የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ 11 ፓርቲዎችን በጊዜያዊነት አገደ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በጠቅላላ ጉባዔ፣ በኦዲት እና በሴት አባላት አማካኝነት ከሚገኝ የገንዘብ ድጋፍ ጋር በተያያዘ 11 የፖለቲካ ፓርቲዎችን በጊዜያዊነት አግዷል፡፡
ቦርዱ ለኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት እንዳስታወቀው የታገዱት ፓርቲዎች የኦሮሞ ነጻነት ንቅናቄ፣ አንድ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ የጌዲኦ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት፣ የሐረሪ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት፣ የገዳ ሥርዓት ለኦሮሞ ነጻነት ፓርቲ፣ የዎላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ፣ አዲስ ትውልድ ፓርቲ፣ የጋምቤላ ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ፣ የጋምቤላ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ፣ የኢትዮጵያ ዴሞክራቲክ ኅብረት እና አገው ለፍትሕና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ናቸው።
በፓርቲዎቹ ላይ የተሰጠው የዕግድ ውሳኔ ቦርዱ የተለየ ውሳኔ እስከሚሰጥ ድረስ ለጊዜው ከማንኛውም ሕጋዊ እንቅስቃሴ ታቅበው እንዲቆዩ የሚያደርግ ነው።
በመሆኑም ቦርዱ የሰጠውን የዕግድ ውሳኔ እስከሚያነሳ ድረስ ከላይ የተገለጹት ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤቱ በሚያዘጋጃቸው ጉባዔዎች ላይ ሊገኙ፣ ሊመርጡም ሆነ ሊመረጡ እንዲሁም በኮሚቴ አባልነት ሊያገለግሉ አይችሉም ተብሏል።
የጋራ ምክር ቤቱ የዕግድ ውሳኔ የተላለፈባቸውን ፓርቲዎች ከማንኛውም የምክር ቤቱ ሥራዎች እና እንቅስቃሴዎች እንዳይካፈሉ እንዲያደርግም ቦርዱ አሳስቧል።
ፕሬዚዳንት ታዬ ካፍ የኢትዮጵያን የአፍሪካ ዋንጫ የማስተናገድ ጥያቄ ተቀብሎ እንዲያጸድቅ ጥሪ አቀረቡ
የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) የኢትዮጵያን የ2029 የአፍሪካ ዋንጫ የማስተናገድ ጥያቄ እንዲቀበል እና እንዲያጸድቅ የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ ጥሪ አቀረቡ።
በአዲስ አበባ እየተካሔደ ባለው 46ኛው የካፍ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ፕሬዚዳንት ታዬ÷ አፍሪካውያን ቤታችሁ ወደ ሆነችው ኢትዮጵያ እንኳን ደህና መጣችሁ ብለዋል።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ እግር ኳስ ትልቅ አሻራ እንዳላትና በፈረንጆቹ 1957 ካፍ ሲመሰረት መስራች ከነበሩ ሀገራት መካከል አንዷ መሆኗን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ እግር ኳስ ያላትን ታሪካዊ ድርሻ ከግምት በማስገባትበፈረንጆቹ 2029 የሚካሄደውን የአፍሪካ ዋንጫ ለማዘጋጀት ጥያቄ ማቅረቧን ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫን ለማስተናገድ ስታዲየሞች እየገነባች መሆኑን ጠቁመው ÷ያሉት ላይም ማሻሻያ እያደረገች እንደምትገኝ አመልክተዋል።
ካፍ የኢትዮጵያን የአፍሪካ ዋንጫ የማስተናገድ ጥያቄ ተቀብሎ እንዲያጸድቅ ፕሬዚዳንት ታዬ መጠየቃቸውንም ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫ አስተናጋጅነት ጥያቄ በካፍ የአሰራር ስርዓት ይታያል – የካፍ ፕሬዚዳንት ፓትሪስ ሞትሴፔ
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በይፋ ያቀረቡትን ጥያቄ ተከትሎ የኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫ አስተናጋጅነት ጥያቄ በካፍ የአሰራር ስርዓት እንደሚታይ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ፕሬዚዳንት ፓትሪስ ሞትሴፔ ተናግረዋል፡፡ የካፍ መስራች አባል ሀገር የሆነችው ኢትዮጵያ በአፍሪካ እግር ኳስ ውስጥ ታሪካዊ ሚና እንዳላትም አውስተዋል፡፡
ለአፍሪካ ነጻነት ትልቅ አቅም የነበረችው ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫን ለማስተናገድ በትክክለኛ ጊዜ ለካፍ ጥያቄ ማቅረቧንም አንስተዋል፡፡
“ኢትዮጵያውያን ለእግር ኳስ ያላቸውን ከፍ ያለ ስሜት እረዳለሁ” ያሉት ፕሬዚዳንቱ እግር ኳስን ህዝባዊ አንድነትን ለመፍጠር መጠቀም እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባስጎበኟቸው በግንባታ ላይ ባሉ ስታዲየሞች እና የስፖርት መሰረተ ልማቶችም መደሰታቸውን ጠቁመዋል፡፡ የኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫ የማስተናገድ ጥያቄ በካፍ የአሠራር ሂደት እንደሚታይም ማረጋገጣቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የካፍ ጉባዔ በኢትዮጵያ መካሄዱ ለእግር ኳሱ መነቃቃት ይፈጥራል – ም/ጠ/ሚ ተመስገን ጥሩነህ
46ኛው የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ በኢትዮጵያ መካሄዱ ለሀገራችን እግር ኳስ መነቃቃት ይፈጥራል ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ፡፡
46ኛው የካፍ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ ዛሬ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።
አቶ ተመስገን በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት÷ 46ኛው የካፍ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ በኢትዮጵያ መካሄዱ ለሀገራችን እግር ኳስ መነቃቃትን ይፈጥራል ብለዋል፡፡
አፍሪካን በዓለም ዐደባባይ ያደመቁ የእግር ኳስ ከዋክብቶችም ለጉባዔው በአዲስ አበባ እንደሚገኙ ጠቁመው÷ ጉባዔው ስኬታማ እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡
በጉባዔው የካፍ ፕሬዚዳንት ፓትሪስ ሞትሴፔ እና የካፍ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት፣ የዓለም አቀፉ የእግር ማኅበር (ፊፋ) ፕሬዚዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ እና የፊፋ ዋና ፀሐፊ ማትያስ ግራፍስትሮም፣ የካፍ አባል ሀገራት እግር ኳስ ፌዴሬሽኖች እና የቀጣናዊ እግር ኳስ ማኅበራት ፕሬዚዳንቶች እንዲሁም ሌሎች የስፖርቱ ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ነው።