ነገሮች ተገጣጥመው ወደ መጨረሻው እየመጡ ይመስላል። በተለይም እጅግ ባለሃብት እንደሆኑ የሚነገርላቸው የሞንጆሪኖ ወንድም አቶ ዳዊት ገብረ እግዚአብሄር አቶ አንዳርጋቸውን ይዘው አስመራ መግባታቸው ቀድሞ የተጀመረ ቢሆንም አሰላለፉን ይፋ እያደረገ ነው። ለዚህ ይመስላል አረና በፓርቲ ደረጃ ከሻዕቢያ ጋር የሚሰራ የትህነግ አንድ ቡድን እንዳለ ይፋ ያደረገው።
በአቶ መስስ እንዝላልነት ሻእቢያ ባድመን ወሮ በንበረበት ወቅት “ከትግራይ ውጭ ያላችሁት በባድመ አያገባችሁም። ባድመ የትግራይ እንጂ የኢትዮጵያ አይደለችም” በሚለው ንግግራቸው የሚታወቁት አቶ ዳዊት በቅርቡ እጅ በአፍ ያስጫነ ዜና በመንግስት ይፋ ከሆነ በሁዋላ “እኚህ ሰው ማን ናቸው” በሚል መነጋገሪያ ሆነው ነበር።
“በፈትለወርቅ ገ/እግዚአብሄር (ሞንጆሪኖ )ወንድም ስም ከተቀመጠ ገንዘብ ለማውጣት የሞከሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ” በሚል በ29 ጥቅምት 2021 የወጣው ዜና መነጋገሪያ የሆነው በስማቸው በባንክ ከተቀመጠው ሃብት 267 ሚሊየን ለማውጣት የህግ ባለሙያዎች የተሳተፉበት ወንጀል ይፋ መሆኑንን ተከትሎ “ስንት ቢኖራቸው ነው 267 ሚሊየን ብር ቆንጥረው ለማውጣት የሞከሩት?” የሚለው ጥያቄ የማህበራዊ ሚዲያ መነጋገሪያ ሆኖ ነበር።
በአቶ ዳዊት ገብረእግዚያብሔር ወንድም ስም በባንክ ከተቀመጠ ገንዘብ 267 ሚሊየን ብር ለማውጣት የሞከሩ 10 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ብቻ ሳይሆን፣ በወንጀሉ ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ከዋሉት ግለሰቦች ውስጥ 2 ዳኞች መሆናቸው የወቅቱ አስገራሚ ጉዳይ ነበር።የፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ የፋይናስና ንግድ ነክ ወንጀል ምርመራ ዳይሬክተር ረዳት ኮሚሽነር ብርሃኑ አበበ በወቅቱ በሰጡት መግለጫ፣ “ወንጀሉ የተፈፀመው በህግ ባለሙያዎች ሀሰተኛ ሰነድ በማዘጋጀት ነው” ማለታቸውም ይታወሳል።
በሀሰተኛ ስሙ ቱሉ በዳዳ(ቶፊቅ ሙላት አበራ) በስራ ግንኙነት እዳ አንዳለበት በመስማማት ሀሰተኛ ሰነድ በህግ ባለሙያዎች በማዘጋጀት ፍርድ ቤት ለግልግል ዳኝት እንዲጠይቁ ተደርጎ ብሩን ከባንክ ለማውጣት ተሞክሮ ቢከሽፍም፣ ትህነግ በወቅቱ በመላው አገሪቱ ሁከት ስፖንሰር ያደርግ ስለነበር ሲራውን የሚረዱ ትህነግ ያከማቸውን ሃብት እንዴት እንደሚጠቀም ማሳያ አድርገው ወስደውት ብዙ ብለዋል። ወቅቱ የጦርነትና የኢትዮጵያ ህልውና አደጋ ላይ የወደቀበት በመሆኑ ዜናው ክብደት ነበረው።
እኚህ ሰው ካለፈው ዓመት ጀምሮ በትግራይ የወርቅ ኮንትሮባንድና ከሻዕቢያ ጋር በፈጠሩት ግንኙነት ስማቸው በተደጋጋሚ ሲነሳ ነበር። እህታቸው ሞንጆሪኖ ዶክተር ደብረጽዮን የሚመሩት ቡድን አመራር መሆናቸውን አስቀድሞ ጥያቄ መፍጠሩ ማን ከሻዕቢያ ጋር ግንኙነት እንደጀመረ አመላካች ሆኗል። ይህ እንዳለ ሆኖ ባለፈው ሳምንት ወደ አስመራ የሞንጆሪኖ ወንድም አቶ ዳዊት ከአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ጋር አስመራ መግባታቸውን ተከትሎ አረና የሰጠው መግለጫ በርካቶች “ዝም ብሎ የተነገረና እንደ ቀድሞ ዓይነት መግለጫ አይደለም” ብለውታል።
አረና ትግራይ ስም ሳይጠራ “ከሁለቱ የትህነግ ቡድኖች መካከል አንዱ” ሲሉ ለይቶ ከሷል። ነገሩ ግልጽ ቢሆንም “እገሌ” ማለትን ያልመረጠው አረና ይፋ ያደረገውን ዜና የሰሙ “በሬ ያኮላሸውን” ሲሉ ተርተዋል። ትህነግ ዳግም ከሻዕቢያ ጋር መስራት መጀመሩ በትግራይ ከመነጋገሪያ በላይ ሰፊ የልዩነት አቋም ክፍተቱ ወደ አንድ ጫፍ መድረሱን ያሳየም ሆኗል።
ከሁለቱ የትህነግ ቡድኖች ውስጥ በአንደኛው ውስጥ ያሉት ቡድኖች ከሻዕቢያ ጋር ግንኙነት እንደጀመሩ መገንዘባቸውን የገለጹት የአረና ትግራይ አመራሮች ናቸው። “አንደኛው ከብልጽግና ሌላኛው ደግሞ ከሻእቢያ ጋር ሆነው እርስ በእርስ ይካሰሳሉ” ሲሉ ውስጥ ውስጡ ሲነገር የነበረውን ጉዳይ በፓርቲ ደረጃ ይፋ አድርገዋል።
አረና ቡድኖቹን ሆን ብሎ ስም አንስቶ ሳይጠራ ፣ አቶ ጌታቸው የሚመሩት ቡድን የመንግስት መዋቅር ውስጥ ያለና ትግራይን በህጋዊ መንገድ እንዲያስተዳድር ፈቃድ የተሰጠው ሲሆን ሌላኛው ቡድን ዶክተር ደብረጽዮን የሚመሩት መሆኑ ህዝብ ስለሚያውቅ የአረና ገለጻ ብዙም ግራ አላጋባም።
አረና ስማቸውን ለይቶ ባይገልጽም እነ አቶ ጌታቸው በግልጽ የመንግስት አካል በመሆናቸው፣ ከሻዕቢያ ጋር የሚሰራው በቅርቡ ዕውቅና የተነፈገው ጉባኤ ያካሄደው የእነ ዶክተር ደብረጽዮንና ፈትለወርቅ (ሞንጆሪኖ) ቡድን ነው። አስመራ የሚመላለሱትም የሞንጆሪኖ ወንድም ናቸው።
አረና ይህን ያለው ከትህነግ፣ ከሻዕብያና ከመንግስት ወገን በጦርነቱ ተሳትፈው ወንጀል የፈጸሙ ተጠያቂ ባለመደረጋቸው አሁንም የጦርነት ፍላጎት መኖሩን ሲያስታውቅ ነው። ፓርቲው ተጠያቂነትን ለመሸሽ ሲባል ክልሉን ለዳግም ውድመት የሚጋብዝ አካሄድ መኖሩን አመክቷል። ስጋቱንም ገልጿል። ሻዕቢያ ከግብጽ ጋር አብሮ ኢትዮጵያን ለማተራመስ የውክልና ስራ እየሰራ መሆኑ በመረጃ ተደግፎ እየተገለጸ ባለበት በአሁኑ ወቅት አረና ይህን ማለቱ ዜጎች ጉዳዩን ከመሃል ከተማ እስከ ገጠር በጥንቃቄ እንዲመረመሩት የሚያስገድድ ሆኗል።
ሻዕቢያ ካለው የቤት ለቤት የከተማ ውስጥ አደረጃጀት ልማድ በመነሳት በመላው ኢትዮጵያ ያሉ ዜጎች እንዲነቁ መረጃ ድጋፍ ሰጥቷል። የአረና ይፋዊ መግለጫ ተከታታይና ዝርዝር ክንወኖችን ይፋ እንዲያደርግ ሚዲያዎች ያለ አንዳች ሃፍረት አገራቸውንና ብሄራዊ ጥቅማቸውን በማስቀደም ደጋግመው ህዝቡን በመረጃ ሊያስታጥቁ እንደሚገባ ዜናውን የሰሙ አሳስበዋል።
የአረና ሊቀመንበ የሚካሰሱት ሁለቱ የትህነግ ቡድኖች ከላይ በተገለጸው መነሻ ምክንያት አንዱ ከኤርትራ ኃይሎች ጋር ግንኙነት እንዳለው ፓርቲያቸው እንደሚረዳ ይፋ አድርገዋል። አረና “እንረዳለን፣ እንገነዘባለን” ሲል አለሳልሶ ያቀረበው መረጃ ” ከሻዕቢያ ጋር ለመስራት የተስማማው የእን ዶከተር ደብረ ጽዮን ቡድን ወደዚህ ስምምነት የደረሰው ሻእቢያ የሚፈልገውን ለመፈጸም ተስማምቶ ነው። ሻዕቢያ የሚፈልገው ደግሞ ይታወቃል” ያሉ፣ በተለይ ጎጃም አካባቢ ከሚነቀሳቀሰው የፋኖ ሃይል ጋር ያለው ስምምነትም የዚሁ አካል መሆኑን አክለዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳል የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ከተለያዩ የክልሉ ከተሞች ነዋሪዎች ጋር ህዝባዊ ውይይት ማካሄድ መጀመሩን መረጃዎች አመልክተዋል። የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር አቶ ጌታቸው ረዳ የሚመሩት አካል በአዲግራት የተደረገለት አቀባበልና ወጣቶች ያሰሙት መፈክር መነጋገሪያ ሆኗል። ሰልፉና መፈክሩ የእነ አቶ ጌታቸው ረዳ ቡድን በወጣቶች ተቀባይነት እንዳለው ለሚነገረው ማሳያ እንደህነ ተመልክቷል።
አቶ ጌታቸው የተጀመረውን ውይይት አስመልክቶ አስተዳደሩ ያሉበትን ክፍተቶች ለማረምና አዎንታዊ ነገሮችን ለማስቀጠል እንደሚያግዝ ጠቅሰዋል ሲል ቪኦኤ ዘግብያል። አቶ ጌታቸው ማክሰኞ በዓዲግራት ከተማ በነበረው ውይይት ላይ ባደረጉት ገለጻ ጊዜያዊ አስተዳደሩን በሚመሩት ሰዎች ላይ “ከፍተኛ የሆነ ስም የማጥፋት ሥራ ተፈጽሟል” ሲሉ በይፋ አንደኛው ወገን ጠቅሰው ተናግረዋል።
በቅርቡ በተካሄደው 14ኛው የህወሓት ጉባኤ ምክትል ሊቀመንበር ሆነው የተመረጡት አቶ አማኑኤል አሰፋ በበኩላቸው በሰጡት ምላሽ “እንደ ፓርቲ ስራዎች በሚገመገሙበት ወቅት የግለሰቦች ስም አብሮ ሊነሳ ይችላል እንጂ፤ ስም የማጥፋት ድርጊት የሚባለው ትክክል አይደለም” ማለታቸውን ቪኦኤ አመልክቷል።
ይህ የርስ በእርስ ውዝግብ በጋመበት ወቅት በአፍሪካ ቀንድ የዩናይትድ ስቴትስ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ማይክ ሐመር፣ የፕሪቶሪያውን ስምምነት አፈጻጸም ከተፈራራሚዎቹ ወገኖች ጋር ለመገምገም ሰሞኑን ወደ ኢትዮጵያ እንደሚጓዙ የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት አስታውቋል። አሜሪካ የሃመርን ጉዞ ይፋ ባደረገችበት ዜና ከመንግስትና ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ጋር እንደምትቆም ይፋ ተደርጓል። ምን አልባትም የእነ ዶክተር ደብረጽዮን ቡድን ከሻዕቢያ ጋር የጀመረው አዲስ ግንኙነት ማብቂያ ሊበጅለት እንደሚችልም ግምት አለ።
በማይጨው የተደረገውን ወይይት አስመልክቶ ቲክቫህ እንዳለው የቀድሞ ሌተናል ጀነራል ፃድቃን ስለ ፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ዙሪያ ሃሳቦች ሰጥተዋል።” የሚታየውን ዋናው የልዩነት ነጥብ በፕሪቶሪያ ውል ላይ ያለ የአመለካለት ልዩነት ነው ” ብለዋል።
” ስምምነቱ ዓለም አቀፍ ውል ነው መከበር አለበት ” ሲሉም በቅርቡ ህጋዊ መህናቸውን ለተናገሩት የእነ ዶ/ር ደብረፅዮን ሃይል መልዕክት አስተላልፈዋል። አቶ ጌታቸው ረዳም ። ” የፕሪቶሪያ ውል ለማፍረስ የሚደረግ ማንኛውም እንቅስቃሴ ጦርነትን መጥራት መሆኑ ሊታወቅ ይገባል ” በማለት አሳስበዋል።
የጊዚያዊ አስተዳደሩ መሪና ምክትላቸው በፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት አመለካከትና አተገባበር ዙሪያ የሰነዙሩዋቸው ጠንካራ ትችቶች ተከተሎ የእነ ዶ/ር ደብረፅዮን ሃይል መልስ ሰጥቷል።
የእነ ዶ/ር ደብረፅዮን ሃይል ወገን ሆነው የተናገሩት የፕሪቶሪያውን ስምምነት ውል ከፈረሙት አንዱ ፍስሃ ሃፍተፅዮን (ዶ/ር) ናቸው ። እሳቸው እንዳሉት ትህነግ የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት እንደማይደግፍ ተደርጎ እየቀረበ ያለው ሃሳብ ስም ማጥፋት ነው ” እንደውም ትህነግ በፕሪቶሪያ ስምምነትና አተገባበር የፀና አቋም እንዳለው ገልጸዋል።
የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት በደቡብ አፍሪካ በሚፈፀምበት ወቅት ትግራይን ወክለው በተሳተፉ ተደራዳሪዎች መካከል ልዩነት ተፈጥሮ እንደነበረ አስታውሰዋል። ያስታወሱት እኚሁፈራሚ፣ ጊዚያዊ መንግስት ማቋቋም አለመቋቋም በተደራዳሪዎች መካከል ከነበሩት የሃሳብ ልዩነት እንድ አንድ ነጥብ ጠቅሰውታል።
” በፕሪቶሪያ ተስማምተን መፈረማችን አንድ ፀጋ ሆኖ የቀሩት ጉድለቶች በሂደት እንፈታቸዋለን ብለን አምነን ነው የተመለስነው ” ሲሉ ዶክተር ፍስሃ ገልጸዋል። ” ህወሓት ከሻዕብያ ጋር ግንኙነት አለው የሚለው ወሬ ነጭ ውሸት ነው ” ሲሉ ተናግረዋል።
ባለፈው ሳምንት በተምቤን ፣ በዓዲግራትና በማይጨው ህዝባዊ ውይይቶች ያካሄደው የጊዜያዊ አስተዳደሩ፣ በቀጣይ የጳጉሜን ቀናትም ኣክሱምና እንዳስላሰ ሽረ እንደሚያቀና ተሰምቷል።
በቴሌግራም ይከተሉን https://t.me/+f_kxmaPjD-9jYTdk