የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን በቅርቡ ባካሄደው ውይይት በሥሩ የሚያስተዳድራቸውን ፓርኮች ወደ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን የመቀየር ፍላጎት እንዳለውና ለዚህም በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ እንዳለ መግለጹ ይታወቃል። ለመሆኑ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ለውጥ ያለው ፋይዳ ምንድነው?
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሰሃ ይታገሱ (ዶ/ር) እንደሚሉት፤ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን በሀገሪቱ 13 ፓርኮች የሚያስተዳድር ሲሆን፤ ከነዚህ ውስጥም አንዱ የድሬዳዋ ነጻ የንግድ ቀጣና ነው። ፓርኮቹ መንግሥት የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪውን ለመደገፍ የተቀናጀ መሠረተ ልማትን ያቀረበባቸው ናቸው።
በአሁኑ ወቅትም የአንድ መስኮት አገልግሎት መስጠት በሚያስችል መልኩ የሚተዳደሩ ሲሆን የአምራች ዘርፉን በሚገባ እየደገፉ ይገኛሉ። አጠቃላይ እነዚህን ፓርኮች ለማልማት የወጣው ገንዘብ ወደ አንድ ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ዶላር እንደሚሆን የሚጠቅሱት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፤ መንግሥት ካለው ቁርጠኝነት ፓርኮቹን በርካታ ገንዘብ አውጥቶ መደገፉን ይናገራሉ።
እስካሁንም በፓርኮቹ ውስጥ 85 በመቶ የሚሆኑ ሼዶችና የለማ መሬትም መያዙንም አስታውቀዋል። 15 በመቶ ያህሉን እስካሁን ባለሀብቶች ገብተው እየተጠቀሙበት እንዳልሆነም ጠቁመዋል። በተለያዩ ዓለም አቀፍና የሀገር ውስጥ ሁኔታዎችም ሼዶችን የመልቀቅ ሁኔታ እንዳለ አመላክተዋል። ለወደፊት የኢንቨስትመንት ማስፋፊያ ሰፊ ቦታ መኖሩንም ገልጸዋል።
በፓርኮቹ ውስጥ ካሉት 147 የሚሆኑ ኢንቨስተሮች 51 በመቶ ያህሉ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች እንደሆኑ በመጥቀስ፤ ከዚህ ቀደም ፓርኮቹ ሲሠራ በዋናነት ታሳቢ ተደርጎ የነበረው የኤክስፖርት ምርቶች የሚመረቱበት እንዲሆን ነበር ብለዋል። በአሁኑ ወቅት የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች በስፋት እየገቡና ከውጪ ባለሀብቶች ጋር እየሰሩ መሆናቸውን አብራርተዋል። 70ሺህ የሚሆኑ ሠራተኞችም በእነዚህ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ተቀጥረው እንደሚሰሩ ጠቁመዋል። አብዛኞቹም ሴቶችና ወጣቶች መሆናቸውን ተናግረዋል።
ዋና ሥራ አስፈጻሚው እንደሚሉት፤ በፓርኮቹ አማካኝነት ኤክስፖርት ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ ከአንድ ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ዶላር በላይ ኤክስፖርት ማድረግ ተችሏል። ይህ ቁጥር ብዙ የሚባል አይደለም። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ ፓርኮቹ የወጪና ገቢ ምርት ሚዛን ላይ እንዲያተኩሩ ተደርጓል።
የኤክስፖርት አፈጻጸም ደካማነት፣ የሀገሪቱ የጸጥታ ችግሮች፣ የመሠረተ ልማት እጥረት ለፓርኮቹ ተግዳሮት የፈጠሩ ጉዳዮች መሆናቸውን፤ ከዚህም ባሻገር በኢንቨስተሮች በኩል የሚነሱ የውጭ ምንዛሪ እጥረት፣ ቢሮክራሲ፣ መሠረተ ልማት፣ የቁጥጥር ሥርዓትና የህጎች በፍጥነት መቀያየር ቅሬታዎች መኖራቸውን ዋና ሥራ አስፈጻሚው አንስተዋል። እነዚህንና መሰል ችግሮችን በመቅረፍ በልዩ ትኩረት ፓርኮቹን ወደ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን ለመቀር እየተሠራ እንዳለም ነው የገለጹት።
“ስናለማ የቆየነው በተለይም ኤክስፖርትን መሰረት ያደረገ ፓርክ ነበር። አሁን ላይ ተጨማሪ ሥራዎችን በማካተት ወደ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን መቀየር አለብን” ብለዋል። ይህም በቀጣዮች ከአምስት እስከ አስር ዓመታት ውስጥ ተፈጻሚ እንደሚሆን ነው የገለጹት። ለዚህም የህግ ጉዳዮችን ጨምሮ በርካታ ሂደቶች መጠናቀቃቸውን አብራርተዋል።
ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ፍላጎቱ በሀገሪቱ ተግባራዊ የተደረጉ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን ተከትሎ ሲሆን፤ ፓርኮቹ አሁን ካሉበት አፈጻጸም የላቀ የኢኮኖሚ አበርክቶ እንደሚኖራቸው ጠቅሰዋል። ኢንዱስትሪን መሰረት ያደረጉ የንግድ ሥርዓቶችን ለመዘርጋትና ኤክስፖርትን በማብዛት የወጪ ገቢ ንግድ ሚዛኑንም ይበልጥ ለማስጠበቅ ይረዳል ብለዋል።
እርሳቸው እንዳሉት፤ ፓርኮቹ ወደ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን ሲቀየሩ ማኑፋክቸሪንግ ብቻ ሳይሆን የንግድና ሎጀስቲክስ እንዲሁም የፋይናንሺያል አገልግሎት በፓርኮች ውስጥ እንዲኖሩ ያስችላል። በተለይም ከውጭ ምንዛሪ እጥረት ጋር ተያይዞ የሚፈጠሩ ችግሮችን ለመፍታት የውጭ ባንኮች ገብተው የምንዛሪ አገልግሎት እንዲሰጡ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል። ይህም የዘመናዊነት ማዕከልነታቸውን ያስጠብቃል።
የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ፤ ዛሬ ላይ ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገር ኬንያ ብልጫ ያለው ኢኮኖሚ ገንብታለች። ሆኖም የኢትዮጵያ ውድድር በዓለም አቀፍ ደረጃ በመሆኑ አዳዲስ የማክሮ ኢኮኖሚ ለውጦችን ተግባራዊ ማድረጓ የግድ ነበር ይላሉ። ከዚህ ውስጥም ልዩ የኢኮኖሚ ዞን እሳቤን ተግባራዊ ማድረግ አስፈላጊ መሆን ይጠቅሳሉ።
አቶ ዘመዴነህ፤ ለማኑፋክቸሪንግ ተብለው የተከፈቱ ፓርኮች የአገልግሎት ዘርፉን ጨምሮ ተጨማሪ አገልግሎት እንዲሰጡ ታስበው ወደ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን የሚያደርጉትን ግስጋሴ በመደገፍ የዶክተር ፍሰሃን ሃሳብ ይጋራሉ። ዘመናዊ የሆኑ በምዕራቡ ዓለም የሚገኙ የኢኮኖሚ ዞኖች ስኬት የተገኘው በአምራች ዘርፉ ብቻ ሳይሆን የአገልግሎት ሴክተሩንም በመያዛቸው ጭምር ነው ብለዋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ በዋጋም በጥራትም ተወዳዳሪ መሆን የሚቻለው ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ሲኖር ነው በማለት፤ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ሲኖር ታላላቅ ኩንያዎች ገብተው ኢንዱስትሪውን ተወዳዳሪ የማድረግ እድሉ እንዳለቸው ያብራራሉ።
ልዩ ኢኮኖሚ ዞን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ መሆን ስላለበት የውጭ ኢንቨስትተሮችን ጨምሮ የግል ሴክተሩን በብዛት ማሳተፍ እንደሚቻልና፤ ለዚህ ደግሞ በቴሌኮም፣ በትራንስፖርትና በባንኪንግ ሲስተም የታዩ ለውጦች አመቺ ሁኔታን እንደሚፈጥሩ ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት ዱባይን ጨምሮ በርካታ ልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች በዓለም አቀፍ ደረጃ መኖራቸውን ጠቅሰው፤ የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ተወዳዳሪነትም በዓለም አቀፍ ደረጃ ሊታወቁ በሚችሉ ነጻ የንግድ ቀጣናና ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች ውስጥ ባሉት ኢንዱስትሪዎች አማካኝነት እንደሚሆን አስገንዝበዋል።
በሚቀጥሉት 25 ዓመታት ውስጥ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እስከ አንድ ነጥብ 7 ትሪሊዮን የአሜሪካ ዶላር ሊደርስ እንደሚችል፤ በሚቀጥሉት 40 ዓመታት ውስጥ ደግሞ በዓለም ውስጥ ካሉት 20 ትላልቅ የኢኮኖሚ ባለቤቶች ከሚባሉት ኢትዮጵያ አንዷ እንደምትሆን፤ ምናልባትም ከነ ሳዑዱ አረቢያና ቱርክ ልትበልጥ እንደምትችል ዓለም አቀፍ ትንበያዎችንና ጥናቶችን መነሻ አድርገው የሚገልጹት አቶ ዘመዴነህ፤ እዚህ ላይ ለመድረስ ከቀጣናዊ የንግድ ውድድር ወደ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት መግባት እንደሚያስፈለግ እና ለዚህ ደግሞ ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች ወሳኝ ሚናን እንደሚጫወቱ አዲስ ዘመን ያነጋገራቸው አስረድተዋል።