በመጀመሪያ ንግግራቸው “አሰናካይ ሐሳቦችን በማረቅ ወደ ፊት መራመድ አስፈላጊ ነው፡፡ ማስተዋል፣ ማሰላሰል፣ አርቆ ማሰብ እና ትዕግስት የኢትዮጵያ የጽናት ዋልታዎች ናቸው”ሲሉ የተደመጡት ፕሬዘዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ በርካታ ጉዳዮችን አንስተዋል። በማህበራዊ፣ በጸጥታ፣ በኢኮኖሚና በተለያዩ ጉዳዮች ላይ መረጃ ያቀረቡት ፐሬዚዳንቱ ርዕስ ለይተው ነው ያቀረቡት።
ኢኮኖሚያችን አዲስ የታሪክ እጥፋት ላይ ነው
ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ ባደረጉት ንግግር የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እውን፣ ገቢር እና ገበያ መር እየሆነ በዓለም ተወዳዳሪ እንዲሆን መሰረቱን ከነጠላ ዘርፍ ተኮርነት ወደ ብዙሃን ዘርፍ ኢኮኖሚ እያሸጋገረ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም የህዝቦች ፍትሐዊ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ መሰረት እየጣለ እንደሚገኝ ጠቅሰው በ10 ዓመት የልማት ዕቅድ ውስጥ ለማከናወን የተያዙ ዕቅዶችን ለማሳካት አወንታዊ አቅጣጫ እንደያዘ አመላካች ነው ብለዋል።
በ2016 በጀት ዓመት 8 ነጥብ 1 በመቶ ጥቅል ሀገራዊ የኢኮኖሚ እድገት ለማስመዝገብ መቻሉን ፕሬዚደንቱ ጠቅሰዋል።
የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርሙ ስጋቶችን እና ፈተናዎችን ወደ ዕድል በመቀየር ተጨባጭ ውጤቶችን እያመጣ ስለመሆኑ አመላካች ነው ብለዋል።
የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት 13.8 በመቶ እድገት ያሳየ መሆኑን በመግለጽ፤ በዚህም 3.9 ቢሊዮን ዶላር የኢንቨስትመንት ፍሰት መመዝገቡን ጠቅሰዋል።
በበጀት ዓመቱ ለ4 ሚሊዮን 250 ሺህ ዜጎች የስራ ዕድል ተፈጥሯል ያሉት ፕሬዚደንቱ ከዚህ ውስጥ የውጭ ሀገር የስራ ዕድል ስምሪት እና ሕጋዊ ማዕቀፍ በማስያዝ 379 ሺህ ዜጎች የውጭ ሀገር የስራ ዕድል ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
በሸቀጦች ወጪ ንግድ እና በአገልግሎት የውጭ ንግድ የታየው እድገትም ሀገሪቱን የኢኮኖሚ ስብራቶችን ለመጠገን የምታደርገው ጥረት በመልካም ጎዳና ላይ እንደሚገኝ አመላካች ነው ብለዋል።
የዋጋ ግሽበትን ለመቆጣጠር መንግስት ዘርፈ ብዙ ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ ከአቅርቦት አንጻር በምርት እና ምርታማነት ላይ ያተኮሩ ስራዎች ተጀምረው የዋጋ ግሽበትን ትርጉም ባለው መልኩ መቆጣጠር እንዳስቻሉ ተናግረዋል።
በተያዘው በጀት ዓመት የነሐሴ ወር አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት 17.2 በመቶ ሆኖ መመዝገቡን ጠቅሰው ይህም በ2015 ነሐሴ ወር ከተመዘገበው 28.8 በመቶ አጠቃላይ ዋጋ ግሽበት አንጻር ሲታይ ዝቅ ያለ ስለመሆኑ ነው ያነሱት።
በበጀት ዓመቱ ለ4 ነጥብ 3 ሚሊየን ዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠር እንደሚሰራ ገለጹ
ፕሬዚዳንቱ በ2107 ዓ.ም በመንግሥት የሥራ አቅጣጫዎች ላይ ባደረጉት ንግግር÷ ኢትዮጵያ ለውጭና ለሀገር ውስጥ ባለሃብቶች ተመራጭ እንድትሆን ትኩረት እንደሚሰጥ ተናግረዋል፡፡
ለዚህም በዘርፉ አስቻይ የሆኑ አሰራሮችን በመተግበር ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀዳሚ ከሆኑት የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት መዳረሻ ሀገራት አንዷ ሆና እንድትቀጥል ትኩረት ይደረጋል ነው ያሉት፡፡
ብቁና ተወዳዳሪ የሰው ሃይል በመፍጠር ረገድ በቅንጅት እንደሚሰራ ጠቅሰው÷ በዓመቱ ለ4 ነጥብ 3 ሚሊየን ዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠር መታቀዱን ገልጸዋል፡፡
ከዚህ ውስጥም 700 ሺህ የሚሆነው የውጭ ሀገራት የሥራ እድል መሆኑን ነው ፕሬዚዳንቱ ያስረዱት፡፡
በዲፕሎማሲ ረገድ ከጎረቤ ሀገራት ጋር ያለውን ሁለንተናዊ ግንኙነት በማጠናከርና ሀገራዊ ጥቅሞችን በማሳደግ በሰላም፣ በጸጥታ፣ በኢኮኖሚና በቀጣናዊ ትስስር የጋራ ጥቅምን በሚስገኙ ሥራዎች ላይ ትኩረት ይደረጋል ብለዋል፡፡
ሕዝቡን እየፈተኑ የሚገኙትን የኑሮ ውድነትና ሌብነት ትርጉም ባለው ሁኔታ ለመቀነሰ ይሰራል
በ2017 በጀት ዓመት ሕዝቡን እየፈተኑ የሚገኙትን የኑሮ ውድነት፣ ሌብነት እና ብልሹ አሰራርን ትርጉም ባለው ሁኔታ ለመቀነሰ በትኩረትና በትብብር እንደሚሰራ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ ተናገሩ፡፡
6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን የጋራ የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ተካሂዷል።
ፕሬዚዳንት ታዬ በወቅቱ እንዳሉት÷ ኢትዮጵያ ባሳለፍነው በጀት ዓመት በተለያዩ ተግዳሮቶች ውስጥ ሆና አመርቂ እድገት አስመዝግባለች፡፡
እድገቱን በተያዘው በጀት ዓመት ለማስቀጠል ሕዝቡን በከፍተኛ ሁኔታ እየፈተኑ የሚገኙትን ተግዳሮቶች ትርጉም ባለው ሁኔታ ለመቀነስ ይሰራል ነው ያሉት፡፡
በተለይም የኑሮ ውድነትን፣ ሌብነትን እና ብልሹ አሰራርን እንዲሁም የጸጥታ ስጋት፣ ኮንትሮባንድና ሕገ ወጥ ንግድን ለመቀነሰ በቅንጅት ይሰራል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ በሒደት ከሙስና እና ከብልሹ አሰራር የጸዳች እንድትሆን ሁሉም ባለድርሻ አካላት በትኩረትና በትብብር እንደሚሰሩ አመልክተዋል፡፡
የፍትሕ ስርዓቱን ጤናማነት እና የሰብዓዊ መብት አያየዝን ለማሻሻል በርካታ ጥረቶች እየተደረጉ እንደሚገኙም ለምክር ቤቶቹ አስረድተዋል፡፡
በኢትጵያ በተለያዩ ጊዜያት ያጋጠሙ የፍትህ መዛባቶች እና የመብት ጥሰቶችን በአግባቡ ለመቋጨት የሽግግር ፍትሕ ሥርዓትን ተግባራዊ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ዘላቂ ሀገራዊ ሰላምን ማስፈንና የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ጉዳዮች ናቸው
ዘላቂ ሀገራዊ ሰላምን ማስፈን እና የህግ የበላነትን ማረጋገጥ የቅድሚያ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ጉዳዮች ናቸው ሲሉ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀስላሴ ተናገሩ፡፡
በንግግራቸውም ከእንግዲህ በኢትዮጵያ ምድር ሃይልን በብቸኝነት መጠቀም መብት የመንግስት ተቋማት ብቻ መሆኑን ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል፡፡ ዓመቱን የዜጎችን ሰላምና ደህንነት የማስጠበቅ ሃላፊነት አፈፃፀም የሚሻሻልበት ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ ለምንገነባው ዘላቂ ሰላም ሁሉም የድርሻውን መወጣት አለበት ብለዋል፡፡ ይህም በህብረብሔራዊነት ያጌጠች ኢትዮጵያን የማፅናትን ምዕራፍ እዉን ያደርጋል፤ ሀገራዊ ምሰሶዎችን ያፀናል ሲሉም ገልጸዋል።
ዛሬም በድጋሚ መቀራረብ፣ መነጋገር፣ መከራከረ፣ መግባባት እንዲሁም አብሮ መቆም የመጨረሻ ግባችን ሊሆን ይገባል በማለት ጠቅሰው፤ ለዚህ ሁሉ ግን የመተማመን ዋጋ ላቅ ያለ መሆንን መረዳት እንደሚያስፈልግም ነው ያስረዱት፡፡
በእኛ በኩል ለመጪው ትውልድ የምሰጠው ስጦታ ይህ ሊሆን ይገባል፤ በሁሉም ረገድ ሰላምን የማምጣትና የማረጋገጥ ስራ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
ለዚህም ዋንኛው በኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በኩል የሚሰራው ስራ መሆኑን አንስተው፤ ኮሚሽኑ የዝግጅት ምዕራፍ ተግባራት አጠናቅቆ በ2016 ዓ.ም ወደ ምክክር ተግባርት መሸጋገሩን አስታውሰዋል፡፡
በዚህም አዲስ አበባን ጨምሮ በሁሉም ክልሎች ግብዓት የሚሆኑ ሃሳቦችንና ጥያቄዎችን ማሰባሰብ መቻሉን ገልፀው፤ ኮሚሽኑ እጅግ መሰረታዊ በሆኑ ጉዳች ላይ አካታች ምክክሮችን በማድረግ የተሻለ ሀገራዊ መግባባት ለመገንባ እየሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡
በሂደትም የመተማመን እና ተቀራርቦ የመስራት ባህልን ለማጎልበት መንገድ ይከፍታል ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ ሀገራዊ የምክክር ሂደቱን ለማሳለጥ ኮሚሽኑ የተጣለበትን ተስፋና የታለመለትን አላማ እውን እንዲያደርግ የሁሉም ድጋፍ እንደሚያስፈልገው ጠቁመዋል።
በመንግስት በኩል አሁንም ቢሆን የሰላም በሮች እንደተከፈቱ መሆናቸውን ገልጸው፤ በተናጠልም ይሁን በጋራ መንግስት በሰላማዊ መንገድ ለመነጋገር ሁልጊዜ ዝግጁ መሆኑንም አረጋግጠዋል፡፡
ከዚህ ውጪ የሃይል አማራጭን በመጠቀም ፖለቲካዊ ፍላጎትን ለሟሟላት የሚደረጉ ማናቸውንም እኩይ ተግባራት መንግስት በልበ ሰፊነት ሚያልፍበት እድል እጅግ ጠባብ ነው ብለዋል፡፡
በልበ ሰፊነት ብዙ ጊዜ ተሰጥቷል፤ የህዝቡን የዘመናት አብሮነት እሴት የሚያላሉ ተግባር በሚፈፅሙ ግለሰቦችና ቡድኖች፣ ህዝብን ከህዝብ በሚያጋጩ አካላት ላይ መንግስት እርምጃ ይወስዳል ነው ያሉት፡፡
በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ከ21 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ተገኝቷል
በ2016 በጀት ዓመት በተለያዩ መስኮች ከ21 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ መገኘቱን የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ ተናግረዋል።
በ2016 በጀት ዓመት የወጪ ንግድ ምርቶች ስብጥር እና አዳዲስ የገበያ መዳረሻዎችን በማስፋት ከወጪ ንግድ 3 ነጥብ 8 ቢሊየን ዶላር መገኘቱንም ገልጸዋል፡፡ ይህም ከ2015 በጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ4 ነጥብ 8 በመቶ ብልጫ እንዳለው ነው ያስረዱት፡፡
በበጀት ዓመቱ ከሸቀጦች የወጪ ንግድ፣ ከአገልግሎት ዘርፍ፣ ከሃዋላ እና ከቀጥተኛ ኢንቨስትመንት በአጠቃላይ ከ21 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር የውጭ ምንዛሪ መገኘቱንም ተናግረዋል፡፡
የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም በዚህ ዓመት እንደሚተገበር ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ ገለጹ
አጠቃላይ የሲቪል ሰርቪሱን ለማዘመን እና የሚፈለገውን ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት ያለመው የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም በዚህ ዓመት ተግባራዊ መደረግ እንደሚጀምር ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ አስታውቀዋል።
የዚህ ሪፎርም ዋና ዓላማ የሥራ ፈጠራ እና ተወዳዳሪነት ባህል ማድረግ እንደሆነ የገልጹት ፕሬዚዳንቱ፤ ቀጣሪ መንግሥት ነው የሚለውን የተሳሳተ አስተሳሰብ በማስቀረት አገልግሎት እና ፈጠራን ማዕከል ወደአደረገ ተወዳዳሪነት ለመለወጥ መሆኑ ጠቁመዋል።
የመንግስት ተቋማት ሃሳብን፣ ፈጠራንና ምርታማነት ላይ ትኩረት አድርገው ለውጥ እንዲያመጡ ይጠበቃል ብለዋል ፕሬዚዳንቱ። በመንግሥት ተቋማት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደገፈ አገልግሎትን ለመስጠትም ሁለንተናዊ ድጋፍ እንደሚደረግ ጠቁመዋል።
በቴሌግራም ይከተሉን እባክዎ https://t.me/+f_kxmaPjD-9jYTdk