በኢትዮጵያ ለሚሰሩ የተለያዩ ፕሮጀክቶች ማስፈፀሚ የሚውል የ400 ሚሊየን ዩዋን የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ ቃል መግባቷን የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ ገለፁ፡፡
ሚኒስትሩ የኢትዮ-ቻይና የኢኮኖሚ ትብብር ጉባኤን በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ፤ ኢትዮጵያ እና ቻይና በሁኔታዎች የማይለወጥ ስትራቴጂክ ግንኙነት እንዳላቸው ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ፕሬዚዳንት ሺ ዥንፒንግ በነበራቸው ውይይት የሀገራቱን ሁሉን አቀፍ ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ ዓለም ዓቀፋዊ ጫናዎችን በመቋቋም እና የፖሊሲ ነፃነቷን በመጠቀም የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ማድረጓ በፕሬዚዳንት ሺ ዥንፒንግ ከፍተኛ አድናቆት እንደተሰጠው ተናግረዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ ኢትዮጵያ ያስመዘገበችውን የኢኮኖሚ እድገት ማድነቃቸውን እና በቻይና ያሉ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ግፊት እንደሚደረጉ መግለፃቸውን አቶ አህመድ ሺዴ አብራርተዋል፡፡
የኢትዮጵያ የእዳ ሽግሽግ በተመለከተ በውይይቱ መነሳቱን ጠቅሰው÷ በቡድን 20 አባል ሀገራት የጋራ ማዕቀፍ መሰረት ኢትዮጵያ የተሟላ የብድር ሽግሽግ እንዲደረግላት ስምምነት ላይ መደረሱን አስገንዝበዋል፡፡
በተጨማሪም በኢትዮጵያ ለሚሰሩ የተለያዩ ፕሮጀክቶች ማስፈፀሚያ የሚውል የ400 ሚሊየን ዩዋን የገንዘብ ስምምነት ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልፀዋል፡፡
በአጠቃላይ ውይይቱ እጅግ ስኬታማ እና የሁለቱን ሀገራት ትብብር ለማጠናክር የሚያስችል እንዲሁም በቴክኖሎጂ፣ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ እና በማኑፋክቼሪንግ በጋራ ለመስራት የሚያስችሉ ስምምነቶች መደረጋቸውን አስረድተዋል፡፡
በተጨማሪም በሁለቱ ሀገራት የመገበያያ ገንዘብ ብር እና ዩዋን መገበያየት የሚያስችል የቀጥታ ግብይት ስለሚፈጠርበት ሁኔታ መምከራቸውን አቶ አህመድ ሽዴ አብራርተዋል።
ኢትዮጵያና ቻይና በ17 ዘርፎች በትብብር ለመስራት የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረሙ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከቻይና ጠቅላይ ሚኒስትር ሊ ኪያንግ ጋር ተወያይተዋል፡፡ በውይይታቸውም በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ትብብር ማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ዛሬ ከቻይና ጠቅላይ ሚኒስትር ሊ ኪያንግ ጋር በሀገራቱ መካከል ያለውን ትብብር የበለጠ ለማጠናከር በሚያስችሉ መንገዶች ላይ ውጤታማ ውይይት አድርገናል ብለዋል፡፡
ቀደም ብሎ ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ በቻይና-አፍሪካ የትብብር ጉባዔ ላይ ከእኛ የዕድገት እና የልማት ግቦች ጋር የሚናበቡ 10 ነጥቦች ያሉት የድርጊት መርሐ ግብር ይፋ ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል፡፡
በተለይም ያደገ ምርታማነትን ለማሳካት ሥራዎቻችንን በምናዘምንበት የግብርና ትብብር መንገድ ላይ ፍላጎታችንን ገልጫለሁ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
በኢንዱስትሪ ልማት እና በዲጂታላይዜሽን ሥራዎች ላይ ድጋፍ በሚገኝበት ሁኔታ ላይ መምከራቸውን አንስተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሮቹ በጋራ በተገኙበት ኢትዮጵያና ቻይና በ17 ዘርፎች በትብብር ለመስራት የመግባቢያ ሰነድ መፈራረማቸውንም ተናግረዋል፡፡
ስምምነቶቹ በኢትዮጵያ እና በቻይና ላለው በሁሉም ሁኔታ ለማይለዋወጠው ስትራቴጂያዊ ትብብር ዓይነተኛ ማሳያ ናቸው ሲሉም ገልጸዋል፡፡
credit to fana and ena