ወንጀለኛ የነበሩ 178 የሠራዊት አባላት በአዲስ አመት ይቅርታ ተደረገላቸው።
የህወሓት ታጣቂ ሃይሎች ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም የሃገሩን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ ስምሪት ላይ በነበረው የሰሜን ዕዝ ላይ በክህደት መንፈስ ጥቃት መከፈታቸውን ተከትሎ አንዳንድ የሰራዊት አባላት የተሰጣቸውን ህገ- መንግስታዊ ተልዕኮ ወደ ጎን በመተው በሰራዊቱ እና በህዝብ ጥቅሞች ላይ ወንጀል መፈፀሙ ይታወቃል።
ወንጀል መፈፀማቸውን ተከትሎ ጉዳያቸው በወታደራዊ ፍትህ ስርዓቱ አማካኝነት ክስ ተመስርቶባቸው በተከሰሱበት ወንጀል ጥፋተኛ ሆነው በመገኘታቸው ምክንያት በወታደራዊ ፍርድ ቤቶች እስከ ሞት ቅጣት ተወስኖባቸው በማረሚያ ቤት የሚገኙ 178 (መቶ ሰባ ስምንት) የሠራዊት አባላት በፈፀሙት ወንጀል ተፀፅተው የይቅርታ ጥያቄአቸውን ለመንግስት እና ለመከላከያ ሚኒስቴር አሥገብተዋል።
የይቅርታ ጥያቄ ማስገባታቸውን ተከትሎ በአንድ በኩል ጉዳያቸው ለይቅርታ ቦርድ ቀርቦ በአዋጅ ቁጥር 840/2006 አንቀፅ 3 ድንጋጌ መሰረት ይቅርታ ማድረግ የሚያሳካቸውን አላማዎች ግምት ከማስገባት ሌላ እነዚህ የሰራዊት አባላት በፈፀሙት ወንጀል መፀፀታቸውንም ተመልክቷል።
መንግስት በሰሜኑ የሃገራችን ክፍል የነበረውን ጦርነት ለማቆም በፕሪቶሪያ የተፈረመውን የሰላም ስምምነት ይበልጥ ለማፅናት ቁርጠኛ በመሆኑ የመከላከያ ሚኒስቴር የይቅርታ ቦርዱን ውሳኔ መሰረት በማድረግ በአዲሱ አመት በመታረም ላይ የነበሩ 178 የትግራይ ተወላጅ የሠራዊት አባላት ከዛሬ ጷጉሜን 05 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ከእስር በይቅርታ እንዲለቀቁ የተወሰነ መሆኑን አንገልፃለን፡፡
የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር