አካልን ነፃ ማዉጣት ከህግ አግባብ ዉጭ የታሰረ ሰዉ ከዚህ እስር እንዲፈታ ለፍርድ ቤት የሚቀርብ የፍትሐብሔር ጉዳይ ነዉ፡፡ ነገሩ የሚታየዉ በፍትሐብሔር መዝገብ ቢሆንም በወንጀል ሰበብ የታሰረዉ ሰዉ ይጠቀምበታል፡፡
መግቢያ
የሰዉ ልጆች ሰዉ በመሆናቸዉና በተፈጥሮ ያገኟቸዉ ሰብአዊ መብቶችና ነፃነቶች የተከበሩ ናቸዉ፡፡ ከእነዚህ መብቶች አንዱ ህጋዊ ያልሆነ እስርን የመቃወም መብት (አካልን ነፃ ማዉጣት) አንዱ ነዉ፡፡ የሰዎች የነፃነት መብት የሚገደበዉ ሕጋዊ በሆነ ሥርዓት ብቻ ነዉ፡፡ ይህን ለመጠበቅ ሲባል የአያያዝ ሥርዓትም ሆነ እስር ላይ የሚቆይበት ሁኔታ በሕግ በግልጽ እንዲደነገግ ይደረጋል፡፡ የአያያዝ ሕጋዊነትን ለማረጋገጥ እንዲቻል የያዘዉ ፖሊስ በ48 ስዓት ዉስጥ ወደ ፍርድ ቤት እንዲቀርብ መደረጉ የነፃነት መብትን ማረጋገጫ አንዱ መንገድ ነዉ፡፡ በዚህ አጭር ጽሁፍ አካልን ነፃ ስለ ማዉጣት እና ተያያዥ ጉዳዮችን እንመለከታለን፡፡
አካልን ነፃ ማዉጣት(Habeas Corpus) ምንነት
አካልን ነፃ ማዉጣት /Habeas Corpus/ ቃሉ የላቲን ቃል ሲሆን ትርጉሙም “that you have the body” ማለት ሲሆን ወደ አማረኛ ሲተረጎም አካል (ሰዉ) ይዘሃል የሚል ይሆናል፡፡ ሀብየስ ኮርፐስ ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ተገድዶ እንዳይዘዋወር የተከለከለ ወይም የታሰረ ሰዉ ከዚህ ክልከላ ወይም እስራት እንዲለቀቅ የሚጠየቅበት ሥነ-ሥርዓት ነዉ፡፡ ከእስር እንዲፈታ የሚጠይቅ ሰዉ የታሰረዉ የወንጀል ድርጊት ፈጽመሀል በሚል ቢሆንም ሀብየስ ኮርፐስ የፍትሐብሔር ጉዳይ ነዉ፡፡ አካልን ነፃ ማዉጣት /Habeas Corpus/ ፅንሰ ሀሳብ በመጀመሪያ ተገልፆ የነበረዉ እ.ኤ.አ 1215 ለእንግሊዛዉያን ነዋሪዎች ልዩ ልዩ ነፃነቶችና መብቶችን ይዞ ብቅ ካለዉ ትልቅ ሰነድ /Magna Charta/ ማግና ካርታ ነዉ፡፡ መርሁም የንጉሶች ሳይሆን የህግ የበላይነት እንዲኖር ማድረግ ነዉ፡፡ ማንም ሰዉ ከሕግ ዉጪ በማንም ሊያዝ፣ ሊታሰር፣ ሊታገት እና እንቅስቃሴዉም ሊገደብ አይገባዉም የሚሉ ዓለም አቀፋዊ መርሆችን አቅፎ የያዘ ነዉ፡፡ ነፃነት ሊገደብ የሚችለው በህግ ሥርዓት (Due Process of law) ጠያቂና ተጠያቂነት በሰፈነበት መልኩ ሊሆን ይገባል በማለት የማግና ካርታ የዉስጥ ይዘት ያስረዳል፡፡
የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ዓለም አቀፍ ቃል ኪዳን (International Convention on Civil and Political Rights) ሀገራችን ያፀደቀችው የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ዓለም አቀፍ ቃል ኪዳን በአንቀጽ 9(1) ማንኛዉም ሰዉ የግል ነፃነቱና ደህንነቱ እንዲረጋገጥለት መብት እንዳለው አመልክቷል፡፡ ማንኛዉም ሰዉ በህግ ከተደነገገዉ ምክንያትና ሥርዓት ዉጭ የግል ነፃነቱ አይነፈግም፡፡ በስምምነቱ አንቀጽ 9(4) መሰረትም ማንኛዉም በመታሰሩ ወይም በመያዙ ምክንያት ነፃነቱን የተነፈገ ሰዉ የእስራቱን ሕጋዊነት ወዲያዉኑ መርምሮ ያለአግባብ መታሰሩን ካረጋገጠ በነፃ እንዲለቀቅ እንዲያዝለት ፍርድ ቤት የመቅረብ መብት አለዉ፡፡
የአካል ነፃነት አቤቱታ አቀራረብ እና አወሳሰን ሥነ-ሥርዓት
አካልን ነፃ ማዉጣት ከህግ አግባብ ዉጭ የታሰረ ሰዉ ከዚህ እስር እንዲፈታ ለፍርድ ቤት የሚቀርብ የፍትሐብሔር ጉዳይ ነዉ፡፡ ነገሩ የሚታየዉ በፍትሐብሔር መዝገብ ቢሆንም በወንጀል ሰበብ የታሰረዉ ሰዉ ይጠቀምበታል፡፡ በፍ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ 177 መሰረት በወንጀል ሕግ ወይም በዚህ ሕግ የተነገረዉን መሰረት በማድረግ ፍርድ ቤት ሳይወስንበት ወይም ሳይፈርድበት ማናቸዉም ሌላ ትዕዛዝ ሳይሰጥ በማናቸዉም ሌላ ስልጣን ወይም በሌላ ሁኔታ ወይም በሌላ ሰዉ የተገደደ፣ እንዳይዘዋወር የተከለከለ፣ የተያዘ ወይም የታሰረዉ ሲኖር ይህ አድራጎት እንዲወገድለትና እራሱ ፍርድ ቤት ቀርቦ እንዲያስረዳ ሊያመለክት ይችላል፡፡ የመያዙ ወይም የመታሰሩ ትዕዛዝ የተሰጠዉ በሕግ ባለስልጣን ቢሆንም መያዙ ወይም መታሰሩ የተፈፀመበት ሁኔታ ሕግን ተቃራኒ በሆነ መንገድ ከሆነ አቤቱታ ማቅረብ ተገቢ ነዉ፡፡ በተገዳጅ የሚቀርበዉ ማመልከቻ በመሀላ-ቃል የተደገፈ ሆኖ የተያዘዉን ወይም የተገደደዉን ሰዉ ስም፣ የአስገዳጁን ሰዉ ስም፣ ተገዶ የተያዘበትን ስፍራ፣ ይህንኑ የሚያረጋግጡ ሰዎች እንዳሉ የምስክሮችን ስምና አድራሻ ዘርዝሮ የሚገለጽ ሊሆን ይገባል፡፡ የተያዘዉ ሰዉ ራሱ መቅረብና የመሀላ-ቃሉን መስጠት የማይችል ከሆነ ሌላ ሰዉ ሊያቀርብለት የሚችል ሲሆን በዚህ ሁኔታ አቤቱታውን የሚያቀርበው ሰው በሚሰጠዉ መሀላ ላይ ዋናዉ ባለጉዳይ ለመቅረብ ወይም ማመልከቻ ለመፃፍ ያልቻለ መሆኑን ጨምሮ ሊገለፅ ይገባል፡፡
በፍትሐብሔር ሥነ-ሥርዓት ሕግ ቁጥር 15(2)(ቀ) መሰረት የሚቀርበዉን አቤቱታ የመቀበል ስልጣን ሙሉ በሙሉ የከፍተኛዉ ፍርድ ቤት ሥልጣን ነዉ፡፡ በዚህ መሠረት ከፍተኛዉ ፍርድ ቤት ማመልከቻ ሲቀርብለት አስገዳጁ ወይም አሳሪዉ ተገዳጁን ወይም ታሳሪዉን ሰዉ ይዞ እንዲቀርብና ይህንንም ሰዉ የማይለቅበትን ምክንያት እንዲያስረዳ በመጥሪያዉ ላይ የመቅረቢያዉን ቀነ ቀጠሮ ወስኖ ትዕዛዝ ይሰጣል፡፡ እንዲሁም ለፍርድ ቤቱ በቀረበዉ ማመልከቻ ላይ ነገሩን በምስክርነት ለማስረዳት ይችላሉ ተብለዉ የተጠቀሱት ምስክሮች እንዲቀርቡ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሊሰጥ ይችላል (የፍ/ /ሥ/ሥ/ህ/ቁ 178)፡፡
በፍ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ 179 መሰረት ጉዳዩ በሚሰማበት ቀን በቀረበዉ ማመልከቻ ላይ የተገለፀዉን አቤቱታ እዉነተኛነት ፍርድ ቤቱ ይመረምራል፡፡ ስለማስረጃዉም ተገቢ መስሎ የታየዉን ትዕዛዝ ይሰጣል፡፡ አመልካቹ የተያዘዉ ሕገ-ወጥ በሆነ መንገድ መሆኑን ፍርድ ቤቱ ከተረዳዉ ወዲያዉኑ እንዲለቀቅ ትዕዛዝ ይሰጣል፡፡ የዚህ ዓይነት ትዕዛዝ ከፍርድ ቤት ከተሰጠ በኋላ ማናቸዉም ሌላ ትዕዛዝ እንዲኖር ሳያስፈልግ የፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ብቻ በቂ ሆኖ መፈፀም አለበት፡፡ በሌላ በኩል ማመልከቻዉ ላይ የተገለፀዉ የአቤቱታ ቃል በማናቸዉም ሁኔታ ለፍርድ ቤቱ የሚያጠራጥር መስሎ የታየዉ እንደሆነ አቤት ባዩ ዋስ ጠርቶ እንዲለቀቅ ሊያዝ ይችላል፡፡ ይህ ዋስትና የገንዘብ ማስያዝ ወይም የሰዉ ዋስ ሊሆን ይችላል፡፡ በዋስትናዉም የሚገባዉ ግዴታ እንዲለቀቅ ያደረገዉ ፍርድ ቤት በፈለገዉ ጊዜ እንዲቀርብ ወይም ማንኛዉንም ፍርድ ቤቱ የሚሰጠዉን ትዕዛዝ አክብሮ እንዲፈፅም የሚያስገድድ ይሆናል ፡፡
ማጠቃለያ
አካልን ነፃ ማውጣት (Habeas Corpus) የሰዎች ሰብአዊ ነፃነት በህገወጥ መንገድ እንዳይጣስ ለመከላከል አስፈላጊ የሆነ ሥርዓት ሲሆን በሀገራችንም የህግ ጥበቃ ያለው መሆኑን በመረዳት ህብረተሰቡ ከህግ ውጪ የሆነ መያዝ ወይም መታሰር ሲያጋጥመው ይህን ህጋዊ መፍትሄ በመጠቀም መብቱን በማስከበር እና ህገወጥነትን በመካላከል የበኩሉን ሊወጣ ይገባል፡፡
ፍትህ ሚኒስቴር ትምህርት ክፍል