የጋዜጠኛነት እና ሥነ ተግባቦት መምህር እና ተመራማሪ እንዳሉት በቅርቡ በተማሪዎች የማኀበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ዙሪያ ጥናት ሠርተዋል።
የማኀበራዊ ሚዲያን ያለገደብ በሚያዘወትሩ 101 የ10ኛ ክፍል ተማሪዎች ላይ በሠሩት ጥናት ተማሪዎቹ የማኀበራዊ ሚዲያን አዘውትረው ከመጠቀማቸው በፊት የነበራቸው የእንግሊዝኛ፣ ሒሳብ እና ኬሚስትሪ ከ60 እስከ 65 በመቶ የነበረው አማካይ ዝቅተኛ ውጤት ከነበረበት ወደ 45 በመቶ አሽቆልቁሏል ይላል።
በተመሳሳይ የእነዚህ ተማሪዎች ከፍተኛ ውጤት በአማካይ ከ80 እስከ 90 በመቶ የነበረ ሲኾን ትኩረታቸውን ማኀበራዊ ሚዲያ ላይ በማድረጋቸው ወደ 70 እና 75 በመቶ ዝቅ ማለቱ ተመላክቷል።
በአንጻሩ የማኀበራዊ ሚዲያን በተገደበ ሁኔታ ለትምህርታቸው በአጋዥነት ከሚጠቀሙት 101 የ10ኛ ክፍል ተማሪዎች ውጤታቸው በየጊዜው ተሻሽሏል። በመኾኑም መቶ በመቶ ያስመዘጉ ተማሪዎች መኖራቸውን ጥናቱ አመላክቶ ዝቅተኛው ደግሞ በአማካይ ከ80 እስከ 85 በመቶ ኾኖ ተመዝግቧል ብሏል ጥናቱ።
አጥኝው እንዳሉት ታዲያ ወላጆች፣ አሳዳጊዎች እና መምህራን ተማሪዎቻቸው የማኀበራዊ ሚዲያን ለትምህርት ተግባር ብቻ እንዲያውሉት በመወያዬት መገደብ ካልቻሉ በውጤታቸው ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳርፋል፤ ሕይዎታቸውንም በማበላሸት ወደ አልተፈለገ አቅጣጫ እንደሚወስዳቸው የጥናቱ ውጤት አመላክቷል።
ችግሩን ማስተካከል የሚቻለው በየትኛውም ደረጃ ባሉ የትምህርት ተቋማት የሚማሩ ተማሪዎችን ባሕርይ በመግራት ነው ብለዋል።
የሥነ ልቦና መምህር እና አማካሪ ማሞ አበበ ወላጆች ልጆቻቸው የማኀበራዊ ሚዲያ አጠቃቀማቸውን መከታተል እንዳለባቸውም ነው የተናገሩት።
አቶ አበባው የተባሉ የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ እና የተማሪ ወላጅ “ልጆቼ የእጅ ስልካቸውን ኾነ ቤት ውስጥ ያለውን ኮምፒዩተር ለትምህርታቸው አጋዥ ብቻ እንዲጠቀሙበት ተግባብተናል፤ የሚዝናኑትም በፕሮግራም ነው፤ በመኾኑም የ12ኛ ክፍል ተፈታኝ የነበረው ልጄ ከ500 በላይ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤትም አስመዝግቧል ” ብለዋል።
ሜሎና የተባለች ተማሪ እንዳለችው እሷ ከትምህርቷ ይልቅ የማኀበራዊ ሚዲያን በማዘውተሯ ውጤቷ እንዳሽቆለቆለ ተናግራለች። “በዚህ ሁኔታ መቀጠሉ ስለማያዋጣኝ በ2017 የትምህርት ዘመን ማኀበራዊ ሚዲያን ከትምህርት ውጭ ላለመጠቀም ለራሴ ቃል ገብቻለሁ” ብላለች።
አቤል የተባለው ተማሪም በሜሎና ሐሳብ ይስማማል። “እኔ እና ጓደኞቼ ስንገናኝ የምንወያዬው ማኀበራዊ ሚዲያ ላይ ስለተጋራው ቲክ ታክ፣ የእግር ኳስ ጨዋታ ወይም ቪዲዮ ነው፤ በመኾኑም ትምህርታችንን አዘናግቶናል፤ ወደ ቀልባችን መመለስ አለብን” ነው ያለው።
(አሚኮ)