“ማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚ ማኅበራዊ ኀላፊነት አለብኝ ማለት ይጠበቅበታል” ነገሠ በላይ (ዶ.ር)
ሃሰተኛ መረጃዎች ሀገር እያመሱ፣ ማኅበራዊ መስተጋብርንም እያናጉ ነው፡፡ በሀሰተኛ መረጃዎች ምክንያት መቃቃሮች፣ አለመግባባቶች፣ ግጭቶች፣ ጦርነቶች እና ቀውሶች ሲፈጠሩ ተስተውለዋል፡፡
ሀሰተኛ ምላስ በምትጠላበት ማኅበረሰብ ውስጥ ሀሰተኛ ምላስ ነግሳ ሀገር ሰላም እንዳይኖራት፣ ፍቅር እንድታጣ፣ እረፍት እንዲርቅ እየኾነ ነው፡፡
ብዙዎች ሀሰተኛ መረጃዎችን ያቀርባሉ፣ ያጋራሉ፣ ሌሎችም ሀሰተኛውን መረጃ ተቀብለው ያደርሳሉ፡፡ ይህ ደግሞ ዕውነትን እያቀጨጨ፣ ሀሰትን እያገዘፈ፣ በሀገር እና በሕዝብ ላይ ጉዳት እያደረሰ ነው፡፡
በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት እና ሥነ ተግባቦት ትምህርት ክፍል መምህር እና የትምህርት ክፍሉ ኀላፊ ነገሠ በላይ (ዶ.ር) አሁን ያለንበት ወቅት መረጃ በስፋት የሚሰራጭበት ወቅት ነው ይላሉ፡፡ ቀደሞ ከነበረው ልምድ አንጻር አሁን ላይ መረጃ በስፋት የሚሰራጭበት በመኾኑ እንደ መረጃው ብዛት የመረጃውን ጥራት ማረጋገጥ ይገባል ነው የሚሉት፡፡
የሚዲያ ተከታታዮች መረጃው ከእነማን ነው የተሠራጨው? ለምን ዓላማ ነው የተሠራጨው? የሚለውን መፈተሸ እና መረዳት እንደሚገባቸውም አመላክተዋል፡፡
የመረጃ ስርጭቱ በበዛ ቁጥር የተሳሳተ መረጃም በዛው ልክ እንደሚተላለፍ ነው የተናገሩት፡፡ መረጃን ሳናጣራ የምንጠቀም ከኾነ በተሳሳተ መረጃ ወደ ተሳሳተ መንገድ ልንሄድ እንችላለን፣ መረጃ እና ቴክኖሎጅ በራሳቸው ጎጅዎች አይደሉም፣ ጎጅዎች የሚኾኑት የተሳሳተ መረጃን ሰዎች ለዓላማ ሲጠቀሙበት የዛ ተከታይ ስንኾን ነው ይላሉ፡፡
በመረጃ ልውውጥ ውስጥ የተሳሳተ መረጃ ሊኖር እንደሚችል ያመላከቱት ምሁሩ የተሳሳተ መረጃ በሚዲያ ሲኾን ይጎላል፣ የሚያደርሰው ጉዳትም ሰፊ እና ከፍተኛ ነው፣ ብዙ ችግርም ይፈጥራል፣ ወደ አላስፈላጊ ውዝግብ፣ ወደ ግጭት፣ ጦርነት እና ቀውስ ያመራል ነው የሚሉት፡፡ የተሳሳተ መረጃ በአማራ ክልልም ኾነ በሀገር ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ መኾኑን ነው ያመላከቱት፡፡
መረጃውን የሚያይ እንጅ ከየት ነው? ለምን ነው? ብሎ ሰከን ብሎ የሚያይ ማኅበረሰብ ስላልተፈጠረ እንደ ሀገር በተሳሳተ መረጃ ተጎጅዎች ኾነናል ነው የሚሉት፡፡ መረጃዎችን መዝኖ መጠቀም ካልተቻለ ጉዳታቸው ሰፊ ነው የሚሉት ምሁሩ መረጃዎች የሚለቀቁት፤ ለፖለቲካ፣ ለማኅበራዊ እና ለሌሎች ዓላማወች ሊኾን ይችላል፣ አሰራጩ አካል የራሱ የኾነ ዓላማ አለው፣ እዚህ ላይ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል ይላሉ፡፡
በችግር ወቅት የተሳሳተ መረጃ የበለጠ ችግሩን እንደሚያባብሰው እና እንደሚያከፋው ነው የሚያነሱት፡፡ ከተሳሳተ መረጃ ምን አልባት መረጃውን የሚያሰራጨው አካል የሚያገኘው ምጣኔ ሃብታዊ ጥቅም ካልኾነ በስተቀር ለማኅበረሰብ ጥቅም የለውም፣ በተሳሳተ መረጃ የሚጎዳው ብዙ ነው ይላሉ፡፡
በማኅበራዊ ሚዲያ የሚዘዋወረውን መረጃ ዝም ብሎ መውሰድ ሳይኾን ሃሳቡን ማየት፣ ሃሳቡን ያጋራውን አካል መመርመር፣ ቀደም ሲል ያጋራቸውን መረጃዎች፣ የግለሰቡን ጓደኞች ማየት፤ ተስፋ የሚጣልበት ሰው መኾኑን ማየት እና ትክክለኛነቱን ማረጋገጥ ይጠበቃል፤ እንዲህ ሳያደርጉ መረጃን ዝም ብሎ መውሰድ ተገቢ አይደለም ነው የሚሉት፡፡
እንደ ምሁሩ ገለጻ አንዳንድ መረጃዎች ከዓመታት በፊት የተጋሩ ሊኾኑ ይችላሉ፣ ለኾነ ዓላማ ሲፈለጉ ደግሞ ዛሬ ላይ ሊወጡ ይችላሉ፣ ሰውም ያን አይቶ ዛሬ እንደኾነ እና እንደተደረገ አድርጎ ይከተላል ይሄ ልክ አይደለም ብለዋል፡፡
መረጃዎችን ፈጥኖ ለሰዎች ከማጋራት በፊት መረጃዎችን መመዘን እንደሚጠበቅ ነው ያመላከቱት፡፡ የተማረው እና ያልተማረው ሁሉ በማኅበራዊ ሚዲያ ተደበላልቋል፣ ኢንተርኔት እና ዘመናዊ የእጅ ስልኮች ያሉት ሁሉ በማኅበራዊ ሚዲያ በአንድነት ይጋራል፤ የምንከተለው የማኅበረሰብ፣ የፖለቲካ እና የምጣኔ ሃብት አንቂ፣ የሃይማኖት መሪ ማነው? የምንከተለው ተጽዕኖ ፈጣሪ ማነው? የሚለው ሁሉ ተደበላልቋል፤ ሁሉም ሰው መረጃ ያጋራል፣ ሁሉም ሰው መረጃ ይጠቀማል፣ የመረጃ መጥለቅለቅ እኛንም እያጥለቀለቀን ወደ ጎርፍ ውስጥ እየገባን ነው ይላሉ፡፡
በዘርፉ በጣም ዕውቀት ያላቸውን፣ ዕውነታን የሚያጣሩ ተቋማትን መከተል እንደሚገባም አንስተዋል፡፡ የሚያጠራጥሩ መረጃዎችን ሃቅ ለሚያጣሩ ተቋማት በመላክ ማረጋገጥ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡ ለመረጃ አጠቃቀም ትዕግሥት ያስፈልጋል፣ ማኅበራዊ ሚዲያ በፈጠነ ቁጥር የሃሰተኛ መረጃዎች ሰለባ መኾን እንደማይገባ ነው የሚናገሩት፡፡ ሃሰተኛ መረጃዎችን ከማጋራት በፊት ሀሰተኛ መረጃዎች የሚጎዷቸው አካላት መኖራቸውን ማረጋገጥ ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡
እንደ ምሁሩ ገለጻ ተመራጩ መረጃውን ከማጋራት በፊት ትክክለኛ መኾን አለመኾኑን ማረጋገጥ እንጅ አጋርቶ ሰዎች ላይ ጉዳት ካደረሰ በኋላ ማረጋገጥ ትክክል አይደለም፡፡ መረጃን ከማጋራት አስቀድሞ በመረጃው እነማን ይጠቀማሉ፣ እነማንስ ይጎዳሉ የሚለውን በስክነት ማየት እና መመርመር እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡ የተገኘን መረጃ ሁሉ ሰው እንዳይቀድመኝ በሚል ሰበብ ብቻ ማጋራት አደጋው እና ጉዳቱ የከፋ እንደኾነ ነው የሚያብራሩት፡፡
ያልተጨበጠ መረጃን ማውራት በማኅበረሰባችን ባሕልም የተወደደ አይደለም የሚሉት ምሁሩ በማኅበራዊ ሚዲያም እነ እገሌ አሉ እያሉ መረጃዎችን ሳያረጋግጡ ማውራት ተገቢ አይደለም ነው የሚሉት፡፡ ብዙዎች በግለሰቦች፣ በተቋማት እና በሌሎች ስም መረጃዎችን እያሳሳቱ እንደሚያሰራጩ ነው የተናገሩት፡፡ እውነታን ማጣራት የሚቻልባቸው ዘዴዎች መኖራቸውንም አንስተዋል፡፡ ቴክኖሎጅ ችግሩንም መፍትሔውንም አብሮ ይሰጣል፣ ነገር ግን በእኛ ሀገር የቴክኖሎጅውን ጉዳት ነው የምንጠቀመው ነው የሚሉት፡፡
እንደ ምሁሩ ገለጻ ማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚ ማኅበራዊ ኀላፊነት አለብኝ ማለት ይጠበቅበታል፡፡ መስከን እና መመዘንም አለበት፡፡ ማኅበራዊ ሚደያ በቀደደው ቦይ ብቻ መፍሰስ ተገቢ አለመኾኑንም አስገንዝበዋል፡፡ መረጃዎችን ከማጋራት አስቀድሞ ትርፍ እና ኪሳራ መሥራት እንደሚጠበቅም አመላክተዋል፡፡
መረጃ መስጠት፣ ማዝናናት እና ማስተማር የሚዲያ ተግባራት መኾናቸውን ያመላከቱት ምሁሩ ሚዲያው ዓላማዎችን ለማሳካት ሂደቶችን መጠቀም ይገባል ነው ያሉት፡፡ ማኅበራዊ ሚዲያ መረጃዎችን በፍጥነት ስለሚያሰራጭ እና ሂደቶቹም እንደ ሜንስትሪም ሚዲያዎች ስላልኾነ ለሀሰተኛ መረጃ ስርጭት የተጋለጠ መኾኑን ነው የተናገሩት፡፡ የሀሰተኛ መረጃዎች እንዲሰፉ ያደረገው አንደኛው ምክንያት እንደ ሀገር ያሉ የግልም ኾኑ የመንግሥት ሚዲያዎች ብዙኀኑን ወገንተኛ ያደረጉ አለመኾናቸው ነው ይላሉ፡፡
ይህም ሰው እነዚህን ሚደያዎች ከመከተል ወጥቶ የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚ እንዲኾን አስገድዶታል ነው የሚሉት፡፡ እንደ ስማቸው ብዙኅን ቢኾኑ፣ የብዙኀኑ ድምጽ ቢሰማባቸው የማኅበራዊ ሚዲያው ተጽዕኖ ይቀንስ ነበር ይላሉ፡፡
የግል ሚዲያዎች ስፖንሰር ካላቸው የስፖንሠራቸውን መልዕክት ነው የሚያስተላልፉት፣ ማኅበረሰቡ ወደ ማኅበራዊ ሚዲያ እንዲሄድ ያደረገው የሜኒስትሪም ሚዲያው ድክመት ነው ብለዋል፡፡ የመረጀ አሰጣጡን ተመጣጣኝ ማድረግ እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል፡፡ በዋናነት ግን የመረጃ አጠቃቀምን፣ በጥንቃቄ፣ በትዕግሥት፣ በሚዛን እና በኀላፊነት መኾን እንደሚገባው ነው ያስገነዘቡት፡፡
አሚኮ
TIPS
The Wars We Still Can Stop
Ethiopia: Israel Foreign Minister Says His Country Wants to Be Part of Ethiopia’s Success
A Nation Silenced: How the 1993 Referendum Stripped All Ethiopians of Their Sea
The 1976 TPLF Manifesto: TPLF’s “Republic of Greater Tigray”
Away from the global spotlight, Eritreans are trapped in a garrison state
Testimonials of a Sudanese Intelligence Officer on the Proxy war between Sudan and Ethiopia from 1970s to early 1990s
Ethiopia-Eritrea Tension: A Volatile History that Never Truly Ended – Could Assab Become Africa’s Crimea?
“As an outlier among the five tplf leaders, I wasn’t part of the armed struggle tradition”
Former Tigray fighters say no to war
Don’t Risk Your Future: The United States Cracks Down on Illegal Immigration
Counter-Video by EBC Challenges EBS Broadcast, Sparks Public Outcry Over Alleged Misinformation
Ethiopia and Eritrea Slide Closer to War amid Tigray Upheaval
Sea Outlet Serious and Unabated Agenda for Ethiopia: Retired Lieutenant General Yohannes
Israel’s Peace With Egypt Is Starting to Crack
Egyptian, Eritrean FMs reject involvement of non-bordering countries[Ethiopia] in Red Sea security
Ethiopia, Creditors Agree on $8.4 Billion Debt Restructuring