በሶማሊያ በውጭ ሃይላት የሚደረግ የጦር መሣሪያ አቅርቦት ሀገሪቷ በአሸባሪዎች እጅ ላይ እንድትወድቅ በር ይከፍታል – አምባሳደር ታዬ
በሶማሊያ ባልተረጋጋ የደህንነት ሁኔታ ውስጥ በውጭ ሃይላት የሚደረግ የጦር መሣሪያ አቅርቦት በመጨረሻ ሀገሪቷ አሸባሪዎች እጅ ላይ እንድትወድቅ በር ሊከፍት ይችላል ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሤ ተናገሩ፡፡
በኒውዮርክ እየተካሄደ በሚገኙው 79ኛው የተመድ ጠቅላላ ጉባዔ ጎን ለጎን አምባሳደር ታዬ ከተመድ የሰላም ግንባታ እና ፖለቲካ ጉዳዮች ረዳት ዋና ፀሐፊ ሮዝማሪ ዲካርሎ ጋር የጋራ ትኩረት በሚሹ ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል፡፡
አምባሳደር ታዬ በ.ተ.መ.ድ. ጥላ ሥራ የሚገኙ የተለያዩ ኤጀንሲዎች ከኢትዮጵያ ጋር ጠንካራ የሥራ ግንኙነት ፈጥረው እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን በማድነቅ ቀጣይነት ያላቸው መደበኛ ምክክሮችን አስፈላጊነት አንስተዋል።
ሚኒስትሩ ለረዳት ዋና ፀሐፊዋ በሱዳን ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ገለጻ በማድረግ እና በአገሪቱ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት የተቀናጀ ጥረት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል። ኢትዮጵያ ለሱዳን ቀውስ መፍትሔው ፖለቲካዊ ነው የሚል አቋም እንዳላት አንስተዋል።
አምባሳደር ታዬ ሶማሊያን በተመለከተ ከሮዝማሪ ጋር በነበራቸው ውይይት ኢትዮጵያ በሽብርተኞች ለመዋጋት ላይ የምታደርገውን ጥረት አጠናክራ እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል።
በሶማሊያ ድህረ የአፍሪካ ህብረት ሽግግር ተልዕኮ በሶማሊያ (አትሚስ) የሚኖረው የኃይል ስምሪት ተገቢውን ጊዜ ወስዶ የተልዕኮዎን የኃላፊነትን ፣ መጠን፣ የፋይናንስ ምንጭ እና ቅንጅት በአግባቡ መሠራት እንዳለበት ገልጸዋል።
ሚኒስትሩ ባልተረጋጋ የደህንነት ሁኔታ ውስጥ በውጭ ኃይላት የሚደረግ የጦር መሣሪያ አቅርቦት መጨረሻው አሸባሪዎች እጅ ላይ ሊወደቅ እንደሚችል ያላቸውን ስጋት ገልፀዋል።
የተመድ የሰላም ግንባታ እና የፖለቲካ ጉዳዮች ረዳት ዋና ፀሐፊ ሮዝማሪ ዲካርሎ በበኩላቸው በቀጣናው እና ከቀጣናው ባሻገርም ተ.መ.ድ. ከኢትዮጵያ ጋር በሰላም ግንባታ ዙሪያ የሚያደርገውን ሥራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
ሁለቱ አካላት በቀጣይም ኢትዮጵያ እና ተመድ በጋራ የሚያከናውኗቸውን ስራዎች የበለጠ አጠናክረው በሚቀጥሉበት አግባብ ላይ መክረዋል።
ፋና