በቅርቡ በባሕር ዳር ከተማ ውስጥ የተፈጸመው የእገታ ወንጀል ብዙዎችን አስገርሟል፡፡ ሁለት ወጣቶች ሠርጋችሁን የአብረሃም እና የሣራ ያድርግላችሁ ሊባሉ አንድ ቀን ብቻ ቀርቷቸዋል፡፡ በማግሥቱ ለሠርጉ የተጠራው እድምተኛ ወደ ሠርጉ ቤት ሲመጣ ግን ያጋጠመው ያልተጠበቀ ነገር ነው፡፡ ለሠርጉ በተጣለው ድንኳን ውስጥ አናስገባም ሠርገኛ ከሚለው ዘፈን ይልቅ ሀዘንተኞች ተቀምጠውበታል፡፡
አጋቾች ሙሽሮችን አግተው ሦስት ሚሊዮን ብር መጠየቃቸው የሙሽሮችን ቤተሰብ ምን ያህል እንደሚያስጨንቅ ገምቱት፤ ለሦስት ጉልቻ በቁልኝ የተባሉት ወጣቶች ሦስት ሚሊዮን ብር የተጠየቀባቸው መከራ አምጪዎች መኾናቸውንም አስቡት። አንድ አነስተኛ ክሊኒክ ከፍቶ የሚሠራን ባለሙያ ሦስት ሚሊዮን ካላመጣህ ሙሽራ ልጅህን በሕይወት አታገኛትም ሲባል ምን ሊሰማው እንደሚችል ራሳችንን በሱ ቦታ አድርገን እናስበው፡፡
ከላይ ያነሳነውን የእገታ ወንጀል ለአብነት አነሳነው እንጂ በአማራ ክልል ውስጥ ከዚህም የከፉ የእገታ ወንጀሎች በስፋት እየተፈጸሙ ነው፡፡
ከሕጻናት እስከ አዛውንት፣ ከሙሽሮች እስከ ባለትዳሮች፣ እናቶች እስከ ልጆች እየታገቱ ገንዘብ ተጠይቆባቸዋል፡፡ ለታጋቾች ገንዘብ መክፈል የቻሉትም ኾኑ ያልቻሉት ታጋቾቻቸውን በሞት ተነጥቀዋል፡፡ የስቃይ እንባንም አንብተዋል፡፡
የእገታ ወንጀሉ በአሳዛኝ ሁኔታ የሚያልቅ ወንጀል ከኾነም ሰነባብቷል፡፡ ተዋናዮቹም የጭካኔን ጥግ በማሳየት ወደር የለሽ ወንጀሎኞች ኾነዋል፡፡
ማኅበረሰቡ በጉያው ያቀፋቸውን አጋቾች መቼ ለሕግ እንደሚያቀርባቸው መገመት አይቻልም፡፡ “ነግ በእኔ” ይሉትን የአበው ብሂል ከዘነጋነውም ሰነባብተናል፡፡
አጋቾች በጠራራ ፀሐይ ሰው እያገቱ ለሻንጣ የሚከብድ ገንዘብ ይጠይቃሉ፡፡ የታጋች ቤተሰቦች ለአጋቾቹ የሚኾን ገንዘብ ወደ አደባባይ ወጥተው ይለምናሉ፡፡ የኑሮ ውድነት ወገቡን ያጎበጠው የዋህ ማኅበረሰብም ከጉሮሮው ነጥቆ ለአጋች ጉሮሮ ጀባ ይላል፡፡
ይሄ የሚቀጥለው እስከመቼ ነው?
አንድ ሰው ታገተ ሲባል ይደነግጥ የነበረው ውስጣችን የብዙዎችን እገታ ተለማምዶታል፡፡ ከመጋረጃ ጀርባ የነበረው የእገታ ወንጀልም የአደባባይ ሥራ ኾኗል፡፡
አሁንም ጥያቄው በዚህ መልኩ የምንቀጥለው እስከ መቼ ነው? የሚለው ነው፡፡ ሕግ ማስከበር የመንግሥት ተቀዳሚ ኀላፊነት ቢኾንም ሕግ የተላለፉ ሰዎችን በጉያችን መደበቁ ግን የኛ ስህተት መኾኑን ማመን ይኖርብናል፡፡
በእርግጥ የአደባባይ ዘረፋዎች እና በጠራራ ፀሐይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን ስንመለከት ሕጉ እና ሕግ አስከባሪዎቹስ ወዴት አሉ? ማለታችን ስህተት አይኾንም፡፡
”ሕጋችንም ታግቶ ይኾን እንዴ“ ብለን ብንጠይቅም ስህተት የማይኾነው ሁሉም ወንጀሎች የሚፈጸሙት የሕግ አካላት በቅርበት ባሉባቸው ትላልቅ ከተማዎች ውስጥ ጭምር ስለኾነ ነው፡፡
ባሕር ዳርን የእገታ ወንጀል መናኽሪያ እንድትኾን ስንፈቅድ፣ ውበቷ ጠርቷቸው ወደ እሷ የሚመጡትን ሰዎች እንዲፈሩ እያደረግን መኾኑን መዘንጋት የለብንም፡፡ ባሕር ዳርን ለአብነት አነሳን እንጂ ጎንደርም፣ ደብረ ማርቆስም፣ ደሴም፣ ደብረ ብርሃንም ኾኑ ሌሎች የክልሉ ከተሞች ውስጥ ችግሩ ተመሳሳይ ነው፡፡
ባሕር ዳርን ወይም ሌሎችን የክልሉ ከተሞች የዝርፊያ እና የእገታ ጥላሸት ሲቀቧቸው እያየን ዝም ማለታችን ወይም ችግሩን ለሕግ አስከባሪዎች ብቻ የተውን ሰዎች ቆም ብለን የምናስብበት ጊዜ አሁን ነው፡፡
በክልሉ በሁሉም አከባቢዎች የሚደረጉ እገታዎችን ማውገዝ ያለብን በጋራ ነው፡፡ የሕግ አካላት ተግባራቸውን በአግባቡ እንዲፈጽሙ እየወተወትን እኛም ግን ጥላሸት እየተቀባ ላለው እሴታችን ዘብ መቆም ይገባናል፡፡
አጋቾች በክልሉ ውስጥ ያለውን የሰላም መደፍረስ ሳይቆርጡት የደረሳቸው ሎተሪ አድርገው ሲዘርፉን እና ሲያግቱን ዝም ማለታችን በጣም ስህተት ነው፡፡ ስንዘረፍም ኾነ ስንታገት የፀጥታ አካላት አልደረሱልንም የሚል ሰበብ መደርደሩ መፍትሔ አያመጣልንም፤ ይልቁንም በጋራ ቆመን ችግር ፈጣሪዎችን ልንታገላቸው ይገባል፡፡
አሚኮ