የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሙን መምጣት ተከትሎ በመንግስት ቃል ከተገቡት ጉዳዮች አንዱ የሆነው የደሞዝ ጭማሪ ከመስከረም 1/2017 ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚሆን መሠረት ሚድያ የተመለከተው እና ትክክለኛነቱ በኢትዮጵያ ቼክ የተረጋገጠ አንድ የፋይናንስ ሚኒስቴር ደብዳቤ ጠቁሟል።
ባለፉት ሰአታት ውስጥ በርካታ የማህበራዊ ሚድያ ተጠቃሚዎች ይህ የፋይናንስ ሚኒስቴር ደብዳቤ ነው የተባለ ምስል እንዲሁም አዲሱን የደሞዝ ስኬል ያሳያል ተብሎ የተገለፀ ስሌት በስፋት ሲያጋሩ ቆይተዋል።
ደብዳቤው በሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ የተፈረመ እንደሆነ የሚያሳይ ሲሆን ለጠ/ሚር ቢሮ ተልኮ ሲቪል ሰርቪስ ደግሞ ኮፒ እንደተደረገ ይገልፃል።
ኢትዮጵያ ቼክ የደብዳቤውን እና የደሞዝ ስኬሉን ትክክለኛነት ያረጋገጠ ሲሆን ለታሰበው የደሞዝ ጭማሪ ከ91.4 ቢልዮን ብር በላይ እንደተመደበ እና ጭማሬው ከመስከረም 1 ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚሆን ይገልፃል።
ይህ በፋይናንስ ሚኒስቴር እና በሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን በኩል ተጠንቶ የቀረበው የደሞዝ ጭማሪ በሚኒስትሮች ምክር ቤት እንዲፀድቅ መቅረቡም ተመላክቷል።
በአዲሱ ስሌት መሠረት ነባር ደሞዛቸው በጣም ዝቅተኛ የነበረው እና 1,100 ብር ያገኙ የነበሩ መጠኑ በ332 ፐርሰንት ጨምሮ 4,760 ብር እንደሚሆን ያሳያል።
በሌላ በኩል ደሞዛቸው ከፍተኛ የነበረው እና 20,468 ብር ያገኙ የነበሩ መጠኑ በ5 ፐርሰንት ጨምሮ 2,1491 ብር እንደሚሆን ይጠቁማል።
Addis_Reporter