘብ ያደረገ በመሆኑ ፈጣንና እመርታዊ ለውጥ ለማስመዝገብ አቅም ይፈጠራል ሲሉ መግለጻቸውን ከብልጽግና ፓርቲ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
በስልጠናው ህልምንና ትልምን ለማሳካት የሚያግዙ እይታዎችና የመፈፀሚያ ትርክቶች ላይ ያተኮሩ ሀሳቦች፣ በህዝብ ቅቡልነትና ትብብር የመስራት አቅም፣ እውቀት መር ሽግግርን ለማፅናት የሚያስፈልጉ ሰብዕናዎች ላይ የመስራትና የፀጥታ ችግሮችን ወደ ተሟላ ሰላም የሚያሻግሩ ሂደቶችና የአመራር ስነምግባርን በሚመለከቱና ተያያዥ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ፅሁፎች ቀርበው ሰፊ ውይይት ተካሂዷል።