(አሰግድ ተፈራ)
ሼኽ መሐመድ ሁሴን አል- አሙዲ አቶ አብነት ገብረመስቀልን ህጋዊ ወኪላቸው አድርገው መስራት ከጀመሩ ሰላሳ ዓመት ዘልቋል። ከተለያዩ በሁዋላ በሁለቱም ወገኖች የተለያዩ የህግ ጥያቄዎች ተነስተዋል። አንዳንዶቹ ውሳኔ ሲያገኙ ቀሪዎቹ የፍርድ አፈጻጸም የሚጠብቁ ሲሆኑ በየደረጃው በፍርድ ሂደት ላይ የሚገኙም አሉ።
አቶ አብነት የተጠየቁትን እንዲከፍሉ ተለይቶና ኖክን ጨምሮ ማስረጃ ሰጥተውበት በቀረበው ክስ ላይ የተሰጠውን ምላሽ ያጤነው ፍርድ ቤት “ …ችሎትም በግራ ቀኙ ከቀረቡ ክስና መከላከያ መልስ ማስረጃዎች ብሎም በግራ ቀኙ ላይ በተደረገላቸው የክስ መስማት ምርመራ መሰረት በጉዳዩ ላይ እልባት ለመስጠት ክፍ/ስ/ህ/ቁ 247 እና 248 አኳያ የሚከተሉትን ጭብጦች ለይተናል…” ሲል የፍርድ አካሄዱን የለያቸውን ጭብጦች በመዘርዘር አመልክቷል።
ከሳሽ ሼክ መሐመድ ሁሴን አል-አሙዲ የካቲት 18 ቀን ጥቅምት 5 ቀን 2014 ዓ.ም ተሻሽሎ በተከሳሽ ላይ ባቀረቡት ክስ መነሻ የተሰጠ ፍርድ መሆኑን ጠቅሶ የሰጠው ፍርድ በውል ባልተገለጸ ምክንያት በአንዳንድ ሚዲያዎች አማካይነት ተዛብቶ ቢቀርብም፣ የፍርድ ሂደቱ እንደሚያስረዳው፣ አቶ አብነት የተከሰሱበትን ጉዳይ ትተው ባልተጠየቁበት ጉዳይ ላይ ምላሽ ሰጥተዋል።
ጉዳዩን የሚከታተሉ እንዳሉት ይህ አካሄድ የፍርድ ሂደቱን ከፖለቲካ ጋር በማገናኘት ለማዛባት፣ የተዛባ መረጃ ለማዳረስና ከክሱ አውድና ጭብጥ ውጪ በክሱ ያልተነሳ ጉዳይን ለማጉላት የተደረገ እንደሆነ ያምናሉ።
በመዝገብ ቁጥር ኮ/መ/ቁ ከሳሽ ያቀረቡትን ክስ ባጭሩ ጨምቆና ሰብስቦ ብይኑን ያሳለፈው ፍርድ ቤቱ እንዳመለከተው፣ ከሳሽ የናሽናል ኦይል ኢትዮጵያ ኃላፊነቱ የተወሠነ የግል ማህበር / ኖክ ሰባ ከመቶ የአክሲዮን ባለቤት ናቸው። ተከሳሽ ደግሞ አስራ አምስት እጅ ድርሻ አላቸው። ተከሳሽ “ቀደም ሲል ባለሃብቱን ከማወቃቸው በፊት ምንም ያልነበራቸው እንደመሆናቸው የአስራ አምስት ከመቶ አክሲዮን ድርሻቸውን ክፍያ እንዴትና ከየት አምጥተው ከፈሉ?” የሚለውን ጥያቄም የሚያነሱ አሉ። ይህ ጥያቄ ዛሬ ሳይሆን ቀደም ባሉት ዓመታት የተለያዩ ጉዳዮችን እየተንተራሱ ከሚነሱባቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ ነው።
ኩባንያው ኖክ እ.ኤ.አ ከ2012 እስከ 2021 በኢትዮጵያ አቆጣጠር ደግሞ ከ2004 ዓ.ም እስከ 2013 ዓ.ም ድረስ በአስር ዓመታት ውስጥ ካተረፈው ትርፍ ላይ ለከሳሽ ይደርሳቸዋል ተብሎ በኩባንያው በሰነድ የተረጋገጠው አጠቃላይ የትርፍ ድርሻ ብር 2,841,324,375.50 (ሁለት ቢሊዩን ስምንት መቶ አርባ አንድ ሚሊዩን ሦስት መቶ ሃያ አራት ሺ ሦስት መቶ ሠባ አምስት ብር ከአምሳ ሳንቲም) እንደሆነ ለፍርድ ቤቱ አሳውቋል።
“ ከታክስ በኋላ ለከሳሽ እንዲከፈል ከተያዘው ብር 2,557,191,936. ሁለት ቢሊየን አምስት መቶ አምሳ ሰባት ሚሊዩን አንድ መቶ ዘጠና አንድ ሺ ዘጠኝ መቶ ሰላሳ ስድስት ብር ከሠማኒያ ሠባት ሳንቲም) የትርፍ ድርሻ ውስጥ ብር 907,645,937.47 (ዘጠኝ መቶ ሠባት ሚሊዮን ስድስት መቶ አርባ አምስት ሺ ዘጠኝ መቶ ሠላሳ ሠባት ብር ከአርባ ሠባት ሳንቲም) በኩባንያው እጅ የቆየ ሲሆን፣ ከብዙ መጻጻፍ በኋላ ኩባንያው ወደ ከሳሽ የባንክ ሂሳብ ገቢ ለማድረግ ህዳር 14 ቀን 2014 ዓ.ም በተጻፈ ደብዳቤ የከሳሽን የሂሳብ ቁጥር በድጋሜ እንድናሳወቅ ገልፆልናል። ተከሳሽ የከሳሽን የትርፍ ድርሻ በተመለከተ በፍ/ህ/ቁ. 2209 መሠረት አለመፈፀሙንና ጉዳት ማድረሡን ያሳያል” የሚለው የፍርድ ሪፖርት ተከሳሽ የተላለፈላቸውን ገንዘብ ባለማድረሳቸው ከሳሽን እንደበደሉ አመልክቷል።
ከታክስ በኋላ ለከሳሽ እንዲከፈል ከተያዘው ብር 2,557,191,936 ብር ላይ 907,645,937.47 በኩባንያው እጅ ሲቆይ ቀሪው ብር 1,649,545,999.4 (አንድ ቢሊዮን ስድስት መቶ አርባ ዘጠኝ ሚሊዮን አምስት መቶ አርባ አምስት ሺ ዘጠኝ መቶ ዘጠና ዘጠኝ ብር ከአራት ሳንቲም) የትርፍ ድርሻ በተመለከተ ከሳሽ እና ተከሳሽ ሠጡ በተባሉ የተለያዩ ክፍያ ትዕዛዞች በተለያዩ አካላትና ግለሠቦች ብር 787,083,349 (ሠባት መቶ ሠማኒያ ሠባት ሚሊዬን ሰማኒያ ሦስት ሺ ሦስት መቶ አርባ ዘጠኝ ብር) እንደተከፈለ (Paid) ኩባንያው ይፋ አድርጓል። የፍርድ ውሳኔ፣ የክስ ማመልከቻና ጭብጥ ከሚለው ውጪ የክሱንና የፍርዱን አውድ ያስቀየረው መረጃ የተነሳው እዚህ ላይ ነው።
አቶ አብነት ላይ የተመሰረተው ክስ ምንድን ነው?
አቶ አብነት በርካታ ክሶችና የክስ አፈጻጸም ላይ የሚገኙ ቢሆንም፣ በዚህ ሪፖርት በተጠቀሰው የክስ መዝገብ አቶ አብነት ላይ የተመሰረተው ክስ ከሳሽ ሼክ መሐመድ ሁሴን አል-አሙዲ በሰጡዋቸው ውክልና መሰረት ወደ ግል ኪሳቸው በሚታወቅ የሂሳብ አካውንት የተላለፈላቸውን፣ እሳቸውም በምላሻቸው ያላስተባበሉትን ሃብት እንዲመልሱ ነው። ይህም ሃብት ሰባ ከመቶ የድርሻባለቤት ከሆኑበት ከኖክ የተላለፈላቸውን 852,462,650 (ስምንት መቶ አምላ ሁለት ሚሊዮን አራት መቶ ስልሳ ሁለት ሺ ስድስት መቶ አምሳ ብር) ነው።
የከሳሽ ጠበቃ አቶ ሰለሞን ለኢትዮሪቪው በስልክ “ለጊዜው” ሲሉ የገለጹት ክስ ከላይ በተባለው መሰረት ተከሳሽ ያላስተባበሉት፣ በሰነድ የተደገፈ የከሳሽን የትርፍ ድርሻ ሃብት ከኖክ የተላለፈላቸውን 852,462,650 (ስምንት መቶ አምላ ሁለት ሚሊዮን አራት መቶ ስልሳ ሁለት ሺ ስድስት መቶ አምሳ ብር) እንዲመልሱ ነው። ሌላ የተጠየቀ ጥያቄም ሆነ ክስ የለም። ብይኑም የሚያስረዳው እሱኑ ነው። ከዚህ ውጭ ያለው ጉዳይና ከክሱ ጋር ያልተገናኘ ወይም በክሱ ውስጥ ያልተካተተ ጉዳይ የሰሙት ከሚዲያ እንደሆነ አመልክተው፣ የሚመለከታቸው አካላት ማስተካከያ እንዲያደርጉበት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። አሁን ላይ በክስ ባይካተትም አስፈላጊው ማጣራት ተደርጎ ወደፊት ጥያቄ ሊነሳ የሚችልበት የፍርድ አካሄዱ ክፍት እንደሆነ ግን አልሸሸጉም።
ውሳኔው ይህ ከሆነ ክሱና ውሳኔው ለምን ተዛብቶ እንዲቀርብ ተፈለገ
በክስ ጭብጥ ውስጥ ባልተካተተና ባልተከሰሱበት ጉዳይ የብልጽግናን፣ የመንግስትን ታላላቅ ተቋማት፣ ባለስልጣናትን በደፈና እና አንዳንድ ግለሰቦችን በማንሳት ክፍያ መፈጸማቸውን ማንሳት የፈለጉበትን ምክንያት እንዲያስረዱ አቶ አብነትን የዕጅ ስልክ ላይ ተደጋጋሚ ሙከራ ብናደርግም ምላሽ ሊሰጡ አልቻሉም። የጽሁፍ መልዕክትም እንዲደርሳቸው ቢደረግም ያሉት ነገር የለም። ምላሽ ካላቸው ግን ለማስተናገድ በሩ ክፍት ነው።
በተለያዩ ክፍያ ትዕዛዞች በተለያዩ አካላትና ግለሠቦች ብር 787,083,349 (ሠባት መቶ ሠማኒያ ሠባት ሚሊዬን ሰማኒያ ሦስት ሺ ሦስት መቶ አርባ ዘጠኝ ብር) መከፈሉን በሰነድ መረጋገጡ የፍርድ ሪፖርቱ ተመልክቷል። ኢትዮሪቪው ባገኘችው መረጃ የተጠቀሰው መጠን ብር ክፍያ የተከናወነውም ከሳሽ ከግል ሂሳባቸው ለኖክ ካሰገቡት ሃብት እንጂ ኖክ ላይ ባላቸው የሰባ ከመቶ ድርሻ ትርፍ ስሌት ላይ አይደለም። ፍርድ ቤቱም ይህን ከኖክ በሰነድ በቀረበለት ዝርዝር አረጋግጧል። ከኪሳቸው አውጥተው እንዳበደሩም አመልክቷል።
ተከፈለ የተባለው 787 ሚሊዮን ብር ከየት መጣ? እንዴትስ አቶ አብነት ዋና ጉዳይ አደረጉት?
በፍርድ ሰነዱ ላይም ሆነ በከሳሽ ጠበቃ ማብራሪያ ለጊዜው ክስ እንዳልቀረበበት የተገለጸውና ለተለያዩ አካላት ተሰጠ የተባለው 787,083,349 (ሠባት መቶ ሠማኒያ ሠባት ሚሊዬን ሰማኒያ ሦስት ሺ ሦስት መቶ አርባ ዘጠኝ ብር) ከየት መጣ? በሚል የፍርድ ሰነዱንና መረጃዎች ለማየት ሙከራ ተደርጓል። በተለይም ኖክ ገንዘቡ ከከሳሽ የግል ኪስ የወጣ እንደሆነ ከምክንያት ጋር አስረድቷል።
ኖክ እንዳረጋገጠው ብሩ ከሳሽና የሰባ ከመቶ አክሲዮን ባለድርሻ ሼኽ መሐመድ ሁሴን አል- አሙዲ ከግል ኪሳቸው የወጣ እንጂ ከድርጅቱ ከተገኘ የትርፍ dividend ድርሻ አካል አይደለም። የተከሳሽ ጠበቃም ያረጋገጡት ይህንኑ ነው። ሼኽ መሐመድ ሁሴን አል- አሙዲ ለኖክ በውጭ ምንዛሬ በብድር መልኩ የሰጡትን ገንዘብ ድርጅቱ እዳውን መክፈል ስላለበት በኢትዮጵያ ብር ተሰልቶ ከተመለሰላቸው ብር ላይ ነው ለተለያዩ ተቋማት፣ ባለስልጣናት፣ አንዳንድ ግለሰቦችን፣ ለብልጽግና ወዘተ ተሰጠ የተባለው ገንዘብ ወጪ የሆነው። ያም ሆኖ ለጊዜው በክሱ አልተካተተም። ነገር ግን በሂደት ሲፈለግ ክስ ሊመሰረትበት እንደሚችል ጠበቃው ገልጸዋል። ፍርድ ቤቱም ጥያቄውን ተቀብሏል።
“የሠውና የሠነድ ማስረጃዎች አሉኝ ተከሳሽ ከከሳሽ ጋር በነበረኝ የረጅም አመታት የንግድ ስራ ግንኙነትና በውክልና ስልጣኔ ለከሳሽ የንግድ ስራ ውጤታማነት በከፍተኛ ጥበብ ቅንነትና ግልጽ’ኝነት እንዲሁም ያለምንም ክፍያ የሰራሁላቸው በመሆኑ ታላቅ ምስጋና እንዲሁም ተገቢው የድካም ዋጋ ክፍያ የሚገባኝ ሆኖ እየለ ክስ መቅረቡ ተገቢነት የለውም ከሳሽ በራሳቸው ትዕዛዝ እውቅናና መተማመኛ ፈራሚነት፣ አጽዳቂነት ከኩባንያው ያገኘትን የትርፍ ክፍፍል ለተለያዩ ግለስቦችና አካለት ክፍያ እንዲፈፀምበት ሲያደርጉ ከመቆየታቸውም በላይ ወደ ተከሳሽ የባንክ አካውንት የገባውን በከሳሽ የተሟላ አውቅናና ተጨባጭ መተማመኛ በመስጠት ለተለያዩ ግለሰቦችና አካለት እንድከፍል ያደረጉ ስለመሆናቸው ተጨባጭ የሰነድ ማስረጃዎች እያሉና የራሳቸው የሠነድ ማስረጃዎችም ይህንኑ የሚያስገነዝቡ ሆነው እያለ ተከሳሽ በተወካይነት ተገቢውን ኃላፊነት እንዳልተወጣሁና የከሳሽን ጥቅም በመጉዳት ለራሴ ጥቅም እንደሠራሁ አድርገው የብር 852,462,650 ከፍያ ጥያቄ ማቅረባቸው ያለምንም ማስረጃ በመሆኑ ክሱ ውድቅ እንዲደረግ እንዲሁም በፍ/ስ/ስ/ህ/ቁ 216 (4) መሰረት የቀረበው የፍርድ ቤት ፈቃድ መጠየቅ የሚቻልበት የህግ መሰረት የለም” ሲሉ ተከሳሽ ወጭና ኪሳራ የማቅረብ መብታቸው ተጠብቶ ክሱ ሙሉ በሙሉ ውድቅ እንዲደረግ በማለት ዳኝነት ጠይቀዋል። ከመከላክያ መልሳቸው ጋርም የሠውና የሰነድ ማስረጃ ዘርዝረው ማቅረባቸውን የፍርድ ሪፖርቱ ያስረዳል።
“በከፍተኛ ጥበብ ቅንነትና ግልጽ’ኝነት እንዲሁም ያለምንም ክፍያ የሰራሁላቸው በመሆኑ ታላቅ ምስጋና እንዲሁም ተገቢው የድካም ዋጋ ክፍያ የሚገባኝ ሆኖ እየለ ክስ መቅረቡ ተገቢነት የለውም” ማለታቸውን ተከትሎ የድርጅት የፋይናንስ ኃላፊን አስፈርመው ከስር ሼክ መሐመድ ሁሴን አል አሙዲ በሚል ጽፈው የደሞዝ ስምምነት ሳይኖር “ውዝፍ ደሞዝ አለኝ” በሚል 14 ሚሊዮን ብር መውሰዳቸውን ሰነድ በማሳየት ወደፊት ዝርዝሩን እንደሚያቀርቡ ጉዳዩን የሚከታተሉ ለዝግጅት ክፍላችን ገልጸዋል። ይህ በህግ ያልተቆረጠን ገንዘብ መውሰድ ወነጀል መሆኑን አመልክተው በርካታ ተያያዥነት ያላቸው ለሰሚ ግራ የሚያጋቡ ጉዳዮች መፈጸማቸውን ይጠቁማሉ።
የአቶ አብነት ወንድም ለሼኽ መሐመድ ዶላር አበዳሪ ሆነው፣ ብድሩንም በቀነ ገደብ ለመለስ መስማማታቸውን የሚገልጽ ሰነድ ተዘጋጅቶ አቶ አብነት በውክላናቸው መሰረት ለወንድማቸው ውልና ማስረጃ በመሄድ ወካይ ምንም ሳያውቁ ባለ ዕዳ የሚያደርጋቸውን ውል ፈጽመዋል። ከዚህም በተጨማሪ ራሳቸው አቶ አብነት ለወከሏቸው ባለሃብት አበዳሪ ሆነው ብድሩን ለመክፈል የተስማሙበት ሰነድ ተዘጋጅቶ፣ አቶ አብነት ለወንድማቸው ውክልና ሰጥተው ሰንድ ላይ የፈረሙበት አግባብ መኖሩንም አክለው በመግለጽ “በታማኝነትና በቀናነት” ስለማገልገላቸው ያነሱትን ጉዳይ “ሆድ ይፍጀው” ሲሉ ይደመድማሉ።
ምንም ተባለ ምን ለጊዜው ፍርድ የተሰጠበት ቀሪው ለከሳሽ የሚደርሳቸው ብር 852,462,650 (ስምንት መቶ አምሳ ሁለት ሚሊዮን አራት መቶ ስልሳ ሁለት ሺ ስድስት መቶ አምሳ ብር) የትርፍ ድርሻ ዋናው የክሱ አንጓ መሆኑን ሰነዱ ያስረዳል።
“…በመሆኑም በተለያዩ ግለሠቦችና አካላት ተከፈለ የተባለው ገንዘብ በተመለከተ ወደፊት በማን ትዕዛዝና ለምን ዓላማ ክፍያዋቹ እንደተፈፀሙ ማስረጃ አደራጅተን ስንጨርስ ክስ የምናቀርብበት መሆኑን እንደተጠበቀ ሆኖ ተከሳሽ ከላይ ባስቀመጥነው ሰንጠረዥ ላይ በተመለከተው መሠረት በተለያዩ ቀናት በውክልና የተቀበሉትን ብር 852,462,650 (ስምንት መቶ አምላ ሁለት ሚሊዮን አራት መቶ ስልሳ ሁለት ሺ ስድስት መቶ አምሳ ብር) የከሳሽን የትርፍ ድርሻ ለወካያቸው ለአሁን ከሳሽ መስጠት ሲገባቸው እስካሁን ድረስ ገንዘቡን እንዲሠጡ በጽሁፍ ቢጠየቁም ለመስጠት ፍቃደኛ አልሆኑም”
እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ በከሳሽ ሼክ መሐመድ ሁሴን አል-አሙዲን እና በተከሳሽ አቶ አብነት የክስ መዝገብ የፍርድ ቤት የሰጠውን ብይን አውድ እንዲሰት ተደርጎ በአንዳንድ ሚዲያዎች ተዘግቧል። ከሳሽ በክሳቸው ያላነሱትና ብይን እንዲሰጣቸው ባልጠየቁባቸው ጉዳዮች ተከሳሽ ሆነ ብለው ክሱን ሌላ መልክ ለማስያዝ መሞከራቸው በምን መነሻው ምን እንደሆነ በትክክል ባይገልጹም፣ ፍላጎቱ ውሳኔውን ለማዛባት ከመፍለግ የመነጨ እንደሆነ ያምናሉ።
” ለመንግስት ታላላቅ ተቋማት፣ ለብልጽግና ፓርቲ ወዘተ ብር መሰጠቱ ከጉዳዩ ጋር ባይገናኝም መግለጽ የተፈለገው ጉዳዩን ወደ ፖለቲካ ቅኝት ለማዞርና የፍርድ ውሳኔውን ቀጥተኛነት ለማሳት ታስቦ ይመስለኛል” ሲሉ ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ የቀድሞ ወዳጃቸው አስተያየት ሰጥተዋል። አክለውም “ይህ ዓይነቱ የድርጅትና የተቋማ ወይም የግለሰቦች ሚስጢር በየትኛውም ደረጃ ይጥቀም አይጥቀም ሳይታወቅ ይፋ ማድረጉ ለማንም የማይጠቅም መጥፎ ባህል ነው። እኔ በርካታ ጉዳዮችን አውቃለሁ ግን ዛሬ ላይ ተነስቼ አልቀባጥርም” ብለዋል።
ተከሳሽ ከከሳሽ የወሰዱትን ወይም የተሰጣቸውን ውክልና አግባብ፣ ደረጃና ኃላፊነት መዝኖ፣ ከህግ አንጻር ውላቸውን አጥርቶ በርካታ ግንቶቹንና የህክ አመክንይዎችን የጠቀሰው ፍርድ ቤቱ፣ ተከሳሽ “…ስራዎችን እንጅ ከዚያ አልፎ ከኩባንያዎች ስራ አመራር ውጭ የሆነውን የስጦታ መስጠት ስራን የሚያካትት ነው ብሎ ችሎቱ የሚያየው አይደለም ፡፡ ይልቁንም ስጦታን በተመለከተ በፍ/ህ/ቁ 2205(2) ላይ በግልጽ እንደተመለከተው አንድ ሠው ስጦታ ለማድረግ እንዲችል ተወካዩ ልዩ የውክልና ስልጣን የሌለው ከሆነ የስጦታ ተግባር መፈፀም እንደማይችል በግልጽ ተደንግጓል” የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሷል።
“.. በመሆኑም ከሳሽ በተከሳሽ ስጦታ የማድረግ ውክልና የሠጠው መሆኑን የሚያሳይ በውክልና ሠነዱ ላይ ዝርዝር ተግባር በሌለበት አግባብ ይልቁንም በውክልና ሠነዱ ላይ በግልጽ የተመለከተው ዝርዝር ተራ ቁጥር 10 ላይ ተከሳሽ በእኔ ስም ስጦታ እንዲቀበል የሚል እንጅ ስጦታ እንዲሠጥ የሚል ባልተዘረዘረበት ሁኔታ በግልጽ ተከሳሽ በልዩ ውክልና ባልተሠጠው የስጦታ መስጠት ተግባር ተከሳሽ የሚፈጽመው ተግባር ‘ ተግባሩ የስጦታ እስከሆነ ድረስ በስልጣኑ መጠን እና ልክ ነው የሚያስብል አይሆንም” ብሏል።
ፍርድ ቤቱ በፍርድ አሰጣጡ ውሳኔ ሪፖርቱ ላይ ባስቀመጠው መሰረት ከሳሽ ተከሳሽን “ለጊዜው” የጠየቁት ከናሽናል ኦይል ኢትዮጵያ ኃላፊነቱ የተወሠነ የግል ማህበር (ኖክ) በውክልና የተቀበሉትን ወይም ወደ ግል ሂሳባቸው የዞረላቸው ብር 852,462,650 (ስምንት መቶ አምላ ሁለት ሚሊዮን አራት መቶ ስልሳ ሁለት ሺ ስድስት መቶ አምሳ ብር) የከሳሽን የትርፍ ድርሻ ለወካያቸው ለአሁን ከሳሽ መስጠት ሲገባቸው እስካሁን ድረስ ገንዘቡን እንዲሠጡ በጽሁፍ ቢጠየቁም ለመስጠት ፍቃደኛ አልሆኑም።
“ ስለሆነም ተከሳሽ ለከሳሽ ከሚደርሳቸው የትርፍ ድርሻ ላይ ከናሽናል ኦይል ኢትዮጵያ ኃላፊነቱ የተወሠነ የግል ማህበር በውክልና የተቀበሉት ብር 852,462,850 (ስምንት መቶ አምሳ ሁለት ሚሊዮን አራት መቶ ስልሳ ሁለት ሺ ስድስት መቶ አምሳ ብር) የትርፍ ድርሻ በፍ/ህ/ቁ. 2210(2) መሠረት ከነወሰዱ እንዲከፍለን እንዲወሰንልን እንጠይቃለን፤ ለተለያዩ ግለሠቦች እና አካላት ተከፈለ የተባለውን የትርፍ ድርሻ በተመለከተ ወደፊት ማስረጃ አሰባስበንና አጠናቀን ስንጨርስ በፍ/ስ/ስ/ህ/ቁ. 218(4) መሠረት ክስ የማቅረብ መብታችንን እንዲጠብቅልን፤ የወጭና ኪላራ ዝርዝር አቅርበን የማስወስን መብታችን እንዲጠበቅልን እንጠይቃለን በማለት የክስ አቤቱታቸውን አቅርበዋል፡፡ ከክሱሡ ጋር የሠነድ ማስረጃ አያይዘዋል” የሚለው የከሳሽ የክስ ማመልከቻ አቶ አብነት ላልተከሰሱበት ክስ ምላሽ ማስጠታቸውን እንደሚያሳይ ጠበቃቸው አቶ ሰለሞን ለኢትዮሪቪው አስረድተዋል።
” በመጨረሻም የተያዘው ጭብጥ ተከሳሽ የውክልና ግዴታውን ካልተወጣ ኃላፊነት አለበት ወይ? ምን ያክል የገንዘብ መጠን የሚል ነው? በዚህ ረገድ አስቀድመን በተመለከተ ነው አግባብ መሰረት ተከሳሽ በተስጠው እንደራሴነት ከወኪልነቱ ስልጣን ወሰን ሳያልፍ በከሳሽ ስም የወክልና ተግባሩን መፈፀም እየተገባው ያልፈፀመ እንዲሁም ተግባሩን ሲፈፅምም ተከሳሽ የማያወቅና ለከሳሽ ጥቅም ያልፈፀመ ለመሆኑ ድምዳሜ ላይ ችሎቱ የደረሰና በፍ/ህ/ቁ 2190 እና 2197 መሰረት አግባብ ተከሳሽ ኃላፊነት አለበት ተብሏል፡፡ ተከሳሽ ኃላፊነት ያለበት ከሆነ ምን ያክል ገንዘብ መጠን የሚለው ከሳሽ ከነበራቸው የአክሲዮን ትርፍ ድርሻ በድምሩ 974,962,650 የተላለፈላቸው ቢሆንም በራሳቸው በተከሳሽ ትዕዛዝ ወደ የዳሽን ባንክ የተላለፈላቸው የገንዘብ መጠን 852,462,650 ብር መሆኑን የኦዲት ሪፖርቱ በጠቅላላ እንዲሁም የኦዲት ሪፖርቱን የገለፀው የሙያ ሪፖርት በተለይ ገጽ 10 እና 11 የሚያስገነዝብ በመሆኑና ተከሳሽ ይህንን በውክልና ስልጣናቸው ያገኙትን ብር 852,462,650/ስምንት መቶ ሃምሳ ሁለት ሚሊዬን አራት መቶ ስልሳ ሁለት ሺህ ስድስት መቶ ሃምሳ ብር/ለከሳሽ ሊከፈሉ ይገባል በሚል በሙሉ ድምጽ ፍርድ ተሰጥቷል፡፡ ስለሆነም ተከታዩ ተወስኗል” ይላል የፍርድ ሂደቱ ሪፖርት ድምዳሜ የገለልተኛ ኦዲት ሪፖርቱን አካቶና ከላይ የተነሱትን ጭብጦች ተንተርሶ።
ው ሳ ኔ
1) ተከሳሽ በውክልና ስልጣኑ መሰረት በግል አካውንት በራሱ ትዕዛዝ ያስተላለፈውን ብር 852,462,650/ስምንት መቶ ሃምሳ ሁለት ሚሊዬን አራት መቶ ስልሳ ሁለት ሺህ፣
2) ስድስት መቶ ሃምሳ ብር/ክፍያ ከቀረበበት ቀን ጀምሮ 27/03/2014 ዓ/ም የሚታሰብ 9% አመታዊ ወለድ ጋር አክሎ አንዲከፈል ተወስኗል ይፃፍ፡፡
3) ወደ ፊት በፍርድ የመጠየቅ መብትን በተመለከተ ወደ ፊት የሚያቀረበለት ችሎት አይቶ የሚዳኝ እንጂ አስቀድሞ በዚህ ችሎት የሚታይ አይደለም ተብሏል።
4) ከሳሽ ወጭና ኪሳራ የመጠየቅ መብቱ ተጠብቋል የሚል ፍርድ ተሰጥቷል። ተከሳሽ የይግባኝ ባለ መብት እንደሆኑ ትገልጾላቸዋል። በዚሁ ውሳኔ መሰረት መዝገቡ ተዘግቷል ወደ መ/ቤት ይመለስ መባሉ የፍርድ ሰነዱ የመጨረሻ ገጽ ያስረዳል።
የማይነበብ የዳኛ ፊርማ አለው