የሳይበር ፋይናንስ ማጭበርበር ከሚፈጸምባቸው መንገዶች መካከል የሞባይል ባንኪንግ እና የኢንተርኔት ባንኪንግ ማጭበርበር አንዱ ነዉ፡፡
ይህ የሳይበር ፋይናንስ ማጭበርበር ድርጊት የሚፈጸመው አጭበርባሪዎች ኢንተርኔትን በመጠቀም ያልተፈቀላቸውን የኢንተርኔት እና የሞባይል ባንኪንግ ሲስተም አካውንቶችን እንደ ማልዌር፣ ማስገር ወይም ሌላ የማጥቂያ ዘዴዎችን በመጠቀም ጥሰው በመግባት ህጋዊ ያልሆነ የገንዘብ ዝውውር በማድረግ ከፍተኛ የገንዘብ ኪሳራ ሊያስከትል የሚችል ጥሰት የሚፈጽሙበት የማጭበርበር አይነት ነው።
ይህ ዓይነቱ ማጭበርበር በተለምዶ የኦንላይን ባንኪንግ ሥርዓቶች ላይ ባለ ደካማ የደህንነት እና የተጋላጭነት ክፍተቶችን እንዲሁም የተጠቃሚዎችን ባህሪ እና ደካማ ጎን ለመለየት የተዘጋጁ የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም ይከናወናል።
የተለመዱ የሞባይል ባንኪንግ እና የኢንተርኔት ባንኪንግ ማጭበርበር አይነቶች
• ማስገር (Phishing)፡- አጭበርባሪዎች ሕጋዊ የባንክ ሰራተኛ በመምሰል ሀሰተኛ ኢ-ሜይሎችን፣ የድምጽ እና የጽሁፍ መልዕክቶችን በመላክ ግለሰቦችን አታለው የይለፍ ቃላቸውን እና መረጃዎቻቸውን እንዲገልጹ በማድረግ የሚፈጸም የማጭበርበር አይነት ነው፤
• እኩይ ሶፍትዌር (Malware)፡ አጭበርባሪዎች የተጠቂውን ኮምፒውተር ወይም ስማርት ስልክ ለማጥቃት የተለያዩ ማልዌሮችን እና ቫይረሶችን ይጠቀማሉ። ማልዌሩ አንድ ጊዜ ከተጫነ በኋላ የተጠቃሚውን የመግቢያ መረጃዎች (login credentials) በመስረቅ ወይም ተጠቃሚዎችን ወደ ማጭበርበሪያ የባንክ ድረ-ገጽ በማዞር ጥቃት ይፈጽማሉ።
• ጣልቃ ገብነት ጥቃት (Man-in-the-Middle Attacks) ፡ ጠላፊዎች በተጠቃሚው እና በባንኩ ድረ-ገጽ ወይም መተግበሪያ መካከል ያለውን ግንኙነት ያቋርጣሉ፣ በዚህም ጥብቅ የሆነ የባንክ መረጃን ለመቆጣጠር፣ ለመቀየር ወይም ለመስረቅ ያስችላቸዋል።
• ማህበራዊ ምህንድስና (Social Engineering) ፡ አጭበርባሪዎች የባንክ ህጋዊ ወኪሎችን በመምሰል የተጠቃሚዎችን ሚስጥራዊ መረጃ (ለምሳሌ የይለፍ ቃል፣ የደህንነት ማለፊያዎችን) እንዲሰጡ ያደርጋሉ።
• ሐሰተኛ የሞባይል ባንኪንግ መተግበሪያ (Fake Banking Apps) ፡ አጭበርባሪዎች ሀሰተኛ የሞባይል ባንኪንግ መተግበሪያዎችን በመስራት እና ወደ ተጠቃሚ በማሰራጨት ተጠቃሚዎች የይለፍ ቃላቸውን እና ጥብቅ መረጃዎችን አሳለፈው እንዲሰጡ ያደርጋሉ።
– የሳይበር ጥቃት ጥቆማ ለመስጠት ነጻ የስልክ መስመር፡933
• ኢ-ሜይል፡ contact@insa.gov.et