የሶማሊ ማህበረሰብ ኃይማኖቱን አክባሪ፣ ለሀገር ሽማግሌ፤ ለጋራድ፣ ሱልጣን እና ኡጋዝ እሺ ብሎ መታዘዝን የሚያውቅ፣ከባህላዊ ጎሳ መሪ የሚሰጥ ትዕዛዝን በመቀበል በጋራ እና በአንድነት መኖር ትልቅ ዕሴቱ ነው፡፡
በመሬት ወሰን የተጋጨም ሆነ በድንገተኛ ጸብ የተጣላ ፣ በጎሳ የመሬት አከላለም ሆነ በግጦሽ መሬት ነፍስ የተጣፋ፣ በድንገተኛ ጸብም ይሁን ሆን ብሎ አደጋ ያደረሰ፣ እንዲሁም ለኒካህ (ጋብቻ) የሚሰጥ ጥሎሽን በተመለከተ በጎሳ መሪ፣ በሀገር ሽማግሌ የተወሰነን የሚያከብር ለቃላቸውም የሚገዛ ማህበረሰብ እንደሆነም ይታወቃል፡፡
በትላንትናው ዕለትም የሀገር ሽማግሌዎች፣ ገራዶች፣ ሱልጣኖች በጋራ ስብሰባ በማካሄድ በሶስት ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል፡፡ የውይይታቸው ሶስት ዋና ነጥቦች፡-
1.የኒካህ (ጋብቻ) ጥሎሽ መቀነስን በተመለከተ፤ ልጆቻችን ለጥሎሽ የሚጠየቁት ዋጋ ከፍተኛ መሆን ወዳልተገባና አላህ ወደ ማይወደው የዝሙት ሊያመራ ስለሚችል ለኒካህ(ጋብቻ) የሚሰጥ ክፍያን መወሰን፤
2.የሰው ህይወት በድንገተኛ ሁኔታ ( በመኪና አደጋና በመሳሰሉት) ያጠፋ ሰው ለቀብር ተብሎ የሚጠየቀው ክፍያን በተመለከተ ገደብ ማስቀመጥ፤
3.በጎሳዎች መካካል በሚፈጠሩ ግጭቶች የሚከሰቱ ጉዳቶች የካሳ አከፋፋል ምን መሆን አለበት በሚሉ ነጥቦች ላይ በመምከር ውሳኔዎችን አሳልፈዋል፡፡
ነገር ግን ይህን እውነታ ሽምጥጥ አድርጎ በመካድ ጦርነት፣ እልቂት፣ ድርቅና ችግር መርዶ እንጂ የሰላም ዜና የሚያሳምማቸው አንዳንድ ትላንትን ናፋቂ የሆኑ የማህበራዊ ሚዲያዎች “በሶማሊ ክልል አንድ ዞን በሼሪአ እንዲተዳደር ተደረገ” በሚል በማህበራዊ ሚዲያ ሀሰተኛ መረጃ ሲያሰራጩ ለመመልከት ተችሏል፡፡
ከለውጡ በኋላ ባሉ ዓመታት እስካሁን ድረስ በክልሉ ላይ ሆን ተብሎ የህዝቡን አንድነትና እድገቱን ለማሰናከል ያልተፈነቀለ ድንጋይ፣ ያልተሞከረ ሴራ፣ ያልታቀደ ተንኮል ባይኖርም ዛሬም በከፍታ እንደምትታይና ለአካባቢ ሁሉ ብርሃን እንደምትሰጥ ኮከብ ይበልጥ ማንጸባረቅና ማብራቱን የቀጠለው የሶማሌ ህዝብ ይህንንም እንደሌሎቹ ታዝቧል፡፡
በዛሬው ዕለትም “ሼሪዓ መንግስት ተመሰረተ” በሚል በማህበራዊ ሚዲያ እየተሰራጨ ያለው መረጃ ሀሰተኛና በሬ ወለደ ብቻ ሳይሆን ኢስላም ጠል አላማ ያነገበ ለዘመናት በሶማሊ ማህበረሰብ ላይ ሲሰራጭ የነበረው ትርክት አንድ ማሳያ ብቻ ሳይሆን ከሀሰተኛ መረጃው ጀርባ ያለውን ግብም ያመላከተ ነው፡፡
ትላንት የሶማሊ ህዝብ ሲገድልና ሲጨፈጭፍ ከነበረ ሃይል ጎን ተሰልፈው የነበሩ እነኚህ አካላት በህዝቡ ሞትና እልቂት ከማዘን ይልቅ ለፍርፋሪ ብለው ህዝቡን ‘አሸባሪና ተገንጣይ’ ሲሉ ስም እንደሰጡት ሁሉ ዛሬ ባይሳካላቸውም በተደጋጋሚ ከሚነዙት ሽብር በተጨማሪ ‘ሸሪዓ ተመሰረተ’ የሚል ካባ ለብሰው መምጣታቸው ዓላማቸውን ይበልጥ ግልፅ ያደረገ ነው፡፡
የሶማሊ ክልል ህዝብን ከሌላው ክልል ህዝብ ጋር የመነጠል ግብን በመያዝ በተከታታይ የሀሰት መረጃዎችን ከሚያሰራጩ ጭር ሲል አልወድም የሆኑ የማህበራዊ ሚዲያዎች መካከል ይህ ዓይነቱን አጀንዳ ተቀብለው የሶማሌ ክልል ማህበረሰብ ትልቅ እሴት የሆነውን የሀገር ሽማግሌና የጎሳ መሪዎችን በመንካትና ያልተባለ በማራገብ መርዛቸውን ሲረጩ ተስተውሏል፡፡
በዚህ አጋጣሚ የሀገር ሽማግሌዎቹና የጎሳ መሪዎቹ የውይይት ዓለማ ህዝብን በሚጠቅሙ ከላይ በተነሱ ባህላዊ የእርቅ መፍቻ መንገዶች ላይ ያተኮሩ ሲሆን ይህን በካደ መልኩ ያልተባለ ተባለ በሚል በሀሰት የሚነዛው ፍጹም ሀሰት ብቻም ሳይሆን ይህ አይነቱ ሴራ ያገኘውንና ያተረፈውን ጠንቅቆ የሚያውቀው የሶማሊ ህዝብን፣የሚከበሩ የጎሳ መሪዎቹንም ሆነ የሀገር ሽማግሌዎቹን የማይወከል መሆኑን እንገልፃለን፡፡
የሶማሊ ክልል መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ