የአበው አደራ ያለባትን፣ እልፍ አዕላፍ መስዋዕት የተከፈለባትን፣ ደምና አጥንት ያጸናትን፣ ሕይወት የተገበረላትን፣ የነጻነት ጀምበር የማትጠልቅባትን፣ የአንድነት ኀይል ያቆያትን፣ ቃል ኪዳን ያለባትን፣ ምህረት እና በረከት የማይነጥፍባትን ኢትዮጵያን ጠብቋት፡፡ ለክብሯም ቁሙላት፡፡ ለሰላሟ ዘብ ሁኑላት፡፡
ለክብሯ ሲባል ረሃብ እና ጥም የተቻለላትን፣ ክረምት እና በጋ የተረሳላትን፣ ምቾት የተዘነጋላትን፣ ልጆቿ በውርጭ እና በሐሩር የተረማመዱላትን፤ አበው እና እመው ከአንቺ በፊት እንቅደምልሽ ያሏትን፣ እየቀደሙ ለክብሯ እየወደቁ ያቆሟትን፣ በጠላቶቿ ፊት ግርማ ያሰጧትን፣ በጠላት ሳያስነኩ ያኖሯትን፣ ድል ብቻ ያስለመዷትን፣ ከጠላቶቿ አልቀው ከፍ ከፍ ያደረጓትን፣ ዳሯን እንደ እሳት በሚንቀለቀል ጀግንነት ያጠሯትን፣ መሐሏን የአንድነት ምንጭ መፍሰሻ አድርገው ያኖሯትን ኢትዮጵያን ጠብቋት፡፡ ለክብሯም በጽናት ቁሙላት፡፡
በታሪኳ ከዓለም ለተለየችው፣ የሰው ዘር መገኛ ለኾነችው፣ ሥርዓተ መንግሥቷን፣ ባሕሏን፣ እሴቷን፣ ሃይማኖቷን እና ጥንታዊ ታሪኳን ላልበረዘችው፣ ከእነ ክብሩ ለጠበቀችው፣ ከእነ ሥርዓቱ ላኖረችው፣ ለልጅ ልጅ ላስረከበችው፣ በእልፍ አዕላፍ መከራዎች ላለፈችው፣ በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ የማታንቀላፋ መብራት ለኾነችው፣ ለተጨነቁት ለደረሰችው፣ ተስፋ ላጡትም የተስፋ ጎህ ላሳየችው፣ ጠላቶች ያጠመዱባትን ወጥመድ ሁሉ በጀግንነት ላለፈችው፣ ምቀኞቿ ሊያስሯት የዘረጉትን ሰንሰለት በየዘመናቱ ለበጣጠሰችው ኢትዮጵያ ክብርን ስጧት፣ ስለ ግርማዋ እጅ ንሱላት፣ የታላቅነቷን ነገር መስክሩላት፡፡
ጠላቶች ሁሉ በቅናት የሚነሱባትን፣ በየዘመናቱ ጦር የሚያዘምቱባትን፣ በየወንዙ የሚማማሉባትን፣ በየሸንተረሩ የሚዶልቱባትን፣ በዘመናቸው ያልተፋቀሩት እርሷን ለመውጋት ሲሉ የሚፋቀሩባትን፣ ከሩቅም ከቅርብም ያሉት በምቀኝነት የሚነሱባትን ኢትዮጵያን ዳሯን እሳት፣ መሐሏን ገነት አድርጋችሁ ጠብቋት፡፡ ጥንት በጀግኖች ልጆቿ የተጠበቀችው፣ በጀግኖች ልጆቿ ጠላትን ሁሉ አሳፍራ የሰደደችው፣ ከእግሯም ስር የጠላችው፣ ክብሯን ሊያዋርድ መጥቶ ስለ ክብሯ እንዲመሰክር ያደረገችው ኢትዮጵያ ዛሬም ልጆቿ በአንድነት እንዲጠብቋት፣ በኅብረት እንዲያስከብሯት፣ በፍቅር እንዲያጸኗት፣ በሰላም ከፍ ከፍ እንዲያደርጓት ትፈልጋለችና፡፡
የኢትዮጵያ ልጆች በጠላቶቻቸው ላይ በአንድነት የሚያብሩ፣ በእናታቸው ቤት የሚፋቀሩ፣ በሰላም የሚኖሩ፣ ፍቅርን እና ኅብረትን የሚያስተምሩ እንጂ መለያየት፣ መጋጨት እና መፋጨት ግብራቸው አይደለም፡፡ ልጆቿ ሲጣሉባት ጠላቶቿ ይበረቱባታል፤ ጊዜ እስኪሰጣቸው ድረስ ሲያደቡባት የነበሩት ጠላቶቿ ያብሩባታል፤ ወዳጅ መስለው የኖሩት ጊዜ የሰጣቸው ሲመስላቸው ይነሱባታል፡፡ ለጠላቶቿ መድኃኒት የልጆቿ አንድነት እና ኅብረት ነው፡፡
የቀድሞው የኢትዮጵያ መሪ መንግሥቱ ኃይለማርያም ትግላችን በተሰኘው መጽሐፋቸው “በሰው ብዛት፣ በሃብት ምጣኔ እና በጦር ኀይሉ ጥንካሬ የተመካው በሌላው ላይ ለመስፋፋት እና ሌላውን ቅኝ አድርጎ ለመግዛት መውጋት እና መውረር እንደ በጎ ነገር፣ እንደ ጀግንነት፣ ታላቅነት እና አስተዋይነት እየተቆጠረ የወራሪው ሀገር መሪ ታላቁ እየተባለ፣ በሚሞካሽበት እና በሚወደስበት ዓለም ደካሞች በሰላም እና በነጻነት የመኖር ተስፋ አልነበራቸውም፡፡ የኀይለኞች እና የጉልበተኞች በነበረችው ዓለም ሕልውናቸውን አጥተው እንደ አንድ ሕዝብ ወይም ሀገር በሉዓላዊነት የመኖር ዕድላቸው አክትሞ ከጥፋት ተርፈው ዛሬ በአንድ ነጻ ሕዝብነት እና ሀገርነት ከሚታወቁት ሁሉ የመወረር እና የቅኝ ተገዢነት እጣ ሳይገጥማቸው ያመለጡ በአንድ እጅ እጣት የሚቆጠሩ ጀግኖች እና አይበገሬዎች ናቸው፡፡ በአንድ እጅ እጣት ከሚቆጠሩ ሀገራት መካከል ደግሞ ኢትዮጵያ አንደኛዋ ናት” ብለው ጽፈዋል፡፡
ኢትዮጵያ በዓለም ፊት በልጆቿ ጀግንነት፣ አይበገሬነት፣ አንድነት እና ብርታት በነጻነት የኖረች ሀገር ናት፡፡ በተለያዩ ዘመናት ነጻነቷን የሚጋፉ ጠላቶች ገጥመዋታል፤ ጦር መዝዘውባታል፤ ሠራዊት አሰማርተውባታል፡፡ ነገር ግን ለአንዳቸውም ሳትንበረከክ እና ሳትበገር በነጻነት ኖራለች፣ በጀግንነት ሉዓላዊነቷን አስከብራለች፡፡ ጀግና መውለድ በማይነጥፈው የማሕፀኗ ፍሬዎች በጀግንነት ተጠብቃ ትኖራለች፡፡
የቀደሞው መሪ መንግሥቱ ኃይለ ማርያም በዓለም ላይ በመቶዎች የሚቆጠሩ ወራሪ እና ተወራሪ ሀገራትን መቁጠር ይቻላል ይላሉ፡፡ በአንድ ዘመን ወራሪ የነበሩ ሀገራት በሌላ ዘመን ተወራሪ ኾነው ሉዓላዊነታቸውን ይነጠቃሉ፣ በቅኝ ግዛት የያዟቸውን ሀገራት ብቻ ሳይኾን መነሻ ሀገራቸውን ያጣሉ፡፡ ኢትዮጵያ ግን ከእነዚህ ሁሉ የተለየች ናት፡፡ በዘመናት ውስጥ ሉዓላዊነቷን እና ነጻነቷን የነጠቃት አንድም ሀገር የለም፡፡ ለዚህ ያበቃት ደግሞ በቅብብሎሽ የጠበቋት ልጆቿ ጥንካሬ፣ የነጻነት ፍቅር እና አንድነት ነው፡፡
ኢትዮጵያ በጀግኖቿ የአርበኝነት ተጋድሎዋ በነጻነት መኖር ብቻ ሳይኾን በዓለም የታፈረች እና የተከበረች ናት ይላሉ መንግሥቱ ኃይለማርያም፡፡ “የዚህች የጥንታዊነት አይበገሬ ነጻ እና አኩሪ ሀገር ባለቤት ለመኾን የቻልነው በአንድነታችን እና በኅብረታችን ነው፡፡ ሀገራችንን የየዘመኑ ተከታታይ ትውልዶች በፈረቃ እና ባላቋረጠ መሪር መስዋዕትነት ያቆዩንን ሀገር እና ያወረሱንን አኩሪ የታሪክ ቅርስ እኛም በፈንታችን ለተከታዩ ትውልድ እናወርሳለን ወይስ አናፈርሳለን ብሎ የዛሬው ትውልድ ራሱን መጠየቅ አለበት” ብለው ጽፈዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን ጀግኖች ከአያሌ መከራዎች እና ፈተናዎች ጠብቀው ኢትዮጵያን በነጻነት ያኖሯት ስለ ሀገራቸው ያላቸው ፍቅር ቀስቅሷቸው እና በጽናት አቁሟቸው ነው፡፡ ጀግኖች የተፋለሙት ለአንዲት ኢትዮጵያ ኀያልነት እና ክብር ነው፡፡ የዛሬ ልጆችም ለአንዲት ኢትዮጵያ ነጻነት እና ክብር በጽናት መቆም እና በአንድነት መኖር አለባቸው፡፡
ነጋድራስ ገብረ ሕይዎት ባይከዳኝ አጤ ምኒልክ እና ኢትዮጵያ በተሰኘው መጽሐፋቸው “ የእኛ የኢትዮጵያውያን ያለፈው ታሪክ እጅግ ያሳዝናል፡፡ ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት ጀምሮ እስካሁን ድረስ ፍጹም የኾነ ሰላም አግኝተን አናውቅም፡፡ የተወደደች ሀገራችን ዘወትር በጠላቶች ተከባ ስትኖር ነበረች፡፡ ትኖራለችም፡፡ ነገር ግን በእግዚአብሔር ቸርነት የውጭ ጠላት ከዚህ በፊት አላወረደንም፡፡ አንድ ስንኾንም ምንም የሚደፍረን እንደሌለ ታሪክ ይመሰክራል፡፡ ዘወትር በስምምነት እና በፍቅር አድረን ብንኾን እስከዛሬ ድረስ ብዙውን ትልልቅ ነገር መፈጸም እንችል እንደነበር ጥርጥር የለውም” በማለት ጽፈዋል፡፡ አንድነት የኢትዮጵያ የኀይል ምስጢር እና ምንጭ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን አንድ ሲኾኑ የትኛውም ጠላት ያከብራቸዋልና አይዝትባቸውም፤ እሳት ይዞ አይዞራቸውም፡፡
“እርስ በእርሳችን መጠራጠርንም አልተውንም፡፡ ሕዝቦቹም ሁሉ እርስ በእርሳቸው በፍቅር ተቃቅፈው ስለልማታቸው ባንድነት ኾነው ሲደክሙ እኛ አንድ ዘር እና ወንድማማቾች መኾናችን አልተገለጸልንም፡፡ እርስ በእርሳችን መፋጀትም እስከዛሬ ድረስ ጀግንነት ይመስለናል” ብለው ጽፈዋል ነጋድራስ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ፡፡ እርስ በእርስ መጋጨት፣ አንድነትን ማላላት፣ የውስጥን ሰላም ማጣት ሀገር እንዳታድግ፣ ጠላቶች እንዲበረቱ፣ ወገኖች እንዲጎሳቆሉ ያደርጋል፡፡ የዛሬው ትውልድ የትናንት ታሪኩን ማወቅ፣ ዛሬ ላይ ታሪክ መሥራት፣ በመስዋዕት የጸናችውን፣ በአንድነት የተጠበበችውን ሀገር በአንድነት እና በፍቅር ጠብቆ ለነገ ማሻገር አለበት፡፡
ሐሪ አትክንስ የኢትዮጵያ ታሪክ በተሰኘው መጽሐፋቸው የኢትዮጵያ ሕዝብ የቆዬ የነጻነት እና ፍቅር ያለው መኾኑን ጽፈዋል፡፡ በአንድነት የመጣው የዓድዋ ድል ደግሞ የኢትዮጵያ ሕዝብ የነጻነት ፍቅር አርማ ነው ብለዋል፡፡ ታላቁ የዓድዋ ድል ኢትዮጵያን በዓለም ካርታ ላይ አጉልቷል፡፡ የዓድዋ ድል ኢትዮጵያን በዓለም ፊት ከማጉላቱም በላይ እነኾ በቀላሉ ለቅኝ ግዛት የማትበገር አፍሪካዊት ሀገር አድርጓታል ይላሉ፡፡ ይህን ያመጣው የውስጥ አንድነት እና ፍቅር መበርታት፣ ለነጻነት ቀናኢ መኾን ነው፡፡
በሪሁን ከበደ የአፄ ኃይለ ሥላሴ ታሪክ በተሰኘው መጽሐፋቸው ኢትዮጵያ የረጅም ዘመን የመንግሥት እና የነጻነት ባለቤት ኾና ለመቆየት የቻለችው በነገሥታቶቿ እና በሕዝቧ አንድነት እና ብርታት ነው፡፡ አባቶች ደማቸውን እያፈሰሱ፣ አጥንታቸውን እየከሰከሱ፣ ከመጣ ጠላት ጋር እየተዋጉ ነው ሀገር ጠብቀው ያቆዩት፡፡ አንዳንድ ሀገሮች እንደ ኢትዮጵያ የረጅም ዘመን መንግሥት እና ታሪክ ያላቸው መኾኑ ቢታወቅም ከመካከሉ ላይ በበዓድ እየተገዙ ለብዙ ጊዜ መንግሥታቸው እየፈረሰ የፈረሰውን መንግሥት እንደገና እያቋቋሙ ሲወድቁ ሲነሱ ኖረዋል፡፡ ኢትዮጵያ ግን መንግሥቷን ከመሠረተችበት ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ መንግሥቷ ፈርሶ ነጻነቷ ተደምስሶ አያውቅም ይላሉ፡፡
ኢትዮጵያ ኀይለኛ እና ገናና መንግሥት ገንብታ አንድነቷን አጽንታ ታፍራ እና ተከብራ ስትኖር ኖራለች፡፡ ዛሬ ደግሞ ለዚህ ዘመን ትውልድ አደራ ተሰጥታለች፡፡ እንደቀደሞዎቹ ሁሉ ከዛሬ ልጆቿም ፍቅርን አንድነትን ትሻለች፡፡ እንዲጠብቋት፣ እንዲያስከብሯት፣ ሰላሟን እንዲጠብቁላት ትፈልጋለች፡፡ ልጆቿ የእርስ በእርስ ጠብ እና ጥላቸውን ትተው፣ ለአንዲት ሀገራቸው፣ ለክብራቸው እና ለሠንደቅ ዓላማቸው ሲሉ በአንድነት እና በፍቅር መኖር አለባቸው፡፡
እርስ በእርስ መጋጨት፣ ውሳጣዊ ሰላም ማጣት ለዚህ ዘመን የሚመጥን፣ ከኢትዮጵያ ክብር እና ታሪክ ጋርም የማይሄድ ነው፡፡ ለኢትዮጵያ የሚመጥናት፣ ለክብሯም የሚኾናት አንድነት፣ ኅብረት፣ ሰላም እና ፍቅር ነው፡፡ ስለ ኢትዮጵያ ስትሉ በፍቅር ኑሩ፣ በአንድነት ተባበሩ፣ አንድነታችሁ ኢትዮጵያን ይጠብቃታል፤ ኢትዮጵያን ያስከብራታል፣ ያሳድጋታልና፡፡