ብልጽግና የተመረጡ አባላቱን በአድዋ ሙዚየም እያሰለጠነ ነው። በዚሁ ሶስተኛ ዙር በተባለ ስልጠና አባላቱ በፓርቲው መሪ አሳቦች፣ ንድፎች፣ ራዕይ፣ የውጭ ግንኙነት፣ የኮሪዶር ልማት፣ አጠቃላይ አገራዊና አህጉራዊ ጉዳይ ፓርቲው የሚያራምደውን አቋም አባላቱ እምን ደረጃ እንደሚረዱት ይመዝናል። በዚሁ መነሻ ሃያ ሰባት የሚሆኑ መመዘኛ የውይይትና የማብራሪያ አንቀጾች ተቀምጠዋል። ስልጠናው የምርጫ መንደርደሪያ ነው ተብሏል።
ፓርቲው የአብዮታዊ ዴሞክራሲ አሳብ ሰለባዎች የበዙበት መሆኑ ስለሚጠቀስ ይሁን በሌላ ምክንያት በአብዮታዊ ዲሞክራሲና የመደመር እሳቤ መካከል ያለውን መሰረታስዊ ልዩነት ማወቅ አንዱ የምዘና ነጥብ እንደሆነ ተሰምቷል። የተለያዩ ሪፎርሞችን ማካሄድ ያስፈለገበት ምክንያትና የተገኘውን ለውጥ፣ የህዳሴ ግድብ መተናቀቅና የተገኘው ኢኮኖሚያዊና ዓላማ ዓቀፋዊ የዲፕሎማሲ አግባብ ወዘተ የመሳሰሉትን ጉዳዮች ማብራራት፣ ማስረዳት፣ ልዩነትን መዳሰስ፣ መዘርዘርና ለጥያቄ መመለስ ላይ ያተኮረው ስልጠና አባላቱን ለማብቃትና በመረጃ ለማስታጠቅ ታስቦ እንደሆነ ነው የተሰማው።
“አገልጋይነት ስነ-ምግባራዊ አመራር የሚያደርገው ምንድነው?አገልጋይነት ከሌሎች አመራር ዘዴዎች የተለየ የሚያደርገው ምንድነው?አገልጋይ መሪነት ለብልፅግና ተመራጭ የሚሆነው ለምንድነው?” የሚለው ፓርቲው ሊያሻሽላቸው ዕለት ዕለት ቃል የሚገባባቸውና ህዝብን ያስመረሩት ጉዳዮች የምዘና መወያያ ሰበዝ ጉዳዮች ናቸው።
አዲስ አበባን የቱሪስትና የስበት ማዕከል ለማድረግ እየተሰራ ያለውን የኮሪዶር ልማት ለኑሮ ውድነት ጋር በማወዳደር ለምን ቅድሚያ እንደተሰጠው የፓርቲው አባላት ምን ያህል ግንዛቤ እንዳላቸው በምሰናው ውስጥ ተካቷል።
ፓርቲው ስኬቴ በሚላቸው ጉዳዮችና በምርጫ ዘመቻ ህዝብ ዘንድ ይዟቸው የሚቀርባቸውን አንኳር ጉዳዮች ያካተቱት ነጥቦች ከስር ያሉት ናቸው
- አገልጋይነት ስነ-ምግባራዊ አመራር የሚያደርገው ምንድነው?አገልጋይነት ከሌሎች አመራር ዘዴዎች የተለየ የሚያደርገው ምንድነው?አገልጋይ መሪነት ለብልፅግና ተመራጭ የሚሆነው ለምንድነው?
- የብልፅግና ማዕከልነት ምንድነው? ከፖለቲካ፣ ከኢኮኖሚ እና ከውጭ ጉዳይ አንጻር የሀሳብ መነሻዎችን እና ተግባራዊ ምሳሌዎችን በመጥቀስ አስረዱ? ከትርክት አንጻር በመዳሰስ አስረዱ?
- አንድ ሰው ዘርፈ ብዙ ሀገራዊ ችግሮች እያሉ ወይም የዳቦ ጥያቄ ሳይመለስ ለምን የኮሪደር ልማት ትሰራላቹ ቢል ምላሻችን ምንድነው?የኮሪደር ልማት መፍጠር ለምንፈልገው ኢኮኖሚ እና ማሳካት ለምንፈልገው ማህበራዊ ግብ ያለው ዋጋ ምንድነው?
- የመደመር መሰረታዊ እሳቤ ከብሔራዊነት ትርክት እና ከህልማችን ጋር ያለው ትስስር ምንድነው?የብሔራዊነት ትርክት እና የሀገራዊ ህልም ትስስር ምንድነው?
- ህልውና መር አካሄድን ከሀገራችን ታሪክ ጋር በማያያዝ አስረዱ? ያመጣው ውጤት እና የፈጠረው ውድቀት ምንድነው?
- ብልፅግና የእይታ እና የምናብ ለውጥ ነው፡፡ ይህንን የእይታ ለውጥ ከታሪክ ምልከታ እና እጣፈንታችን ከመወሰን አንጻር አስረዱ?
- የተለያዩ የተሰሩ ስራዎችና ኢንሼቲቮች መነሻ ህልም እና የሚፈጥሩት አለም እና አቅም ምንድናቸው?
- ሳይንስ ሙዚየም፣ አብርሆት፣ ገበታ ፕሮጀክቶች ከፍ ያለ ምናብ እና አርቆ እይታ ውጤቶች ናቸው ሲባል ምን ማለት ነው? ህልማችንን ልዕልና መር የሚያደርገው ምንድነው? የህልማችን መዳረሻ እና ተግባራዊ ምሳሌዎችን በማገናኘት አስረዱ?
- የፖለቲካ ገበያ የጋራ ህልማችን እንቅፍት ነው ሲባል ምን ለማለት ነው?
- በነባራዊና አለም አቀፋዊ ትንታኔያችን ውስጥ ብዝሀ ቀውስ፣ የመረብ ዘመን እና ድህረ-እውነት የሚሉ ጉዳዮችን ደጋግመን እንገልጻለን፡፡ እነዚህ ጉዳዮች በማያያዝ እና በማሰናሰል ነባራዊ አለም አቀፍ ሁኔታ ምልከታችንን አስረዱ? እነዚህ እውነታዎች ከሀገራችን ፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ እና ዲፕሎማሲ አንጻር እየፈጠሩ ያሉትን እና የሚኖረውን አወንታዊ እና አሉታዊ ተጽዕኖ አስረዱ?
- የስነ-ምግባር አስተውሎት/ኢንተለጀንስ ለአመራሩ ቁልፍ የሚያደርገው ምንድነው? ብልፅግናን ለማረጋገጥ እና ለመደመር ስነ-ምግባር አስፈላጊ ነው ቢባል ምን ለማለት ነው?
- የለውጥ ዋና ዋና ስኬት ከሆኑት ውስጥ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ ማህበራዊ እና በውጭ ግንኙነት ውጤቶች አንዳንድ በመዘርዘር ከእነዚህ ውጤቶች ጀርባ ያለውን የሀሳብ መነሻ እና የአካሄድና የመንገድ ልዩነት አስረዱ?
- የህግ ማስከበር ተቋማት ሪፎርም በተቋማት ውስጥ እና በሀገር ግንባታ ውስጥ የፈጠረው ለውጥ እና ያመጣውና የሚያመጣው ተጽዕኖ ምንድነው?
- ተቋማት ግንባታ የለውጡ መሰረታዊና ቁልፍ ጉዳይ የሆነው ለምንድነው? አመራሩ በተቋማት ግንባታ ውስጥ የሚጫወተው ሚና ምንድነው?
- የፖለቲካና የኢኮኖሚ ሪፎርም ስራዎቻችን ከህልማችን መዳረሻ እና ስኬት ጋር በማያያዝ አስረዱ?
- ህልውና መር እይታ ከችግር የማያሻግር የተባለበት ምክንያት ምንድነው?
- የሀገራዊ ህልማችን ቁልፍ መዳረሻዎች ምንድናቸው? በዝርዝር አስረዱ?ህልምን ለማሳካት እንቅፋቶች ምንድናቸው? ህልምን ለማሳካት ከአመራሩ ምን ይጠበቃል?
- የፖለቲካ ሪፎርም ማድረግ ለምን አስፈለገ? የፖለቲካ ሪፎርም ገፊ ምክንያቶች፡-የፖለቲካ ሪፎርም ማድረግ ያስፈለገበት ምክንያት፡-የሪፎርሙ መሰረቶች ምንድናቸው? ውጤታማነቱስ እንዴት ይመዘናል? የፖለቲካ ሪፎርም ውጤታማነት መመዘኛዎች፡-የመሃል ፖለቲካን ባህሪያትና ፋይዳ ተረድቶ የመምራት አስፈላጊነትን አስረዱ? የጠንካራ ፓርቲ ግባችንን ማሳካት ለህልማችን እውን መሆን ያለውን ፋይዳ አስረዱ?የጠንካራ ፓርቲ ግባችንን ማሳካት ለህልማችን እውን መሆን ያለውን ፋይዳ፡-ፓርቲያችንን ለማጠናከር ከአመራሩ ምን ይጠበቃል?
- የኢኮኖሚ ሪፎርም ማድረግ ለምን አስፈለገ? የሪፎርሙ አንጓዎች ምንድናቸው? ምን አይነት ውጤትስ ያመጣል?
- አብዮታዊ ዲሞክራሲ እና መደመር ቁልፍ ልዩነቶችን አስረዱ? በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ እና በውጪ ግንኙነት የምንከተላቸው መንገዶች ከአብዮታዊ ዲሞክራሲ ጋር ያለውን ልዩነት በዝርዝር አስረዱ?
- የሰላም እጦት ቁልፍ ምክንያቶች ምንድናቸው?የብልጽግና የሰላም ግንባታ ግብ ምንድነው? ሰላምን ለማምጣት የምንከተለው አካሄድ ከነባሩና ከተለመደው አካሄድ ጋር ያለው ልዩነት ምንድነው? ሰላምን ለማረጋገጥ ያደረግናቸው ጥረቶች እና የመጡት ውጤቶች ምንድናቸው? የገጠሙን ተግዳሮቶችስ?
- ከለውጡ በኃላ ብዙ ኢንሼቲቮች ተጀምረው ውጤት አምጥተዋል፡፡ ከእነዚህ ኢንሼቲቮች ጀርባ ያለው ሀሳብ፣ የተሰሩበት መንገድ፣ የሚያመጡት ውጤት ምን ለመድረስ እና ለመፍጠር በማመን ነው? ከሀሳቦቻችን ጋር በማስተሳሰር አስረዱ? እየፈጠሩት ያለው የአመለካከት እና የባህል ለውጥ አስረዱ?
- የምግብ ሉዓላዊነት የብልጽግና ቁልፍ አጀንዳ ሆነ? የምግብ ሉዓላዊነት ግቦቻችን ምንድናቸው? የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ እየተሰሩ ያሉ ዋና ዋና ስራዎች ምንድናቸው? ያመጡት ውጤትስ?
- የህዳሴው ግድብ መጠናቀቅ ያለውን ቁልፍ ሀገራዊ ፋይዳ አብራሩ? ከኢኮኖሚ፣ ከፖለቲካ፣ ከተቋማት መፈጸም ብቃት እና ከዲፕሎማሲ አንጻር?
- የለውጡ የውጭ ግንኙነት ዋነኛ የአመለካከት እና የተግባር ልዩነት ምንድነው? ዘላቂ ወዳጅነት የመሰረትንባቸው ሀገራት እነማን ናቸው?
- ለስኬት እያበቁን ያሉ ቁልፍ የአመራርነት ሚናዎች ምንድናቸው? በሀገራችን ቁልፍ የአመራር ክፍተቶች እና ውድቀቶች ምንድናቸው? በተለይም ለችግር እየዳረጉን ያሉ ቁልፍ የአመራር ክፍተቶች ምንድናቸው? በአመራር ክፍተት ምክንያት የተፈጠሩ ወይም የተባባሱ ቁልፍ ሀገራዊ ችግሮች ምንድናቸው? እንደ ብልጽግና አመራር ካለፈው መማር እና ማዳበር ያለብን ቁልፍ የአመራርነት ክህሎቶች ምንድናቸው? አንድ አመራር የብልጽግና አመራር የሚሆነው ምን ሲሆን ነው? ፓርቲያችን የአመራርን ክፍተት ለማረም እየተከተለው ያለው ስትራቴጂ ምንድነው? ምን ይጎድለዋል? ምን ይታረም?
- ከዚህ አመራር የቀሰሙትን እውቀት እና ያገኙትን ውጤት ከሚመሩት ተቋም፣ ከሚመሩት ክልል፣ ዞን ጋር በማስተሳሰር በዝርዝር አስረዱ? ከስልጠናው ተነስተው ቀጣይ ግለሰባዊ እቅድ እና ተቋማዊ እና አስተዳደራዊ እቅድ በዝርዝር ያስቀምጡ?