” የህዝባዊ በዓላት የፖለቲካ መድረክ ሊሆን አይገባም ” ሲል የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ ፓርቲ ገለጸ። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በተለይ ” ኢሬቻ ” በዓልን በማክበር ሒደት በመንግሥት መዋቅሮች እና በመንግሥታዊ ኃላፊነት ቦታ ላይ የተቀመጡ ባለሥልጣናት ባሕሉ ካለው ሕዝባዊ እሴት ባፈነገጠ መልኩ ባሕሉን ከሕዝቡ ባለቤትነት ነጥቀው ፖለቲከኞቹ ዋነኛ አጋፋሪ እንደሆኑበት አመልክቷል። ይህ አካሄድ በሌሎች ዘንድ የመገለል እና የስጋት ስሜት ይፈጥራል ሲል ፓርቲው አመልክቷል።
” ገዢው ፓርቲም በዚህ መልኩ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት በሚመስል መልኩ መንቀሳቀሱ ተገቢ አይደለም ብለን እናምናለን ” ያለው ኢዜማ፣ በተለይ ለባሕሉ ተብሎ በተለያዩ አካባቢዎች ከተቋማት እና ከንግዱ ማኅበረሠብ በድጋፍ ስም በመንግስት መስሪያ ቤቶች ደብዳቤ የንግድ ማኅበረሠቡን በሚያስጨንቅ እና ከአቅም በላይ የሆነ ከፍተኛ አስገዳጅ የገንዘብ መዋጮ የመጠየቅ እንቅስቃሴ እንዳለ ጠቁሟል። አክሎም ይህ ተግባር ማኅበረሠቡን ከፍተኛ ምሬት ውስጥ በመክተት ባሕሉን በስጋት እንዲመለከተው እያደረገ ይገኛል ” ብሏል።
” የባሕሉ ባለቤት የሆነው ሕዝብ ተቋማትን እና ግለሰቦችን አስጨንቃችሁ መዋጮ በመሰብሰብ በዓሉን አድምቁልኝ አይልም ፤ ይህንንም ሕገወጥ ተግባር የሚጠየፈው መሆኑን አንዳች ጥርጥር የለንም ” ሲል በዓሉን ተንተርሶ የሚደረገውን እንቅስቃሴ ኢዜማ አውግዟል። ባህሉን ለህዝብ መልሱልን ያለበት ዋና ምክንያትም ዘርዝሯል።
” የየትኛውንም ማኅበረሠብ ባሕላዊም ሆነ ሃይማኖታዊ በዓል ለፖለቲካ ፍጆታ ማዋል ባሕሉን መበረዝ እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል ” ያለው ፓርቲው ይህን መሰል የአደባባይ ክብረ በዓላት ለየትኛውም አይነት የፖለቲካ አጀንዳ ማራመጃነት መጠቀምን ፍፁም እንደሚያወግዝ አስታውቋል።
በንግዱ ማኅበረሠብ ላይ እየተደረገ ያለውን ተጠያቂነት የሌለበት ሕገወጥ ጫናን ጨምሮ ሌሎች አስገዳጅ ድርጊቶችን መንግሥት በቶሎ እንዲያቆም ፓርቲው አሳስቧል። መንግሥት ባሕሉን ጠንቅቆ ለሚያውቀው ማኅበረሠብ እንዲመልስና እንደ መንግስት የሚጠበቅበትን መሠረታዊ ኃላፊነቶቹን ብቻ በቅጡ እንዲወጣም ጠይቋል።
በቴሌግራም ይከተሉን https://t.me/+f_kxmaPjD-9jYTdk