አንድነታችን ጥያቄ ውስጥ እንዳይገባ ብለን በትዕግስት ስናልፍ ቆይተናል። ይህ ቡድን ከጥፋት ተግባሩ ሊገታ ባለመቻሉ ህጋዊ እርምጃ መውሰድ እንጀምራለን።በዚህ ሂደት ላይ ለሚፈጠረው ማንኛውም ጥፋት ተጠያቂው የዚህ ቡድን አመራር እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል- ጊዜያዊ አስተዳደሩ
ከትግራይ ታጣቂው ኃይልና የቀድሞ መኮንኖች ጋር መስጥሯል፣ ከኢሳያስ አፉወርቂ ጋር የጎንዮሽ ግንኙነት ጀምሯል በሚል መረጃና ማስረጃ የሚቀርብበት በዶክተር ደብረጽዮን የሚመራው የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግንባር ትህነግ አንድ ክፋይ እነ አቶ ጌታቸውንና በጉባዔ ያልተገኙ ያላቸውን በሙሉ አንስቶ አዲስ ሹመት መስጠቱን አስታውቋል። የፊደራል መንግስትም ይሁን የአቶ ጌታቸው ወገን ይህ እስከታተመ ድረስ ያለው ነገር የለም።
በሚሊዮን የሚቆጠር ሰው ካስጨረሱና ትግራይ ወድማ የሻዕቢያ መፈንጫ እንድትሆን ካደረጉ በሁዋላ ሲሸነፉ የሰላም ስምምነት የፈረሙት የትህነግ አመራሮች ዳግም ለስልጣን ሲሉ እዚህ ውዝግብ ውስጥ መግባታቸው አስገራሚ እንደሆነ ሲገለስ ስንብቷል። በጦርነቱ ወቅት ሲደግፏቸው የነበሩ ሳይቀሩ ክፉኛ ተቃወዋቸዋል።
“ደብረጽዮን የጦርነት አንቴና ነው። አንቴናው የዕልቂት ሞገድ ነው የሚስበው” በሚል ክፉኛ የዘለፋቸው የርዕዮት አዘጋጅ ዶክተር ደብረርጽዮን ይህ ሁሉ ሰው ሞተ ጀኖኖሳይድ ተፈጸመ የሚባለው ፕሮፓጋንዳ ነው የሚል አቋም ማራመዳቸውም እጅግ እንዲወገዙ አድርጓቸዋል። ይህ ንግግራቸው “እንዳንገነጠል እንቅፋት የሚሆን የለፋንበትን የጄኖሳይድ ጉዳይ አፈር የከተተ ነው” በሚል ሰፊ ተቃውሞ አስነስቶባቸዋል።
በአቶ ጌታቸው ረዳ የሚመሩ የህወሓት ማእከላይ ኮሚቴ አባላት እና ሌሎች በቅርቡ አካሂደውት በነበረ “ህወሓት ማዳን” የተሰኘ ስብሰባ፥ ጉባኤ ያደረገው ህወሓት በሕገወጥነት ፈርጀው በቅርቡ ሌላ ጉባኤ እንደሚያደርጉ ገልፀው እንደነበረ ይታወሳል።
ይህ እየሆነ ባለበት ወቅት ነው ከዛሬ ጀምሮ አቶ ጌታቸው ረዳን ጨምሮ ሁሉም በጊዚያዊ አስተዳደሩ ስር የሚገኙ በጉባኤ ያልተሳተፉ የስራ ሃላፊዎች በጉባኤ በተሳተፉ ሹማምንት መቀየሩን በዶ/ር ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል የሚመራው ትህነግ መወሰኑን በትግርኛ ባሰራጨው መግለጫ ይፋ አድርጓል።
” የጊዜያዊ አስተዳደሩ መሪ አቶ ጌታቸው ረዳ ትህነግ ከሰጣቸው የስራ ሃላፊነት ተነስተዋል እንዴትና በማን እንደሚተኩ ከፌደራል መንግስት እየተነጋገርኩ ነው ” ሲል በዶ/ር ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል የሚመራው ትህነግ ማስታወቁን የትግርኛ ደብዳቤውን የተረጎሙ ወገኖች አስታውቀዋል። ንግግሩ ግን ከየትኛው የፌዴራል መንግሥት አካል ጋር እንደሆነ በግልጽ ያለው ነገር የለም።
በዶ/ር ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል የሚመራ ትህነግ ባሰራጨው መግለጫ፣ በጊዚያዊ አስተዳደሩ ካቢኔዎች ፣ ቢሮዎች ፣ ኤጀንሲዎች ፣ ኮሚሽኖች የዞን አስተዳደሮች የሚገኙ በጉባኤ ያልተሳተፉ የስራ ሃላፊዎች በማንሳት በጉባኤ በተሳተፉ አባላቱ ሙሉ በሙሉ መተካቱን አስታውቋል።
ደብረጽዮን የሚመሩት ትህነግ አዲሱን ምደባ አስመልክቶ ባወጣው ዝርዝር መሰረት አቶ በየነ መክሩ፣ ፕሮፌሰር ክንደያ ገ/ሂወት፣ ዶ/ር ሓጎስ ጎዲፋይ እና ወ/ሮ አልማዝ ገ/ፃዲቕ ከጊዚያው አስተዳደሩ ካቢኔ ተነስተዋል። ከስር ዝርዝራቸው የተቀመጠው ደግሞ ተሹመዋል።
- ዶ/ር አብራሃም ተኸስተ
- አቶ አማኒኤል አሰፋ
- ዶ/ር ፍስሃ ሃብተፅዮን
- አቶ ተወልደ ገ/ፃድቃን
- ወ/ሮ ብርኽቲ ገ/መድህን
- አቶ ይትባረክ አምሃ
- ዶ/ር ፀጋይ ብርሃነ መተካቱ ገልጿል።
- አቶ ርስቁ አለማው
- አቶ ሰለሙን መዓሾ
- አቶ ሺሻይ መረሳ
- አቶ ሃፍቱ ኪሮስ ከዞን ዋና አስተዳዳሪነት በማንሳት
- በአቶ ተኽላይ ገ/መድህን
- በአቶ ወልደኣብራሃ ገ/ፃዲቕ
- በአቶ ሺሻይ ግርማይ
- በአቶ ፍስሃ ሃይላይ
- በአቶ ሃይላይ ኣረጋዊ
- በዶ/ር አብራሃም ሓጎስ ተተክተዋል ብሏል።
ከዚህ በተጨማሪ አቶ ረዳኢ ሓለፎም ፣ ወ/ሮ ሰብለ ካሕሳይ ፣አቶ ነጋ አሰፋ ፣ ዶ/ር ገ/ሂወት ገ/ሄር ከኤጀንሲ እና የኮሚሽን የስራ ሃላፊነት ወርደዋል ያለው በዶ/ር ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል የሚመራ ህወሓት በእነ ማን እንደተተኩ ያለው ነገር የለም። ይህ ዘገባ አስከተጠናቀረበት ቀንና ሰዓት ድረስ በትህነግ ምክትል ሊቀመንበር ጌታቸው ረዳ የሚመራ የትህነግ አንዱ ክፋይ መጨረሻ ላይ ” አንድነታችን ጥያቄ ውስጥ እንዳይገባ ብለን በትዕግስት ስናልፍ ቆይተናል። ይህ ቡድን ከጥፋት ተግባሩ ሊገታ ባለመቻሉ ህጋዊ እርምጃ መውሰድ እንጀምራለን።በዚህ ሂደት ላይ ለሚፈጠረው ማንኛውም ጥፋት ተጠያቂው የዚህ ቡድን አመራር እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል” ብሏል።