በአዲስ አበባ አንዳንድ ኤምባሲዎች የኢትዮጵያን ሃብት በመዝረፍና የጥቁር የውጭ ምንዛሬ ንግድ ላይ መሰማራታቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ አስታወቁ። እርምጃም እንደሚወሰድ አመለከቱ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህ ያሉት በተለያዩ ኩባንያዎች ስም ፣ በፍራንኮ ቫሉታ ስም ፣ በወርቅ ንግድ ስም የኢትዮጵያን ገበያ የሚያዛቡ ግለሰቦች መኖራቸውን ሲያስታውቁ ነው። ሹፌሮች ፣ የማስተላለፍ ስራ የሚሰሩ ሳይቀሩ የብላክ ማርኬት ዶላር ወደ አንዳንድ ሀገራት በባቡርና በቅጥቅጥ መኪና እንደሚያግዙ አመልክተዋል።
በጥቅሉ መንግስት መረጃ እንዳለው ጠቅሰው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለፓርላማው እንዳሉት ስም ሳይጠቅሱ ኢትዮጵያን መዝረፍ መብታቸው ያደረጉ አገራት ኤምባሲዎች መኖራቸውን ተናግረዋል። ” ከሀገር ወርቅ ይወጣል ፣ ዶላር ይወጣል ይሄን ዘረፋ መከላከል ያስፈልጋል። ህገወጥነት ፣ ኮንትሮባንድ ዘራፊዎች በውስጣችን ያሉ ሰዎች ተጨምረውበት የሚደረግ ማንኛውም ህግ ያልተከተለ ዘረፋ መከላከል አለብን” ብለዋል።
” አንዳንድ አገራት በዚህ መንገድ ኢትዮጵያን መዝረፍ መብት እንደሆነ አድርገው የሚያስቡ አሉ” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ህዝብ በየአቅጣጫው የሚያነሳውን ሃቅ ይፋ አድርገዋል። አክለውም እነዚሁ ኢትዮጵያን መዝረፍ መብታቸው አድርገው የሚያዩ አገራት ኢትዮጵያ ግን ከብሔራዊ ጥቅሟ አንጻር ጥያቄ ስታነሳ የሚያሰሙትን ድምጽና አቋም “እንደ ግስላ ይሆናሉ” ብለዋል። እነዚህ አገራት እኛን መዝረፍና የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም አለማክበራቸው አግባብ እንዳልሆነም አመልክተዋል።
በዚህ ደረጃ የጠቀሱትን ኤምባሲ ወይም አገር ኢትዮጵያ የባህር በር ስትል ግስላ እንደሚሆኑ መግለጻቸውን ተከትሎ ንግግራቸው ” … ኢትዮጵያ የጋራ” በሚል አዲስ አበባ ተቀምጠው እየዘረፉ ያሉትን አካላት ህዝብ የሚያጠራበትን ንግግር የሚያስታውስ ሆኗል።
አብይ አህመድ ” ነገር እንዳናበላሽ ነው የታገስናቸው ስራቸው ብላክ ማርኬት ማሯሯጥ የሆኑ ኤምባሲዎች አሉ ” ካሉ በሁዋላ እርምጃ እንደሚወሰድ ተናግረዋል። የሚወሰደው እርምጃ ምን እንደሆነ ግን አላብራሩም።
የኤርትራ ኤምባሲ በስም ባይጠቀስም ጠቅላይ ሚኒስትሩ መግለጽ ካልፈለጓቸው ኤምባሲዎች መካከል አንዱ እንደሆነ ንግግራቸውን ተከትሎ አብዛኞች አስተያየት ጽፈዋል። ሻዕቢያ በርሃ ከነበረበት ጊዘ አንስቶ ቡድን አደረጃቶ ኢትዮጵያን ሲዘርፍ እንደነበር ይታወሳል። ከ1983 በሁዋላ አዲስ አበባ የተተከለው ኤምባሲ በህገወጥ ንግድና በጥቁር ገበያ ንግድ መሰማራቱ በተደጋጋሚ ሲገለጽ ቆይቷል። “ኢትዮጵያ የጋራ ኤርትራ የግል” በሚለው ብሂል ህዝብ ኢትዮጵያ እየታለበች መሆኑን በተደጋጋሚ መንግስትን ሲጎተጉት ቆይቷል። ቀደም ሲልም ሆነ አሁን ያለው መሻከርም ከዚሁ “ስዘርፍ ዝም በለኝ” የሚል እሳቤ የተነሳ እንደሆነ በርካታ መረጃ አለ። አብይ አህመድ ባይሉም ከኤርትራ በተጨማሪ የሶማሊያ ዲፕሎማቶችም በተመሳሳይ በዚሁ ስራ መሰማራታቸው የመንግስትን ክትትል የሚያቁ አስቀድመው መረጃ በሰጡን መሰረት መዘገባችን አይዘነጋም።
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን አስመክተው ሲያብራሩ ባላፉት ሶስት ወራት ከወጪ ንግድ 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን ሲያስታውቁ እንዳሉት “ባለፉት ሶስት ወራት ከወርቅ ወጪ ንግድ 500 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ተገኝቷል፡፡ ይህም የወርቅ ምርት ምን ያህል ለህገ ወጥ ንግድ ተጋልጦ እንደነበር የሚያሳይ ነው” ያሉት አብይ አሕመድ፣ ዝርፊያው ምን ያህል የከፋ እንደሆነ የሚያሳይ ነው ብለዋል። ዝርፊያው ክፉኛ እንደነበር ከኢኮኖሚ ማሻሻያው በሁዋላ የተገኘው ሃብት ምስክር መሆኑንም ገልሰዋል።
” እነሱ ላይ ጥብቅ ክትትል ይደረጋል የማይታረሙ ከሆነ እርምጃ ይወሰዳል። ጤናማ ዝምድና የማያደርግ ማንም ኤምባሲ እኛ አንፈልግም እኛ የምንፈልገው ጤናማ ህጋዊ ስርዓት ያለውን መንገድ የሚከተል ብቻ ነው ” ያሉት አብይ አህመድ ” በጥቁር የሚሰሩ ነገር እንዳናበላሽ ብለን ነው የታገስናቸው” ሲሉ ከዚህ በሁዋላ ይህ እንደማይቀጥል አስታውቀዋል።
በቴሌግራም ይከተሉን – https://t.me/+f_kxmaPjD-9jYTdk